የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ በየመን ለሞቱ ኢትዮጵያውያን የሀዘን ቀን እንዲታወጅ ጠየቀ
ዓርብ፣ ነሐሴ 2 2017
ኮከስ ይህንን ጥሪ ያቀረበው ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍተዋል ያላቸው «ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ዜጎችን ለአደገኛ ስደትና አሰቃቂ እልቂት» እንደዳረጉ ሰሞኑን በየመን የባሕር ዳርቻ የሞቱትን ማሳያ በመጥቀስ ነው። የፓርቲዎች ስብስብ - ኮከስ የመሰል ችግሮች ሰለባ ናቸው ያላቸው"ወጣቶች" ለሀቀኛና ዘላቂ መፍትሔ እንዲነሱና ለትግል ከጎኑ እንዲቆሙ"፣ ለሞቱት ኢትዮጵያውያንም ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ ጠይቋል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ - ኮከሰ ሰሞኑን በየመን የባሕር ዳርቻ የሞቱት ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ «ከቁጥሩ በላይ አሳሳቢው መሠረታዊ ጉዳይ መንሥዔውና አስተማማኝ ዘላቂ መፍትሔው ነው» ብሏል።
ዜጎች በሀገራቸው ብሩህ ተስፋ እስካልታያቸው ድረስ መሰል «የመርዶ ዜናዎች ነገም የሚቀጥሉ ናቸው» ሲል በሀገር ውስጥ ያለው ችግር እንዲስተካከል መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል ሲልም ጠይቋል። የዚህ ስብስብ አባል ፓርቲ የሆነው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ።
«በሀገራቸው ዕድል ጨልሞባቸው፣ በጦርነት፣ በኢኮኖሚ ጫና፣ በድህነት የማይመረጡ ምርጫዎችን በመምረጣቸው ዜጎች ለእንደዚህ አይነት አደጋ ዜና መሆናችን የሚያሳዝን ነው።»
በተመሳሳይ ሰሞነኛ የስደት ጉዳይ ሰባት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሶማሊያ ወደ የመን ሲጓዙ የተሳፈሩበት ጀልባ ተበላሽቶ በረሃብ እና በውኃ ጥም መሞታቸውን የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ «ገጽታውን እየቀያየረ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው» ያለው «እልቂት እንዲገታ» ገዢውን ሥርዓት «በሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሕዝባዊ ትግል መቀየር የግድ ይላል» ብሏል። ለዚህ ወጣቱ ትውልድ «ለሀቀኛና ዘላቂ መፍትሔ እንዲነሳ» ሲል ለትግል ከጎኑ እንዲሆን ጠይቀቋል።
«ሕዝባዊ መንግሥት ያስፈልጋል። መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል። ኢ - ፍትሐዊነቶች ሥር የሠደዱ ናቸው። ሥርዓቱ ሕዝቡን አግልሎታል። ሕዝቡም ደግሞ ከፍርሃት ቆፈን ወጥቶ በሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ትግል መብቱን መጠየቅ አለበት።»
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለእነዚህ በጀልባ መገልበጥ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ኀዘኑን ገልጿል። ቅዱስ ሲኖዶሱ አክሎ በመሬት መንሸራተትና በድንገተኛ ጎርፍ፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ችግር እየገጠማቸው ለሚገኙ ወገኖች ሁሉም የሰው ልጆች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ደግሞ ለዚህ አደጋ ብሔራዊ የኀዘን ቀን እንዲታወጅ መጠየቁን የስብስቡ አባል ፓርቲ የሆነው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ ገልጸዋል። «ለእነዚህ ዜጎች መንግሥት የኀዘን ቀን ካላወጀ ሕዝብ በሙሉ ሲያልቅ ሊያውጅ ነው?» ሲሉ ጠይቀዋል።
ጦርነትን፣ ግጭትን፣ ሥራ ማጣትን ሽሽት፤ በሌላ በኩል የተሻለ ኑሮን ፍለጋ የሕገ ወጥ ስደትን የሚመርጡ ቀላል የማይባሉ ተጓዥ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የሞታቸው፣ የበረሃ ሲሳይ ሆነው የመቅረታቸው ዜና ያለማቋረጥ ይደመጣል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ