በዩክሬን መገኘት “ጠቃሚ” እንደሚሆን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ገለጹ
እሑድ፣ ነሐሴ 18 2017
ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ጦርነት ሲያበቃ የውጪ ሀገራት ወታደሮች በዩክሬን መገኘት “ጠቃሚ” እንደሚሆን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ገለጹ። የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ በበኩላቸው ሀገራቸው ለዩክሬን የደሕንነት ዋስና ለመስጠት ከጦርነቱ በኋላ ሀገራቸው ወታደሮቿን በኪየቭ ልታሠፍር እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
ሁለቱ መሪዎች ጉዳዩን ያነሱት ዛሬ እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካይኔይ ዩክሬንን ጎብኝተው ከፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ካናዳ ዩክሬንን የሚደግፈው የምራባውያን የበጎ ፈቃደኛ ሀገራት ጥምረት አካል ነች።
ዛሬ ብሔራዊ የነጻነት ቀኗን ያከበረችው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የገጠመችው ጦርነት ሲያበቃ ዋስትና የሚሆናት የደሕንነት ማረጋገጫ ከምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር በመሆን ለማበጀት ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ቀኑን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ዩክሬን ለነጻነቷ መዋጋት እንደምትቀጥል የገለጹት ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ሀገራቸው “ለሰላም ያቀረበችው ጥሪ አልተሰማም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ “ለዩክሬን ፍትኃዊ እና ዘላቂ ሰላም” ካናዳ የምታደርገውን ድጋፍ እያጠናከረች እንደምትገኝ አስታውቀዋል። የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ በበኩላቸው ዩክሬናውያን “ዛሬም ሆነ ወደፊት የነጻነት ቀናቸውን ሲያከብሩ ከጎናቸው ቆመናል” የሚል መልዕክት በኤክስ በኩል አስተላልፈዋል።
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮብ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የሀገራት ቡድን ለዩክሬን የደሕንነት ዋስትና ሊሰጥ እንደሚችል ለአሜሪካው ኤንቢሲ ቴሌቭዥን ጣቢያ ገልጸዋል። ይሁንና ለዩክሬን የደሕንነት ዋስትና የሚሰጠው ሀገር “ገለልተኛ፣ ከየትኛውም ወታደራዊ አሰላለፍ ያልወገነ እና የኑክሌር ጦር መሣሪያ ያልታጠቀ” መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ ለሦስት ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ የተዋጉት ሩሲያ እና ዩክሬን ዛሬ እሁድ እያንዳንዳቸው 146 የጦር ምርኮኛ ወታደሮች እንደተለዋወጡ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። ዩክሬን በባልቲክ ባሕር ኡስት ሉጋ ወደብ እና በቮልጋ ግዛት የሚገኙ ሁለት የተለያዩ የነዳጅ ማጣሪዎች ላይ ዛሬ እሁድ በድሮን ጥቃት መፈጸሟን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የዩክሬን ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ኦሌክሳንደር ሲርስኪ በዶኔትስክ ግዛት ሩሲያ ተቆጣጥራቸው የነበሩ ሦስት መንደሮችን ወታደሮቻቸው መልሰው እንደያዙ አስታውቀዋል።
እሸቴ በቀለ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር