1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት ድምጽ ሰጪዎች ደስተኛ ናቸው?

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 2 2017

ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመሩት የደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ለሀገሬው ሰዎች የተወሰነ ተስፋ ፈንጥቋል። ይሁንና በበርካታ ሽኩቻዎች ውስጥ የሚገኘው መንግሥት ደቡብ አፍሪካ ከተዘፈቀችበት የኤኮኖሚ ቀውስ የሚያወጣ የተቀናጀ የፖሊሲ ዕቅድ የለውም።

ደቡብ አፍሪካ
ከደቡብ አፍሪካ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው አብዛኛዎቹ ወጣቶች ሥራ አጥ በመሆናቸው ኑሯቸውን ለመግፋት ችግር ውስጥ ወድቀዋል።ምስል Nic Bothma/EPA-EFE

በደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት ድምጽ ሰጪዎች ደስተኛ ናቸው?

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሰኔ የተመሠረተው የደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት 100 ቀናት ሞልቶታል። በርካቶች በዚህ ወቅት ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመሩትን መንግሥት ስኬቶች እና ቀጣይ አካሔድ እየገመገሙ ይገኛሉ።

አስር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ለመቆጣጠር እና ሀገሪቱን ለመምራት ሲወዳደሩ የተፈጠረው ልዩ ሙከራ “ለጋ” ለሚባለው የደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲ ትልቅ ትርጉም አለው።

ለአዲሱ መንግሥት ትልቁ ፈተና የደቡብ አፍሪካ ኤኮኖሚ ዕድገት እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ሥራ አጥነት ናቸው። በሀገሪቱ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሥራ ይፈልጋሉ። ከግማሽ በላይ የሀገሪቱ ወጣቶች ሥራ አጥ ናቸው። ከዋጋ ግሽበት ጋር ተደማምሮ እጅግ ደሐ የሚባሉ የሀገሬው ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ አሁንም ይቸገራሉ።

በተስፋ እና በሥጋት መካከል

የደቡብ አፍሪካ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንግረስ (COSATU) በዚህ ሣምንት ሀገር አቀፍ ተቃውሞ ጠርቶ ነበር። በተለያዩ ከተሞች የተካሔዱት ሰልፎች ሥራ አጥነትን ለመቀነስ የተወሰደው እርምጃ ዘገምተኝነት እና የአንድነት መንግሥት በተመሠረተ በሦስተኛው ወር የተላለፈው የወጪ ቅነሳ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።

የአንድነት መንግሥት ሲቋቋም ከውጪ ከፍ ያለ መተማመን ቢፈጥርም በደቡብ አፍሪካ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንግረስ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች በሀገሪቱ ያለውን ስሜት አደብዝዞታል። ደቡብ አፍሪካዊው ተንታኝ ሳንዲሌ ስዋና የአንድነት መንግሥት ሲመሠረት ሀገሪቱ ወደ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በመሸጋገሯ ስኬታማ ሆናለች የሚል እምነት አላቸው።

“ሥልጣን ጠቅልሎ ከያዘው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ተላቃ ሀገሪቱ ውድድር ወደሞላበት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በመሸጋገሯ ደቡብ አፍሪካ እና መላው አፍሪካ ደስ ሊላቸው ይገባል” የሚሉት ሳንዲሌ ስዋና “በርካታ ሥጋቶች እና ብዙ ዕድሎች ይኖራሉ። ነገር ግን ወዲያው ስኬታማ አይሆንም። ብዙ ሥራ ይጠይቃል” በማለት ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በታሪክ ከአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በነበረው በደቡብ አፍሪካ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንግረስ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች በአጠቃላይ በሀገሪቱ ፓርቲውን በተመለከተ ያለውን አተያይ የሚጠቁሙ ናቸው።

የደቡብ አፍሪካ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንግረስ (COSATU) በሀገሪቱ የበረታውን የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት በመቃወም ሀገር አቀፍ ተቃውሞ እንዲካሔድ ጥሪ አድርጓልምስል Esa Alexander/REUTERS

የኔልሰን ማንዴላ ነጻ አውጪ ፓርቲ ባለፈው ግንቦት ወር በተካሔደው ምርጫ 40 በመቶ ገደማ ድምጽ ብቻ በማግኘት በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ሽንፈት ገጥሞታል። ይሁንና ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ዴሞክራሲያዊ ጥምረት (Democratic Alliance) ከተባለው እና ሌሎች በርካታ አነስተኛ ፓርቲዎች ጋር በመጣመር ሥልጣናቸውን ማስጠበቅ ችለዋል።

አንዳንዶች ራማፎሳ ታሪኩን በሙሉ በአንዳች የሙስና ቅሌት ስማቸው በሚነሳ ጉምቱ ፖለቲከኞች ሲመራ የቆየውን የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ለማነቃቃት ኃላፊነታቸውን ለሌላ አሳልፈው ቢሰጡ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

የደቡብ አፍሪካ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንግረስ እና የተጣመሩ ፓርቲዎች ሁሉ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ተቆጣጥሮት የቆየውን ሥልጣን በመቀየር የአንድነት መንግሥት መመሥረቱ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ በማሳሰብ በለውጡ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እየሞከሩ እንደሚገኙ ስዋና ይናገራሉ።

ራማፎሳ የሚመሩት የአንድነት መንግሥት ሀገሪቱን ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል አጠቃላይ የፖሊሲ ዕቅድ የለውም የሚለው ትችት ተንታኙ ስዋና የሚጠቅሱት ዐበይት ጉዳይ ነው። ከተመሠረተ 100 ቀናት ያስቆጠረው መንግሥት ከደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ይልቅ ለቢዝነስ እና ኢንዱስትሪ ትኩረት ሰጥቷል ሲሉም ይተቻሉ።

“የሀገሪቱ ሕዝብ የሆነ ዕቅድ ያስፈልገናል” የሚሉት ስዋና “ዕቅዱ የዴሞክራሲያዊ ጥምረት ፓርቲ፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ወይም የደቡብ አፍሪካ የንግድ ማኅበረሰብ ሊሆን አይገባም” የሚል አቋም አላቸው። ስዋና “በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን እየመራ የሚገኘው የተወሰኑ ሰዎች ስብስብ ነው። የአንድነት መንግሥት አይደለም” ሲሉ ይተቻሉ።

በዓለም ላይ በሕዝቦቻቸው መካከል ከፍተኛ የሀብት ልዩነት ካለባቸው ሀገራት አንዷ ደቡብ አፍሪካ ናት ምስል McPHOTO/blickwinkel/picture alliance

ስዋና ባለፉት 100 ቀናት በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ከሚገኙ ተሿሚዎች በቂ የኃይል አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ውድቀት፣ መጠነ ሰፊ ወንጀል እና ሙስናን ለመዋጋት በሚያስፈልግ ጥረት ላይም ይሁን የሥራ አጥነትን በመሳሰሉ በአንገብጋቢ ጉዳዮች ረገድ አንዳች አስተያየት እንዳልሰጡ በአጽንዖት ያነሳሉ። ችግሮቹ በ100 ቀናት ሊፈቱ እንደማይችሉ የሚስማሙት ስዋና የሹማምንቱ ዝምታ ግን የደቡብ አፍሪካን የአንድነት መንግሥት የሥራ አፈጻጸም ለመገምገም አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል።

ያላቻ ጋብቻ፦ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ እና ዴሞክራሲያዊ ጥምረት

ከዚህም ባሻገር በደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት ውስጥ ያለው ሽኩቻ መነጋገሪያ የሆነ ነው። በቅርቡ ለመጪዎቹ አስር ዓመታት የደቡብ አፍሪካን የጤና አገልግሎት ይቀይራል በተባለለት ብሔራዊ የጤና መድን አተገባበር ላይ ፖለቲካዊ ልዩነት ተከስቷል።

የዕቅዱ ዋንኛ ተቃዋሚ ዴሞክራሲያዊ ጥምረት የተባለው ፓርቲ ተግባዊ ሊደረግ የታሰበው ብሔራዊ የጤና መድን ለቢዝነስ መጥፎ ነው በማለት ይሞግታል።

በዴሞክራሲያዊ ጥምረት እና በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ መካከል ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት በተዘጋጀ አዋጅ ላይ ጭምር ግጭት ተፈጥሯል። በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል በተፈጠረው ልዩነት ፕሪቶሪያ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞችን የሚያካትተው የትሽዋኔ ከንቲባ ከሥልጣናቸው ተባረዋል። ከንቲባው የዴሞክራሲያዊ ጥምረት አባል ነበሩ።

በዚህ ሁሉ አለመግባባት ውስጥ የበለጠ ተጎጂ እየሆነ የመጣው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በውስጡም ሆነ በደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት ውስጥ የተቀናጀ ድምጽ መፍጠር ተስኖታል።

ጥቂት ሊለካ የሚችል ለውጥ

በአዳዲስ ባቡሮች እና የሀገሪቱን ዋና ዋና ወደቦች በማሻሻል በሎጂስቲክስ፣ በሕዝብ እና በሸቀጦች ማጓጓዣ ዘርፎች ባለፉት ወራት ሊለካ የሚችል ለውጥ መኖሩን ስዋና ገልጸዋል።

በዴሞክራሲያዊ ጥምረት ፓርቲ የሚመራው የደቡብ አፍሪካ ሀገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቪዛ፣ የሥራ ፈቃድ እና የፓስፖርትን ጨምሮ ለረዥም ጊዜ ለተከማቹ ማመልከቻዎች መልስ ለመስጠት የሚያስችል አጠቃላይ ዕቅድ ይፋ አድርጓል።

ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ባለፈው ግንቦት ወር በተካሔደው ምርጫ ያገኘው ድምጽ 40 በመቶ ገደማ ብቻ በመሆኑ የአንድነት መንግሥት ለመመስረት ከዴሞክራሲያዊ ጥምረት (Democratic Alliance) ጋር ተጣምሯል። ምስል South African GCIS/AP/picture alliance

በርካታ የምክር ቤት አባላት የተመረጡባቸውን አካባቢዎች እየጎበኙ ነው። ሚኒስትሮች ለተሾሙባቸው ተቋማት ሥራዎች ትኩረት መሥጠት ጀምረዋል። ነገር ግን የዶይቼ ቬለው ዘጋቢ ቱሶ ኩማሎ እንደሚለው አዲሱ መንግሥት የደቡብ አፍሪካውያንን እምነት እና ድጋፍ ለማግኘት ወደ ሀገሪቱ ዜጎች የበለጠ መቅረብ አለበት።

ኩማሎ እንደሚለው የደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት በዝግታም ቢሆን ወደፊት መራመድ እንጀመረ ዜጎች እየታዘቡ ነው። ነገር ግን “ሰዎች ከፍተኛ ለውጥ ይጠብቃሉ፤ ማኅበራዊው ለውጥ እንደሚጠበቀው ፈጣን አይደለም” የሚለው ኩማሎ ሥራ አጥነት እና የወንጀል መስፋፋት አሁንም የሀገሬውን ዜጎች ከሚፈትኑ መካከል እንደሆኑ አስረድቷል።

“ወደፊት ለመራመድ እና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከፖሊሲዎቻቸው ጋር መጣጣም አለባቸው። እንደዚያ ከሆነ ሰዎች በምን እንደሚለኳቸው በግልጽ ያውቃሉ” የሚለው ቱሶ ኩማሎ ”ስኬቱ ፓርቲዎቹ በፖሊሲዎቻቸው፣ በርዕያቸው እና በአምተኛው ዓመት መጨረሻ ሊያሳኩ በሚልጉት ግብ ምን ያክል ቀናጃሉ በሚለው ይወሰናል” በማለት አስረድቷል።

የተነቃቃው የንግድ እንቅስቃሴ

የፖለቲካ ተንታኙ ዳንኤል ሲልከ “የደቡብ አፍሪካ የአንድነት መንግሥት በሀገሪቱ ያለውን ስሜት አሻሽሎታል” ሲሉ ይናገራሉ። በተለይ ራማፎሳ የሚመሩት የአንድነት መንግሥት “በሀገሪቱ አክራሪ የሚባለውን የፖለቲካ ኃይል በተለይም የኤኮኖሚ ነጻ አውጪዎች (Economic Freedom Fighters) እና ኤም ኬ ያሉትን ገሸሽ በማድረግ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን መካከለኛ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ማጣመሩ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ባለወረቶችን ጨምሮ በብዙዎች አተያይ ለንግድ ሥራ አመቺ ተደርጎ የሚወሰድ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አወቃቀር በጁሐንስበርግ የአክሲዮን ገበያ እና በሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረ የፖለቲካ ተንታኙ አስረድተዋል። የራንድ የምንዛሪ ተመን 7.5 በመቶ ተጠናክሯል። የአክሲዮን ገበያው በአንጻሩ 11 በመቶ ከፍ ብሏል።

ነገር ግን ዳንኤል ሲልከ ባለፉት 100 ቀናት ተጨባጭ የፖሊሲ ማሻሻያ ይፋ እንዳልሆነ በስዋን ሐሳብ ይስማማሉ። “ባለፉት 100 ቀናት ተጨባጭ የፖሊሲ ማሻሻያ ለውጥ በደቡብ አፍሪካ አላየንም” የሚሉት ዳንኤል ሲልከ “አብዛኛው የተሻለ ገጽታ ለመፍጠር የተደረገ ማለባበስ ነው። ነገር ግን በኤኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ ደቡብ አፍሪካ የት መድረስ እንዳለባት የሚጠቁም ዝርዝር ጉዳይ ይቀራል” በማለት አስረድተዋል።

ማርቲና ሽዊኮውስኪ/እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW