በውጭ የሚገኙ 21 ድርጅቶች ስለ ወልቃይትና አካባቢው
ሐሙስ፣ ጥር 4 2015
የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራ እና ራያ ጉዳይ የፍትህ እና የማንነት ጥያቄ ነው ሲሉ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማኀበራት ዐስታወቁ። በአሜሪካ፣ በአውሮፖና በአውስትራሊያ የሚገኙ 21 ማኀበራት፣ በጋራ ባወጡት መግለጫ ለአካባቢዎቹ የማንነት ጥያቄ የሚመጥን ፍትሃዊ መፍትሄ ማስተጋባት፣አካባቢውን መልሶ ማቋቋም፣ የተጎዱትን እንዲያገግሙ መርዳትና አስፈላጊውን የባጀት ድጋፍ መስጠት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኾናቸው ገልጸዋል። ማኀበራቱ ይኽንኑ መግለጫቸውን፣ለኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ለሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ማስገባታቸውን አመልክተዋል።
እነዚሁ በአሜሪካ፣ በአውሮፖና አውስትራሊያ ከሚገኙ ማኀበራት መኻከል፣ የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ሲቪክ ማኀበር፣ የኢትዮጵያውያን ምሁራን ኔትወርክ፣ ራዕይ ለኢትዮጵያና ዐድዋ ታላቁ የአፍሪቃ ድል ማኀበር ይገኙባቸዋል። ማኀበራቱ ለዶይቸ ቬለ(DW)የላኩት መግለጫ እንዳመለከተው፣ በወልቃይትና አካባቢው ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማካኼድ የጋራ አቋም ላይ ደርሰዋል።
የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራና ራያ ጉዳይ የፍትህና የማንነት ጥያቄ ነው የሚለውን ይህንኑ አቋማቸውን፣ የኢትዮጵያ፣የአፍሪቃና የዓለም ሕዝብ እንዲያውቁትም እንፈልጋለን ብለዋል። ዶክተር ሺፈራው ገሠሠ የድርጅቶቹ ተወካይ ናቸው። «እንግዲህ የወጣው መግለጫ፣የወልቃይት፣ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራና ራያ ጉዳይ የማንነትና የፍትህ ጥያቄ ነው በሚል ርዕስ ነው። ይኽንን መግለጫ ያወጡት፣ ሃያ የሲቪክ ድርጅቶችና የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራ የዐማራ ዓለም አቀፍ አንድነት ማኀበር በጋራ በመሆን በጠቅላላው 21 ድርጅቶች ናቸው። መግለጫው ለኢትዮጵያ የፌዴራል ዋና ዋና አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ እንዲኹም ለዐማራ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር እንዲደርስ ተደርጓል።»
ማኀበራቱ በአስቸኳይ መተግበር አለባቸው ብለው በመግለጫቸው ላይ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች ውስጥ፣የአካባቢው ነዋሪዎችን የዐማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ያለምንም ገደብ፣ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። እንዲኹም ለእነዚህ አካባቢዎች ሊሰጥ የሚገባው የበጀት ፈሰስ ባስቸኳይ እንዲመደብ ጠይቀዋል። የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሰቲት ሁመራ የዐማራ ዓለም አቀፍ አንድነት ማኀበር ሰብሳቢ አቶ በሪሁን ጥሩ፣ የአካባቢው ሕዝብ ሊሟላለት ይገባዋል ያሏቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ያነሳሉ።
«ሁለት ዓመት ሙሉ፣ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት የሌለው፣የፍትህ ተቋማት የሌሉት፣ሁለት ዓመት ሙሉ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው።ሁለት ዓመት ሙሉ ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር፣ከራሱ በፊት የሃገሬ ችግር ይበልጣል፤ስለዚህ ሃገሪቱ ችግር ላይ ነው ያለችው፣ጦርነት ነው ያለችበት ስለዚኽ ጦርነቱ ይቀድማል ብሎ አንገቱን ደፍቶ ነው ጦርነቱን ደግፎ ሲታገል የቆየው ማለት ነው።ስለዚኽ ይኽ አሁን ማንነቱ ከተረጋገጠ፣ሰላም ከኾነ፣ሃገሪቱ ወደ ሰላም አቅጣጫ ከኼደች በጀት ሊፈቀድለት ይገባል።»
የወልቃይትና አካባቢውን ጉዳይ፣በህገ መንግስቱ መሰረት በሕዝበ ውሳኔ ለመፍታት በመንግስት እየቀረበ ያለውን የውሳኔ ዐሳብ አስመልክቶ አቶ በሪሁን ሲመልሱም እንዲህ ብለዋል። «ሕዝበ ውሳኔ የሚባለው ነገር፣በወልቃይት ውስጥ ሌላ ሕዝብ የጠየቀ የለም።እኔ ትግሬ ነኝ ብሎ የጠየቀ ሰው የለም።ሕዝበ ውሳኔ የዜጎችን መብት ሊያረጋግጥ ይችላል፤ጠያቂ በሌለበት ግን ይህ ምክንያታዊ ሊደረግ አይችልም።» ማኀበራቱ በተከታታይ የሚያወጧቸው መግለጫዎች ግብ፣የሕዝቡን ጥያቄ ማሰማትና ለችግሮቹ ምን መደረግ እንዳለበት፣ የመፍትሔ ዐሳቦችን ማመላከት መሆኑን ዶክተር ሺፈራው ጠቁመዋል።
«ጥያቄው እንዲቀርብ ማድረግ ነው በተደራጀ መንገድ።ውጭ ያለውም ሕዝብ ይኽን ድጋፍ ሰጥቶ በተደራጀ መልኩ በጥያቄው ዙሪያ እንዲሰለፍ ነው።ሃገር ቤት ያለውም አለኝታ አለን እንዲል ነው።እንደገና ደግሞ ለመንግስት ሕዝቡ ምን ያስባል? የሕዝቡ ነጸብራቅ የኾነው በውጭ የሚኖረው የኢትዮጵያ አደረጃጀት የሚሰሩ ሲቪክ ማኀበራት ኹሉ አሉ በዚኽ በ21 ዱ ውስጥ፤ እና ምን ያስባል? ምን መኾን ነው ያለበት የሚለውን ነው እንግዲህ አጽንኦት ሰጥተን የምናስተላልፈው።እና ይኼ እንግዲህ ዋና መስመሩ፣ሕዝቡን ያነቃል፣ ያደራጃል፣አለኝታነትን ያሳያል፣ጥያቄዎችን አንጥሮ ያወጣል፣ምንድነው መጠየቅ ያለበት የሚለውን ነገር በአስተማሪነቱና በቀስቃሽነቱ ይረዳል መግለጫው።»
ከመግለጫዎቹ ባሻገር፣ ማኀበራቱ ሌሎች ተጨባጭ ያሏቸውን ርምጃዎችን በቀጣይ የሚወስዱ መኾናቸውንም ተወካዩ ጠቁመዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ