1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የወባ በሽታ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2017

በአሁኑ ጊዜ የበሽታው ሥርጭት ምጣኔ 61 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ሃላፊው አሃዛዊ መረጃዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል ቀደምሲል ጀምሮ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የጠቀሱት ሃላፊው እንደክልል በ870 ሺህ 390 ካሬ ሜትር ላይ የወባ ትንኝ ማራቢያ የሆነ ያቆረ ውሃን የማፋሰስ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል ፡፡

Äthiopien | Bewohner reinigen Gräben zur Malaria-Prävention
ምስል፦ Southwest Ethiopia Peoples Regional State health bureau

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የወባ በሽታ

This browser does not support the audio element.

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እየጨመረ በመጣውየወባ በሽታ ሰዎች ለህመምና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ ፡፡ ዶቼ ቬለ በዞኑ ቤንች ሸኮ ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ኮንታ ዞኖች ስለበሽታው ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የበሽታውን እየሰፋ መምጣት ገልጸዋል ፡፡

የወባ በሽታ ታማሚ ከነበሩት መካከል አንዱ መሆናቸውን የጠቀሱት በቤንች ሸኮ ዞን የማጂ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ተካ ኦሪስ “ ከእኔ በተጨማሪ ሌሎች የቤተሰብ አባላቶቼ በበሽታው ተይዘዋል ፡፡ ሆስፒታሎችም በሽተኞች በመሞላታቸው ተኝቶ ለመታከም አልጋ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ፡፡ በዚህ ሳምንት ብቻ  በበሽታው የሞቱ ሰዎች አሉ “ ብለዋል ፡፡

ለበሽታው ሥርጭት መስፋት መንስኤው ምንድ ነው ?

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የበሽታው ሥርጭት የመስፋት አዝማሚያ እያሳየ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የበሽታው ሥርጭት ምጣኔ 61 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ሃላፊው አሃዛዊ መረጃዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል ፡፡

በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል ቀደምሲል ጀምሮ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የጠቀሱት ሃላፊው እንደክልል በ870 ሺህ 390 ካሬ ሜትር ላይ የወባትንኝ ማራቢያ የሆነ ያቆረ ውሃን የማፋሰስ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል ፡፡

በተጨማሪም 351 ሺህ 663 የአልጋ አጎበር መሠራጨቱን የተናገሩት ሃላፊው “ በ156 ቀበሌዎች ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ተከናውኗል ፡፡ እንዳዛም ሆኖ ግን በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች በሽታው ሊከሰት ችሏል ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ከአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚታመነው” ብለዋል ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እየጨመረ በመጣው የወባ በሽታ ሰዎች ለህመምና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ ፡ምስል፦ Mahlet Fasil Desalegn/DW

በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል ስለተባሉት ሰዎች

በበሽታው የሰዎች ህይወት እያለፈ ይገኛል በሚል ከነዋሪዎች የቀረበውን ጥቆማ አስመልክቶ በዶቼ ቬሌ የተጠየቁት የቢሮው ሃላፊ ከታችኛው የጤና መዋቅሮች የሞት ሪፖርቶች ለቢሮው መላካቸውን ሃላፊው ተናግረዋል ፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሞት ሪፖርት ከወባ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ መውሰድ እንደሚያስቸግር የጠቀሱት ሃላፊው “ በትክክል የሞታቸው ምክንያት በወባ ነው ወይስ በሌላ  የሚለውን መልሶ በወባ ሞት ኦዲት ማረጋገጥ / verified / ማድረግ ያሥፈልጋል ፡፡ ይህንንም በቀጣይ የምናጣራው ነው የሚሆነው “ ብለዋል ፡፡

ቀጣይ ሥራዎች  

አሁን ላይ  በዞን ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የተቀናጀ ግብረኃይል ተቋቁሞ የህዝብ ንቅናቄ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጣላቸውን የቢሮው ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ተናግረዋል ፡፡ በተለይም ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ተጨማሪ የአልጋ አጎበር እና የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ተጠይቆ በጉዞ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሃላፊው ይህም ለመከላከል ሥራው ተጨማሪ አቅም ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል ፡፡

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ዋንኛ የጤና ችግር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደ ኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር በ2030 ወባን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከመጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አገር አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ ይፋ በማድረግ እየሰራ  እንደሚገኝ ይታወቃል ፡

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW