በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በጋምቤላ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2017
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በጋምቤላ ክልል አዋሳኝ ሥፍራዎች ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት ሦስት የፀጥታ አባላትን ጨምሮ አሥር ሰዎች ተገደሉ ፡፡ ግጭቱ ሊቀሰቀስ የቻለው ከወርቅ ምርት ቁፋሮ ጋር ተያያዞ የተነሳውን አለመግባባት ተከትሎ መሆኑን የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ በሁለቱ ክልሎች የወረዳ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ለግጭቱ መነሾ እንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው ፡፡
10 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በጋምቤላ ክልል አዋሳኝ ሥፍራዎች ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት ሦስት የፀጥታ አባላትን ጨምሮ 10 ሰዎች ተገደሉ ፡፡ ግጭቱ ሊቀሰቀስ የቻለው ከወርቅ ምርት ቁፋሮ ጋር ተያያዞ የተነሳውን አለመግባባት ተከትሎ መሆኑን የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ግድያው በሲቪል ነዋሪዎች እና በፀጥታ አባላቱ ላይ የተፈጸመው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ ሲያል ተባለ ቀበሌ ውስጥ ነው ፡፡
የጋምቤላ ክልል ከ40 ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አስገባ
የጥቃቱ መነሻ
ጥቃት አድራሾቹ ከአጎራበች የጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ የተነሱ ናቸው ሲሉ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የቀበሌው ነዋሪ “ ጥቃት አድራሾቹ ትናንት ሰኞ ተደራጅተው ነው ወደ ቀበሌው የመጡት ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ከጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ መጁጅ ቀበሌ ተነስተው ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤሮ ወረዳ ሲያል ቀበሌ ገብተው ተይዘዋል ከተባሉ አምስት ሰዎች ጋር የተያያዘ ነው ፡፡ ሰዎቹ ድንበር ተሻግረው ወርቅ ሲቆፍሩ ተይዘዋል ነው የተባለው ፡፡ ቆፋሪዎቹ ለምን ይያዛሉ በሚል የተሰባሰቡ ሰዎች ወደ ቀበሌው በመግባት በከፈቱት ተኩስ ሰባት ሲቪሎች እና ሦስት የፀጥታ አባለት ተገድለዋል ፡፡ ሌሎች ስድስት ሰዎችም በጥይት ቆስለዋል “ ብለዋል ፡፡
የሙርሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ
የሁለቱ ወረዳ ባለሥልጣናት ምን ይላሉ ?
በምዕራበ ኦሞ ዞን የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ክይዳዲ በወረዳው ጥቃት መድረሱንና አሥር ሰዎች መሞቸውን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ የጥቃቱ መነሻ ፖሊስ ወሰን ተሻግረው በወርቅ ቁፋሪ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለምን ይይዛል በሚል ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ በህግ ሥር የዋሉ ሰዎች ምርመራ ተደርጎ እንደሚለቀቁ በአጎራባች ዲማ ወረዳ ራሳቸውን ላደራጁ ቡድኖች ቢነገራቸውም አልሰማ ብለው ውጊያ ከፈቱብን ብለዋል ፡፡
ዶቼ ቬለ ድንበር ተሻግረው የወርቅ ቁፋሮ አድርገዋል ፣ ለጥቃት አድራሾችም መነሻ ሆኗል የተባለውን በጋምቤላ ክልል የዲማ ወረዳ ሃላፊዎችን አነጋግሯል ፡፡ የወረዳው መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኡመድ ኦቶ ግን “ ወርቅ አምራቾቹ የቆፈሩት በራሳቸው የመጁጅ ቀበሌ እንጂ ወደ ቤሮ ወረዳ ሲያል ቀበሌ አልተሻገሩም ፣ ጥቃት አድራሾም ቢሆኑ እነሱ ራሳቸው ናቸው “ ብለዋል ፡፡
በጋምቤላ አምስት ስደተኞች ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ክልሉ ፖሊስ አስታወቀ
አሁን አካባቢው በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?
ሁለቱ ወረዳዎች ለግጭቱ እንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ናቸው ቢሉም አሁን ላይ አካባቢው ተረጋግቷል ወይ ? በግጭቱ ተደናግጠው የሸሹ ነዋሪዎችስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ሲል ዶቼ ቬለ የጠየቃቸው የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ክይዳዲ “ አሁን ወደ አካባባው የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት ገብቷል ፡፡ በእኛ በኩል የወደቁ አስክሬኖችን ሰብስበን እየቀበርን እንገኛለን ፡፡ የተወሰኔ የቀበሌው ነዋሪዎችም ተደናግጠው ከሸሹበት እየተመለሱ ይገኛሉ ፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ሰለም መሆኑን እያዩ ሁሉም ሊመለሱ ይችላሉ ብልን እንጠብቃለን “ብለዋል ፡፡
ፎቶ መግለጫ ፡ በቤሮ እና በዲማ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ባህላዊ የወርቅ ማውጫ ሥፍራዎች
ፎቶ ከዲማ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የተወሰደ
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ