በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንዳንድ ግጭቶችን የዳሰሰዉ ኮንፈረንስ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2017
“ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአስተዳደራዊ መዋቅር ወሰኖች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች የክልሉን የልማት ትኩረት እየሰረቁ ነው “ አሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሠላም ፤ የአንድነት እና የልማት ኮንፈርንስ ላይ እንዳሉት ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም በአንዳንድ የክልል አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ ብለዋል ፡፡ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የፖለቲካ ትንታኛና የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባል የግጭቱ መነሻ በኢፌዴሪ ህግ መንግሥት ላይ በሚስተዋለው ክፍተት የተነሳ ነው ይላሉ ፡፡
የሶዶው የሠላም፣ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንስ ምን አነሳ ምን ጣለ ?
ከሁለት ዓመታት በፊት ምሥረታውን ያካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የሠላም፣ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንስ በዎላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል ፡፡ በኮንፍረንሱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በክልሉ ከምሥረታው ወዲህ ተከናውነዋል ያሏቸውን ተግባራት አብራርተዋል ፡፡ በህዝቡ የሚነሱ ያደሩ ጥያቄዎችንና አዲስ የልማት ፍላጎቶችን ለሟሟላት ጥረት መደረጉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሦስት ወረዳዎች የእንስሳት ወረርሽኝ ተቀሰቀሰ
ያልተፈቱት ግጭቶች
የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን የህዝበ ለህዝብ ሥራዎች መከናወናቸውንና የፀጥታ መዋቅሮችን አቅም የማጎልበት ሥራ መሠራቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡ ይሁንእንጂ አልፎ አልፎ በውስን ቦታዎች በመዋቅሮች መካከል ባሉ ወሰኖች በሚከሰቱ አለመግባባቶች የሚነሱ ግጭቶች መኖራቸውን መደበቅ አይቻልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “ እነኝህ ግጭቶች የክልሉን የልማት ትኩረት እየሠረቁ ይገኛሉ ፡፡ ግጭቶቹ ለግል ፍላጎታቸው ጥያቄ አባሪ ለማድረግ በሚከጅሉ ጥቂት አካላት የሚነሱ ናቸው ፡፡ የዚህ ኮንፍረንስ ዋና ዓላማ እነዚህንና መሰሎቻቸው ከተጠናወታቸው በሽታ አክሞና ፈውሶ ለማለፍ ነው “ ብለዋል ፡፡ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ኮሬ ዞን ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች ተገደሉ
የግጭቶቹ መሠረታዊ ምክንያት ምንድ ነው?
12ኛ ክልል በመሆን ነሀሴ 12 2015 ዓ.ም ምሥረታውን ያካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምሥረታው ማግሥት አዳዲስ የማንነትና የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች እየተነሱበት እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡ በተለይም በጋሞ ዞን የዛይሴ እና የቁጫ አካባቢዎች እንዲሁም በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶችን ካስተናገዱ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ ፡፡ ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የፖለቲካ ትንታኛና የቀድሞው የህዝብ ተወካች ምክር ቤቱ አባል አቶ ዳያሞ ዳሌ የግጭቱ መነሻ ምክንያት በኢፌዴሪ ህግ መንግሥት ላይ በሚስተዋሉ ክፍተቶች የተነሳ ነው ይላሉ ፡፡ ብሄር ብሄረሰብ ከሆንክ የራሴ አስተዳደር ይገባኛል ብለህ የመጠየቅ መብት አለህ ፡፡ የወረዳ ፣ የዞን ወይንም የክልል መዋቅር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ህገ መንግሥቱ በሀሳብ ደረጃ መብት ከመስጠት በስተቀር መሬት ላይ አንዴት እንደሚተገበር ዝርዝር ህግ የለውም ፡፡ አከሌ ይገባዋል ወይንም አይገባውም የሚል ቁርጥ ያለ መልስ አይሰጥም ፡፡ በዚህም የተነሳ ከተጨቃጨኩና ከተጋጨሁ ላገኝ እችላለሁ የሚል አካሄድ እንዲለመድ በማድረግ ጥያቄው የግጭት ምንጭ እንዲሆን እያደረገው ይገኛል “ ብለዋል ፡፡ተስፋ የተጣለበት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልል የሰላም ምክክር
እንደመፍትሄ
አሁን ላይ ህገ መንግሥቱን የማሻሻል አጀንዳ ለብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን መቅረቡንና በዚያው መንገድ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አቶ ዳያሞ ተናግረዋል ፡፡ ይሁንአንጂ በአሁኑወቅት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ሥጋቶችን ለመቀመስ ክልሉ ሁለት ነገሮች ያሥፈልጉታል የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ዳያሞ “ አንድም ግጭቱን የሚመሩና በሂደቱም የሚሳተፉ የየአካባቢ ባለሥልጣናት ላይ የህግ የበላይነትን ማስፈን ሁለቱም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር ይገባል ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወይም በዚያ ካልተዳደርኩ ብሎ መሞት የሚፈልግ አርሶአደር እንደሌለ ይታወቃልና “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ