በዋግኸምራ አበርገሌ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ህፃናት እየሞቱ ነው
ሰኞ፣ ግንቦት 15 2014በአማራ ክልል ዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ለጊዜው ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ የህፃናት ህይወት እያለፈ ነው ሲል የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ። ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአማራ ክልል ጤና ቢሮና የአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት አንዱ ሌላውን ይመለከተዋል የሚል ምላሽ ሰትተዋል፡፡ የአበር ገሌ ወረዳ በህወሓት ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዱ ሲሆን የተወሰነው የወረዳው ህዝብ ተፈናቅሎ በሰቆጣ አካባቢ ሲኖር ቀሪው ደግሞ ቀየውን ሳይለቅ በዛው እንደሚኖር የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አመልክቷል፡፡
ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ የሚገኙት የአበርገሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓለሙ ክፍሌ ከአካባቢው በተለያዩ መንገዶች ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ጠቁመው ከግንቦት 7/2014 ዓም ጀምሮ ምንነቱ በውል ያልታወቀ በሽታ ተከስቶ 9 ህፃናትን እገሏል፣ በሽታው አሁንም እየተስፋፋ ነው ብለዋል፡፡
አበርገሌ ወረዳ በህወሓት ቁጥጥር ስር ቢሆንም እንደሌሎቹ አካባቢዎች ምግብና መድኃኒት እየቀረበለት ባለመሆኑ በበሽታና በርሀብ ሰዎች ህይወታቸው እያለፈ እንደሆነ የብሔረሰብ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ተናግረዋል፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ኪዳት አየለ ወደ ወረዳው ባለሙያ መላክ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው በወረዳው እየተፈጠሩ ያሉ የጤና ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁትና መፍትሔ እንዲፈለግ ለክልሉ ጤና ቢሮ ደብዳቤ መፃፋቸውን ለዶቼ ቬሌ አስረድተዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ስቡህ ገበያው በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች ወደ ቦታው ተንቀሳቅሰው በሽታውን የሚቆጣጠሩበት መንገድ እንዲፈለግ ለክልሉ ጤና ቢሮ በደብዳቤ እንደተገለፀለት ገልጠዋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት ተረባርበው ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች ወደ ቦታው የሚደርሱበት ሁኔታ ሳይውል ሳያድር እንዲደርሱ ያሳሰቡት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ያ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የጤና ቀውስ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊና የአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጉዳዩ አንዱ ሌላውን እንደሚመለከት ምላሽ በመስጠታቸው በክልሉ በኩል ተከስቷል በተባለው በሽታ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማካተት አልተቻለም፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ