በዚምባብዌ ተቃዋሚዎች ዳግም ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ አስተላለፉ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23 2015
በዚምባብዌ ባለፈው ረቡዕ ተካሂዶ ገዢው ፓርቲ ያሸነፈበት የምክር ቤትና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዳግም እንዲካሄድ ተቃዋሚዎች ጠየቁ ። ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫው ሰላማዊ ቢሆንም ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርቶችን ያሏሟላ እንደነበር ግን አልሸሸጉም ። በምርጫው አሸናፊ ናቸው የተባሉት በስልጣን ላይ ያሉት ኤመርሰን ምናንጋግዋንና ፓርቲያቸው ዛኑ ፒኤፍ ናቸው ። የዜጎች ጥምረት ለለውጥ (CCC) የተሰኘው የዚምባብዌ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ተችበርብሯል ያለው ምርጫ ዳግም እንዲካሄድ ዛሬ ጥሪ አስተላልፏል ።
በዚምባብዌ ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው የምክርቤትና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፤ በስልጣን ላይ ያሉት ኤመርሰን ምናንጋግዋንና ፓርቲያቸው ዛኑ ፒኤፍ አሸናፊዎች ሁነዋል። የዝምባብዌ የምርጫ ኮሚሺን ፕሬዝደንት ፕሪሲላ ማካንያራ ችጉምባ የምርጫውን ውጤት ይፋ ባደደረጉበት መግለጫቸው ፕረዝዳንት ምንጋግዋ ከመራጩ ህዝብ 52.6 ከመቶ በማግኘት ውድድሩን ያሸነፉ መሆኑን ገልጸዋል። “ እኔ የዝምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ፕሪሲላ ማካንያራ ቺጉምባ የዛኑ ፒ ኤፍ መሪ ምንጋግግዋ ኤሜርሰን በ2023 ምርጫ የዚምባብዌ ሪፑብሊክ ፕሬዝዳነት ሁነው የተመረጡ መሆኑን አስታውቃለሁ በማለት የምርጫውን ውጤት አብስረዋል።
የ80 ዓመቱ አዛውንት ተመራጭ ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ውድድሩን በማሸናፋቸው የተደሰቱ መሆኑን ገልጸው፤ ምርጫው ግልጽና ተአማኒ የነበረ ቢሆንም በውጤቱ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች፤ የትና እንዴት ቅሬታቸውን ማቅረብ እንዳለባቸው አስታውሰዋል።
የተቃዋሚው መሪ ኔልሰን ቻሚሳ ግን ምርጫው የተጭበረበርና ግልጽነት የጎደለው ነበር በማለት የማይቀበሉት መሆኑን ነው የተናገሩትና የአካባቢ አገሮችና አለማቀፉ ማህብረሰብ ከጎናቸው እንዲቆሙ የጠየቁት። በዝምባብዌ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ችግር ያለ መሆኑን በመጥቀስም፤ መሰረታዊ ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር ከችግር አዙሪት መውጣት እንደማይችል አስታውቀውል ። “ ምርጫ ሰላማዊ፣ ታአሚኒና ህጋዊ መሆን ያለበት ቢሆንም እዚህ የሚደረገው ምርጫ ግን ማስፈራራት የተሞላበት ነው” በማለት ይህ የሰለጠነ አካሂድ አይደለም፤ መለወጥም አለበት ሲሉም ተሰምተዋል።
በምርጫው፤ የካርተር ማዕከል፤ የአውሮፓ ህብረትና የደቡብዊ አፍሪካ አገሮች የልማት ትብብር (ሳዴክ) የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች፤ ተጋብዘው ሂደቱን ታዝበዋል ። ሁሉም ግን ባወጧቸው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች፤ ምርጫው ሰላማዊ የነበር ከመሆኑ ውጭ፤ የነጻ፤ ዴሞክርሲያዊና ተአማኒ ምርጫ መስፈርቶችን እንደማያሟላ ነው የገለጹት። የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ሚስተር ካስታልዶ የመጀመሪያ ደርጃ ሪፖርታቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት “ ምርጫው መሰረታዊ የሆኑት እኩልነት፣ ወጥነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ጉድለቶች የታዩበትና ከአካባቢና አለማቀፍ የምርጫ ደረጃ ዝቅ ያለ ነውም” ብለዋል።
የካርተር ማዕከል የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ፕሮፊሰር አታላሂሩ ሙሃማዱ ጄጋ በብኩላቸው፤ “ የካርተር ማእክል የ2023 የዝምባብዌ ምርጫ የተካሄደው በጥብቅ የህግ ማዕቀፍና የምርጫ ኮሚሽኑም ነጻና ግልጽ ባላሆነበት ድባብ ነው” በማለት ምርጫው የነበረበትን ጉድለት አብራርተዋል ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚስተር ትናንት ባወጣው መገለጫም፤ የዝምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን ውጤቱን የገለጸ ቢሆንም፤ ምርጫውን የታዘቡ በርካታ ወገኖች ግን መሰረታዊ የምርጫ መስፈርቶችን ያላሟላ እንደንበር አስታውቀዋል በማለት፤ ጉዳዩን እየተከታተለው መሆኑን ገልጿል። የፖlለቲካ ተንታኞችም የምርጫ ዘመቻውና ውድድሩ ለበርካታ አመታት በስልጣን ለቆየው ገገዥ ዛኑፒኤፍ ፓርቲ ያደላ እንድነበርና ይህም ለውጤቱ አስተዋጾ ሳያደርግ እንዳልቀረ ያምናሉ።፡
ምናንጋግዋወደ ስልጣን የመጡት ለ37 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩትን ሚስተር ሙጋቤን ተክተው የንበር መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ባለፈው ግዜ የተደረገውና እሳቸው አሸናፊ የሆኑበት ምርጫም እስክ ፍርድ ቤት የዘለቀ ውዝግብ የነበረበት ነበርበት። የአሁኑ ምርጫ ውዝግብም ቢያንስ ወደ ፍርድ ቤት ሳይደርስ እንደማይቀር ነው የሚታመነው። 17 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ዝምባብዌ በአለም፤ በገንዘብ ግሽበት፤ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ከሚጠቀሱት አገሮች ርታ ስትሆን፤ ከሰራተኛ ህዝቧም መደበኛ ስራ ያለው 25 ከመቶው እንደሆነ ነው የሚገለጸው።፡
ገበያው ንጉሤ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ