1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብና ምዕራብ ትግራይ የነበሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ይፈርሳሉ ስለመባሉ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2015

ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የቀድሞው የትግራይ ምዕራባዊ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር በማፍረስ የተቋቋመው 'የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን' አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው የሚኒስቴሩ መልእክትን ለአንድ ክልል ወይም ለተወለዱበት አካባቢ ያጋደለ ብለውታል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይምስል DW/G. Tedla Haile Giorgis

በምዕራብና ደበብ ትግራይ የተመሰረቱ አስተዳደሮች ይፈርሳሉ

This browser does not support the audio element.

ጦርነቱ ተከትሎ በምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ከፌደራል ኃይሎች ውጭ የሆኑ ታጣቂዎች በአካባቢዎቹ እንዳይኖሩ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን መከላከያ ሚኒስቴሩ ገለፀ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ትላንት የአሸንዳ በዓልን አስመልክተው በይፋዊ የማሕበራዊ መገናኛ ገፃቸው ባሰራጩት መልእክት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ« በኃይል የተወሰዱ» ያሏቸውን አወዛጋቢ ግዛቶች "በሕገመንግስቱ መሰረት የሚመለሱበት ሁኔታ ለመፍጠር" እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። በመከላከያ ሚኒስቴሩ ዶክተር አብርሃም በላይ የትናንት መልእክት ዙርያ ለዶቼቬለ ምላሽ የሰጡት፥ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የቀድሞው የትግራይ ምዕራባዊ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር በማፍረስ የተቋቋመው 'የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን' አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው የሚኒስቴሩ መልእክትን ለአንድ ክልል ወይም ለተወለዱበት አካባቢ ያጋደለ ብለውታል። አቶ አሸተ አክለውም "የሚፈርስ መዋቅርም ሆነ፥ የሚፈታ ትጥቅ የለንም" ብለዋል።

ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ይመለሳሉ

ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ከሰላም ስምምነቱ በኃላም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት ጉዳት አላገገመም፣ ጥያቄዎቹ አልተመለሱም፣ የተፈናቀለው ወደቀዬው አልገባም ያሉ ሲሆን የህዝቡ ጥያቄዎችና ችግሮች ለመፍታት በቀጣይነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።  በተፈናቃዮች መጠልያ ያለው በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው ህዝብ "ለመስማት እና ለማየት በሚዘገንን" የችግር ሕይወት ላይ መሆኑ ያነሱት ዶክተር አብርሃም በላይ  ይህ ህዝብ መች ወደ ቀዬው ይመለሳል የሚል ደግሞ የሁሉም ጥያቄ መሆኑ አስታውቀዋል።

የፕሪቶሪያ ውል ተግባራዊነት

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ የተወሰዱ አወዛጋቢ የተባሉ ግዛቶች በሕገመንግስቱ መሰረት የሚመለሱበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል ።  የነበረውን ጦርነት ተጠቅሞ በኃይል በተያዙ አካባቢዎች የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ፣ ከፌደራል መንግስት ኃይሎች ውጭ ሌሎች ታጣቂዎች በአካባቢው እንዳይኖሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃላፊነት ወስዶ እየተገበረ መሆኑ ተጠቁሟል። 

ህዝቡ ዝግጁ ሲሆን ደግሞ በሕገመንግስቱ መሰረት በአካባቢዎቹ ህዝበ ውሳኔ የሚካሄድበት ሁኔታ እንደሚኖር ዶክተር አብርሃም በላይ ትናንት ባሰራጩት መልእክት ዐስታውቀዋል። "ከዚህ ውጭ ከሕግና ስርዓት ውጭ በጉልበት የሚንቀሳቀስ አካል" የፌደራሉ መንግስት ርምጃ እንደሚወስድበት መከላከያ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል። 

በመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ የትናንት መልእክት ዙርያ ለዶቼቬለ ምላሽ የሰጡት፥ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የቀድሞው የትግራይ ምዕራባዊ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር በማፍረስ የተቋቋመው 'የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን' አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው የሚኒስቴሩ መልእክት ለአንድ ክልል ወይም ለተወለዱበት አካባቢ ያጋደለ ብለውታል። 

ከጦርነቱ ጅማሮ በኋላ ጥያቄ በሚነሳበት አካባቢ የተቋቋመው አስተዳደር ይፈርሳል መባሉም አቶ አሸተ ደምለው ሲመልሱ "የሚፈርስ መዋቅርም ሆነ የሚፈታ ትጥቅ የለንም" ብለዋል። 

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት የተፈናቀሉ ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፥ ችግሮች በሕገመንግስታዊ መንገድ እንዲፈቱ እንደሚጠብቅ ይገልፃል። የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም "የአማራ ታጣቂዎች እና የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ እንዲወጡ ከፌደራል መንግስት እንጠብቃለን" ሲሉ ለዶቼቨለ ገልጸዋል።

ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር
ማንተጋፍቶት ስለሺ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW