1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዋግህምራ ሁለት ወረዳዎች «ሰሚ አጥተዋል» መባሉ

ሰኞ፣ መጋቢት 4 2015

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ የሁለት ወረዳ ነዋሪዎች አሁንም «ሰሚ አጥተዋል» ሲሉ የምክር ቤት አባላትና የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ።

Äthiopien | Binnenvertriebene aus Tigray
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«ወደ አካባቢዎቹ እርዳታ አይደርስም»

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ የሁለት ወረዳ ነዋሪዎች አሁንም «ሰሚ አጥተዋል» ሲሉ የምክር ቤት አባላትና የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ። በፌደራል መንግሥት የተያዘው የሰላም ሂደት በቅርቡ ተጠናቅቆ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንደሚመለሱ፣ በህወሓት የተያዙ አካባቢዎችም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነፃ እንደሚሆኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እየገለጸ ነው።
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ የሁለት ወረዳ አስተዳደሮች አሁንም በህወሓት ቁጥጥር ስር ቢሆኑም ከየትኛውም አካል እርዳታ እንማይደርሳቸውና ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የሰጡት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የዝቋላ ምርጫ ክልል ተወካይ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ኪዴ ጓዴ የሰላም ስምምነቱ የሁለቱን ወረዳ ነዋሪዎች እንደ ሌሎች አካባቢዎች በእኩለነት አልተመለከተም የሚል ቅሬታ አላቸው።

«ሁለቱን ዓመት አገራዊ ጉዳይ ስለሆነ ተሸክመነዋል፣ … ነገር ግን የሰላም ስምምነቱ አገራዊ ጉዳይ መሆን አለበት፣ ለሁሉም ህዝቦች ደግሞ እኩል ነው መሆን መቻል ያለበት፣ እስካሁን ግን እነኚህ ሁለት ወረዳዎች ከእርዳታ፣ ከድጋፍ፣ ከልማትና ከተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች፣ አገልግሎቶች ውጪ ናቸው። ታፍነው ነው ያሉት፣ በእናቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለምሳሌ ማንሳት ይቻላል፣ በመንግሥት በኩልም በእነርሱ (ሕወሓት) በኩልም መረጃ የሚሰጥ የለም፣ በቅርብ ጊዜ በየቤታቸው ሞተው ያልተቆጠሩትን ሳይጨምር፣ 15 እናቶች ከተገላገሉ በኋላ፣ አምስት እናቶች ደግሞ ከነጨቅላ ልጆቻቸው ጋር ፃግብጂ ወረዳ ብቻ የሞቱ ናቸው፣ ይህ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክር ቤትም ተረጋግጧል።» ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪካዊ ሂደቶች ሁሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ «ሰሚ አጥቷል» ሲሉም አቶ ኪዴ ወቅሰዋል። 
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ስቡህ ገበያው በበኩላቸው የአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች በህወሓት ቁጥጥር ስር በመሆናቸው ያሉበትን ደረጃ እንኳ ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት መፍትሔ እንዲያመጣ ነው የጠየቁት።
«በሁለቱ ወረዳ ውስጥ ያሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች የጤና፣ የትምህርት፣ የመሰረተ ልማት፣ የውኃ፣ አገልግሎቶች የሉትም፣ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ገብቶ ማረጋገጥም አልተቻለም፣ ምክንያቱም እስካሁን ድረስ ህወሓት ነው በአካባቢው ያለው፣ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ብቻ ነው የምናውቀው፣ ስለሆነም መንግሥት በአስቸኳይ አካባቢውን ከጠላት ነፃ ማድረግ አለበት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ገብተው ማነኛውንም ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፣ በሰቆጣና አካባቢው ተፈናቅሎ የሚገኘው ህዝብም ወደ ቀየው መመለስ አለበት።»
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የምንመራውን ህዝብ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ሳናውቅ «መምራትም ከብዶናል» ነው ያሉት።

«(የሁለቱ ወረዳ ነዋሪዎች) አሁን ባሉበት ሁኔታ የሞራልም፣ የቁሳቁስም፣ የሰብዓዊ ችግርም ተጭኗቸው፣ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፤ መንግስት በአስቸኳይ መፍትሔ መስጠት አለበት ኅብረተሰቡ ተጎድቷል። እኛ መሪዎችም ወንበር ላይ ተቀምጠን ይህ ህዝብ ተፈናቅሎ፣ እዛም ያለው (አበርገሌና ፃግብጂ) ህዝባችን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በማናውቅበት ሁኔታ «መሪ ነን» ለማለት ይከብደናል።» የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሰሞኑን በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ እንዳሉት በህወሓት ቁጥጥር ስር ያሉ ወረዳዎችን በሰላሙ ስምምነት መሰረት ለመፍታት የፌደራሉ መንግሥት እየሠራ እንደሆነ በማመልከት፤ በቅርብ አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላም እንደሚመለስም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ67 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በብሔረሰብ አስተዳደሩ ሦስት የመጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከ60ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ በህወሓት ስር ባሉት በእነዚሁ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛሉ።
ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW