1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሬ ዞን ሰዎች በተደጋጋሚ እየተገደሉ ነዉ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 12 2017

በዞኑ ጎርካ ወረዳ የዳኖ ቀበሌ እንደ ከሬዳ ሁሉ ተመሳሳይ ሥጋት ውስጥ እንደምትገኝ ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ በተለይም ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ታጣቂዎች በአርሻ ሥራ ላይ የነበሩ ሁለት አርሶአደሮችን ተኩሰው ካቆሰሉ ወዲህ አርሶአደሮች ወደ ማሳ ወርደው ምርት ለመሰብሰብ መቸገራቸውን ነው አንድ የመንደሩ ነዋሪ የገለጹት

ነዋሪዎች እንደሚሉት በዞኑ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር የዜጎችን ደሕንነት መጠበቅም አልቻለም
በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሬ ዞን ካለፈዉ መስከረም መጀመሪያ ጀምሮ 15 ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸዉን ነዋሪዎችና ፖለቲከኞች አስታዉቀዋልምስል Kore Zone communication office

በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሬ ዞን ሰዎች በተደጋጋሚ እየተገደሉ ነዉ

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን እየጨመረ በመጣው የታጣቂዎች ጥቃት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡ በአካባቢው የፀጥታ ሥጋቱ እየበረታ የመጣው ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩ 15 አርሶአደሮች መገደላቸውን ተከትሎ ነው ፡፡ የዞኑ የህዝብ እንደራሴዎችና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲያስከብር ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ አካባቢውን “ ሸኔ “ ሲል ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ለማጽዳት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀናጅቼ እየሰራሁ ነው ብሏል ፡፡

ከሥጋት ያልተላቀቀው የኮሬ አካባቢ

በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ የምትገኘው የከሬዳ ቀበሌበታጣቂዎች ጥቃት የተነሳ የፍረሃት ድባብ ከጠላባት  ሰነባብቷል ፡፡ በዚህች ቀበሌ ብቻ በአንድ ሳምንት በታጣቂዎች የተገደሉ ሦስት ጎረቤቶቻቸውን መቅበራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡

አቶ አዳነ ቹመታ የከሬዳ ቀበሌ ነዋሪና በሙያቸው የጤና ባለሙያ መሆናቸውን ይነገራሉ ፡፡ ሳይታሰብ በተደጋጋሚ ወደ መንደሩ የሚገቡ ታጣቂዎች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል የሚሉት አቶ አዳነ  “ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው ፡፡ ደህንነታችንን የሚጠብቅ  አካል ባለመኖሩ ሁልጊዜ በሥጋት ውስጥ ነው ያለነው ፡፡  ለምሳሌ አኔ የጤና ባለሙያ ብሆንም ካለብኝ ሥጋት አንጻር ራሴን ለመጠበቅ የግል መሣሪያ መታጠቅ ግድ ሆኖብኛል “ ብለዋል ፡፡

በዞኑ ጎርካ ወረዳ የዳኖ ቀበሌ እንደ ከሬዳ ሁሉ ተመሳሳይ ሥጋት ውስጥ እንደምትገኝ ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ በተለይም ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ታጣቂዎች በአርሻ ሥራ ላይ የነበሩ  ሁለት አርሶአደሮችን ተኩሰው ካቆሰሉ ወዲህ አርሶአደሮች ወደ ማሳ ወርደው ምርት ለመሰብሰብ መቸገራቸውን ነው አንድ የመንደሩ ነዋሪ የገለጹት ፡፡

የአርሶአደሮች ግድያ

አቶ ቃዬል ቡሱአ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ / ኢዜማ / ፓርቲ የኮሬ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት  ሃላፊ ናቸው ፡፡ በዞኑ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ፓርቲያቸው በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን የጠቀሱት ሃላፊው “ ባለን መረጃ ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ ብቻ 15 አርሶአደሮች ተገድለዋል ፡፡ አሁንም ህዝቡ እየሞተ ነው ያለው ፡፡ ዓላማው ከእርሻቸው ላይ ማባረርና መፈናቀል  ነው “ ብለዋል ፡፡

በአካባቢው የታጣቂዎች ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ሌላው የኮሬ ዞን ህዝብን በመወከል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የህዝብ እንደራሴ የሆኑት አቶ ዜናነህ አዱላ ለዚህ ምክንያቱ ሁለት ነው ይላሉ ፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት በአካባቢው ግድያ በሚፈጽሙ አካላት ላይ የህግ የበላይነት አለማስፈኑ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዜናው “ ሌላው በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን አብዛኛው ቀበሌያት “ ሸኔ “ የሚባለው ታጣቂ ቡድን የሚንቀሳቀስበት መሆኑ ነው ፡፡ ይህም ለተፈጸሙ ጥቃቶች ሃላፊነት የሚወስድ አካል ማግኘት እንዳይቻል አድርጎታል “ ብለዋል ፡፡

የክልሉ መንግሥት ምን ይላል

ዶቼ ቬለ በኮሬ ዞን በሚስተዋለው የፀጥታ ሥጋር ዙሪያ የጎርካ ወረዳንም ሆነ የኮሬ ዞን የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት አድረጓል ፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች ስብሰባ ሌሎች ደግሞ ጉዞ ላይ መሆናቸውን በመግለጻቸውና ተለዋጭ የሥልክ ቀጠሮ ቢያዝላቸውም  በቆጠሯቸው ባለመገኘታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ ዛሬ ከክልሉ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ  ጉዳዩ ከጋዜጠኞች ተነስቶላቸዋል ፡፡

“ በእኛ የአስተዳደር ወሰን በሦስት እና በአራት መዋቅሮች አካባቢ የሸኔ እንቅስቃሴ አለ “ ያሉት አቶ አለማየሁ “ አሁን ከፌዴራል ፀጥታ አካላት ጋር በመሆኑ በቅንጅት እየተንቀሳቀስን ነው  ፡፡ ችግሩ ለህዝቦቻችን ዕዳ ሆኗል ፡፡ ግን ደግሞ መልክ ለማስያዝ እየሠራን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW