1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዋግሕምራ ነጻ የወጡ ቀበሌዎችና የወደሙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት

ሰኞ፣ መስከረም 9 2015

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለ9 ወራት በህወሓት ስር የነበሩ 6 የዝቋላ ወረዳ ቀበሌዎች ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ ጥምር ኃሎች ነፃ መውጣታቸውን የዝቋላ ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል ። በወረዳው የጤናና የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው ሥራ ለመጀመር መቸገራቸውን ደግሞ የየዘርፉ ኃላፊዎች አመልክተዋል፡፡

Äthiopien | Teile der Amhara-Region nun unter Kontrolle der Regierung
ምስል Waghemra Communication office

የዋግህምራ ዞን ቀበሌዎች የማህበራዊ አገልግሎት ማስጀመር ተግዳሮት ፈጥሯል

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለ9 ወራት በህወሓት ስር የነበሩ 6 የዝቋላ ወረዳ ቀበሌዎች ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ ጥምር ኃሎች ነፃ መውጣታቸውን የዝቋላ ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል ። በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ በታጣቂው ስር የነበሩ ሌሎች ቀበሌዎችም በመንግስት ቁጥጥር ስር መግባታቸውን ብሔረሰብ አስተዳደሩ ገልጧል ። የጤናና የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው ሥራ ለመጀመር መቸገራቸውን ደግሞ  የየዘርፉ ኃላፊዎች አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል፣ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ ወረዳዎች ካለፉት 9 ወራት ጀምሮ በህወሓት ስር ቆተዋል፣ በታጣቂው ስር የነበሩ የዝቋላ ወረዳ ቀበሌዎች ሰሞኑን በተወሰዱ ውጊያዎች በኢትዮጵያ ጥምር ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዝቋላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታፈረ ሚሰን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡

“ ዝቋላ ወረዳ ላይ 6ቱ ቀበሌዎች ራስ ገነት፣ ደብረ ዓባይ፣ ደብረ ሰማይ፣ ደብረ ሰላም፣ ደብረ ህይወትና ሰሜን በር ያው በጠላት ለብዙ ወራት ማለት ነው የቆዩበት ሁኔታ ነው የነበረው፣ መስከረም 1 አካባቢ ጀምሮ ጦርነት ሲካሄድ ነው የነበረው፣ ከዚያ በኋላ ምሽጉን ለቅቀው ወጥተዋል፣ በጣም የሚያስገርም ምሽግ ነው ያለው እዛ ላይ… ያንን ምሽግ ለቅቀው ወጥተዋል፣ ስድስቱነ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ፣ ከዚያ በኋላ ያገኘነው ትምህርት ቤቶች ላይ ንብረት የምትባል አንዲትም ነገር የለችም ጣራውን ሁሉ ቆርቆሮውን ሁሉ ስብስብ አድርጎ ተቋማትን የጤና ጣቢያዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን ሁሉንም ገንጥሎ ምሽግ ሲሰራ ነው የከረመው፡፡”

ምስል Waghemra Communication office

የብሔረሰብ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ በበኩላቸው ህወሓት በዝቋላ 6 ቀበሌዎች በቆየበት ወቅት በማህበራዊ መስጫ ተቋማት ላይ ውድመት ማድረሱን አመልክተዋል፡፡የትምህርትና የጤና ተቋማት ውድመት ደርሶባቸዋል፣ የተገልጋዮችን ስነ ልቦና የሚጎዱ ፅሁፎችም በየተቋማቱ ግድግዳዎች ላይ መፃፋቸን አብራርተዋል፡፡

እንደመምሪያ ኃላፊው ህወሓት ቀደም ይዟቸው ከነበሩት የብሔረሰብ አስተዳደሩ አካባቢዎች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ቦዎችን በመቆጣጠር በዝቋላ ወረዳ 6 ቀበሌዎችን ለ 9 ወራት ተቆጣጥሮ ቆይቷ ብለዋል፡፡ በቆይታቸውም የመንግስትና የግል ንብረቶችን ማውደማቸውን አቶ ከፍያለው አመልክተዋል፡፡

በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ህወሓት በሰቆጣ ወረዳ በሚገኙ ብርብር ጊዮርጊስ፣ ሐሙሲት፣ ወለህ ማሪያም፣ ጢያ፣ ዘርጣ በተባሉ ቀበሌዎች ጥቃት በማድረስ ተመሳሳይ የተቋማት ውድመት ማድረሱንም አቶ ከፍያለው ገልጠዋል፡፡

“ አጠቃላይ ለሶስተኛ ዙር በመጣበት ጊዜ የወደሙ ትምህርት ቤቶች 50 ናቸው፣ ያወደማቸው ጤና ተቋማት ደግሞ 5 ጤና ጣቢያዎችና 15 ጤና ኬላዎች ናቸው፣ ያኔ ከዚህ በፊት ያወደመውን አይጨምርም፡፡” ሲሉ አስረድተዋል አቶ ከፍያለው፡፡

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ኪዳት አየለ በዝቋላ ወረዳና በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ  ጤና ጣቢያዎችና  ጤና ኬላዎች ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው ጠቁመው፣ መሰረታዊ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን ባልተሟላ መልኩም ቢሆን እንዲጀመሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ምስል Waghemra Communication office

ዶ/ር ኪዳት “ … መሰረታዊ የሚባሉትን የወሊድና የድንገተኛ የህክምና አገልግሎቶች ጊዜ ሳይሰጥ መጀመር ስላለባቸው እንደዚያ ነው እያደርግን ያለነው አሁን ላይ ሁሉም ጤና ጣቢያዎች ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መጀመር ባይችሉም መሰረታዊ የሚባሉትን የድንገተኛ ህክምናና የወሊድ አገልግሎት እንዲጀምሩ አድርገናል፣ ባለው አቅም ማለት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የዝቋላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታፈረ ሚሰን እንደሚሉት በወረዳው ስድስቱ ቀበሌዎች የትምህርትና የጤና ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ በመሆኑ ተማሪዎችን በዛፍ ስር ቢሆንም ለማስተማር ምዝገባ እየተካሄደ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ አስረድተዋል፡፡

“ … ንብረት እየተመዘገበ ነው ያለ በየትምህርት ቤቱ የጠፋ ንብረትና የወደመ ንብረት፣ ተማሪ ምዝገባ እየተካሄደ ነው ያለው ያው ዛፍ ስር ቢሆንም መጀመር አለብን … ወንበር የለም መጽሐፍ የለም መማሪያ መጽሐፍ ካገኘንና ቦርድ ካገኘን ድንጋይ ላይ ቢሆንም ተቀምጠው እየተማሩ ከዚያ በኋላ ግብዓት ብለን ነው እንቅስቃሴ እደረግን ያለነው፡፡ ”

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጂና አበርገሌ የተባሉ ወረዳዎች አሁንም በህወሓት ስር እንደሚገኙ የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የዞኑና የየወረዳ ባለስልጣናት መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና የዞኑ ተወላጅ ዲያስፖራዎችና መላ ኢትዮጵያውያን የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW