1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በደቡብ ኢትዮጵያ አሪ ዞን የተከሰተው ጸረ ሰብል ተምች ያስከተለው ስጋት

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2018

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳ ለጊዜው “ ምንነቱ ያልታወቀ “ ባሉት ተባይ የአርሻ ማሳቸው መወረሩን አርሶ አደሮች ተናገሩ ፡፡ ተባዩ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው የሰብሎችን ፈሳሽ በመምጠጥና በማድረቅ መሆኑን የተናገሩት አርሶአደሮቹ ተባዩ ከሳምንት በፊት በአካባቢው ከታየ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ መንጋነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ የተምች ወረርሽኝ ተከሰተ
በደቡብ ኢትዮጵያ አሪ ዞን የተምች መንጋ ተከሰተምስል፦ Private/Ari zone communication affairs office

 

በአሪ ዞን የተከሰተው ምንነቱ ያልታወቀ ተባይ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳ ለጊዜው “ ምንነቱ ያልታወቀ “ ባሉት ጸረ ሰብል ተባይ የአርሻ ማሳቸው መወረሩን አርሶ አደሮች ተናገሩ ፡፡ ተባዩ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው የሰብሎችን ፈሳሽ በመምጠጥና በማድረቅ መሆኑን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል ፡፡ ተባዩ ከሳምንት በፊት በአካባቢው ከታየ በኋላ  ቀስ በቀስ ወደ መንጋነት እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል ፡፡

ተባዩ ያገኘውን ሰብል ሳይመርጥ እየበላ እንደሚገኝ ለዶቼ ቬለ የገለጹት ሦስት የማለተር ቀበሌ አርሶአደሮች “በወረዳው ቀደምሲል  የአንበጣም ሆነ የተምች ተባይ ተከስቶ ያውቃል ፡፡ የአሁኑ ተባይ ግን ለአካባቢው አዲስና ከዚህ በፊት የምናውቀው አይነት አይደለም “ ብለዋል ፡፡

ተባዩ በምርት ላይ የደቀነው ሥጋት

አርሶአደሮቹ እንደሚሉት በአካባቢያቸው የተከሰተውተባይ በመጠኑ ከዝንብ ከፍ ያለና በራሪ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በባህር ዛፍ ቅጠሎች ላይ መስፈሩን የተናገሩት አርሶአደሮቹ “ በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ቦቆሎ ፣ ማሽላ እና የቡና ዛፍ ቅጠሎች ላይ ተዛምቷል፡፡ አሁን ላይ በመጠኑ እየጨመረ በመንጋ መልክ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ፡፡ የሚመርጠው ተክል ያለም ፡፡ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎችን ጨምሮ ባገኘው አረንጓዴ ቅጠል ላይ በመስፈር ወደ ቢጫነት እየቀየራቸው ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

ተባዩ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው የሰብሎችን ፈሳሽ በመምጠጥና በማድረቅ መሆኑን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል ፡፡ምስል፦ Private/Ari zone communication affairs office

የመከላከል ሥራው

ዶቼ ቬለ ተከሰተ የተባለውን ተባይ አስመልክቶ ያነጋገራቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የአርባምንጭ እጽዋት ጥበቃ ማዕከል ሃላፊ አቶ ሙሉዓለም መርሻ ተባዩ ጉዳት የሚያደርሰው የሰብሎችን ፈሻስ በመምጠጥና በማድረቅ ነው ይላሉ ፡፡ በአሁኑወቅት ተባዩ በሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በባህላዊ መንገድ  እና በኬሚካል ርጭት የመከላከል ሥራው በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡

ተባዩ የአንበጣ አይነት ባህሪ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ሙሉዓለም “  ጠዋት እና ማታ ንቁ አይደልም ፡፡  ካረፈበት ቦታ አይንቀሳቀስም ፡፡ አርሶአደሩ በዚህ ወቅት ከተክሎች ላይ በማራገፍና በመጨፍለቅ እየተከላከለ ይገኛል ፡፡ እንዲሁም ለተባዩ መቆያና መራቢያ ሊሆኑ የሚችሉ አረሞችን የማስወገድ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ፡፡ በተጨማሪነት የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ወደ ወረዳው በማድረስ የርጭት ሥራ  እየተከናወነ ነው ፡፡ አሁን ላይ በአብዛኛው በቁጥጥር ሥር እየዋለ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የተባዩን አይነት መለየት  

ተባዩ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተገናኘ ወይም ከአጎራባች አገራት የገባ ሥለመሆኑ ለጊዜው ማረጋጋጥ እንዳልተቻለ የጠቀሱት አቶ ሙሉዓለም “ አሁን ላይ በግምት ደረጃ የማሽላ መጣጭ ተባይ ከሚባለው የተባይ አይነት ጋር ተመሳሳይነት አለው ፡፡ ነገር ግን ይህን በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጥ ያሥፈልጋል ፡፡ ለዚህም ናሙና በመሰብሰብ በቤተ ሙከራ ውስጥ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍል ታላቁን የስምጥ ሸለቆ ተከትሎ ከኬኒያ በሚነሳ የግሪሳ ወፍ እና የአንበጣ መንጋ በሰብሎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚደርሱ ይታወቃል ፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ብይነ መንግሥታት / IGAD /  አባል አገራት ድንበር ተሻጋሪ ተባዮችን መረጃ በመለዋወጥ በጋራ ለመከላከል እንደአውሮፓዊያኑ  አቆጣጠር በ2020 ዓ.ም በአዲስ አባባ አድርገውት በነበረው ጉባዔ ከሥምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡


ፎቶ ከዎባ ኣሪ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኑኬሽን ጽህፈት ቤት
ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW