1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተው ድርቅና ያስከተለው ጉዳት

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2016

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሳህላ ወረዳ በተከሰተ ድርቅ ሰዎችና እንስሳት እየሞቱ መሆናቸውን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣናት አመለከቱ። ድርቁን የከፋ ያደረገው ባሳለፍነው የዝናብ ወቅት በአካባቢው ዝናብ ባለመጣሉ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ፎቶ ከማኅደር፤ ከአራት ዓመት በፊት በድርቅ የተጎዳው የዋግኽምራ ዞን
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለድርቅ ከተጋለጠ መሰንበቱን፤ በክረምቱ ወቅትም ዝናብ እንዳልነበረ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ ከአራት ዓመት በፊት በድርቅ የተጎዳው የዋግኽምራ ዞን ምስል DW/A. Mekonnen

ድርቅ በዋግኽምራ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሳህላ ወረዳ በተከሰተ ድርቅ ሰዎችና እንስሳት እየሞቱ መሆናቸውን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣናት አመለከቱ። ድርቁን የከፋ ያደረገው ባሳለፍነው የዝናብ ወቅት በአካባቢው ዝናብ ባለመጣሉ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

በሳህላ ወረዳ የመሻህ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ነጋሽ ጎበዙ በተከሰተው ድርቅ ከ15 በላይ እንስሳት እንደሞተባቸው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል። ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተክሊት እንደሰሻው በበኩላቸው በርካታ እንስሳት በመኖ እጥረት እየሞቱ በመሆኑ የሚመለከተው አካል እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል፣ እርሳቸውም ከነበሯቸው እንስሳት መካከል ከፊሉ በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን በመጥቀስ።

የሳህላ ወረዳ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀን መለሰ 95 ከመቶ የወረዳው እንስሳት ሀብት እጅግ ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን ጠቁመው በድርቁ ምክንያት እስካሁን 2,700 እንስሳት መሞታቸውን አረጋግጠዋል። የወረዳው አደጋ መከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ባለሙያ አቶ አዲሴ ደመቀ በበኩላቸው ድርቁ እየከፋ መሄዱን አመልክተው እስካሁን በርሀብ ምክንያት hሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዋግኽምራ ሀገረ ስብከት ግማሽ ሚሊዮን ብር ርዳታ መድረሱን በማመልከትም፤ የመንግሥት ርዳታ ግን ከተቋረጠ ግን ወራት ማለፋቸውን አስረድተዋል።

ከሳህላ ወረዳ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ 95 ከመቶ የወረዳው እንስሳት ሀብት እጅግ ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን ያመለክታል። ፎቶ ከማኅደር፤ በጉጂ ዞን እንስሳትን የጎዳው ድርቅምስል DW

ዋግኽምራብሔረሰብ አስተዳደር ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ በአካባቢው ድርቅ መከሰቱን በአካል ጭምር ሄደው ማረጋገጣቸውን፣ እንስሳት መሞታቸውንና የሰው ሕይወት ማለፉን ደግሞ ከወረዳው እንደተረዱ ተናግረዋል። ችግሩን ለክልሉም ሆነ ለእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቢያሳውቁም እስካሁን ተግባራዊ ምላሽ ከየትኛውም አካል አልተገኘም ብለዋል። ከአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለኃላፊው በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW