በደቡብ ክልል እያገረሸ የመጣው የወባ በሽታ
ሐሙስ፣ ኅዳር 8 2015የኢትዮጵያ መንግሥት የወባ በሽታን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለማስቆም የተለያዩ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡በተለይም የአገሪቱ የጤና ሚንስቴር እ.አ.አ በ2009 ዓ.ም ወባን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንዲረዳ የነደፈው ስትራቴጂ በተወሰነ ደረጃ ውጤታማ መሆን የጀመረ መስሎ ነበር ፡፡ ‹‹ በኢትዮጲያ አቆጣጠር በ2022 ዓ.ም. ወባ የኅብረተሰቡ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ ›› በሚል የተያዘው ግብ ከስኬት ይደርስ ይሆን ወይ የሚለው አሁን አሁን ሲበዛ አጠራጣሪ እየሆነ ይገኛል፡፡ በአብዛኞቹ ክልሎች የወባ በሽታ ሥርጭት እየሠፋና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚገኝ ከየክልሎቹ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ የጤና ሚኒስቴር በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በያዝነው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ በሚኒስቴሩ የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ጉዲሳ አሰፋ ‹‹ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በተካሔዱ ተግባራት ስርጭቱን ለመቀነስ ተችሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ መልሶ የማገርሸት ሁኔታ እየታየ ይገኛል ›› ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የበሽታው ደረጃ ደቡብ ክልል
በኢትዮጲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ ከመጣው የወባ በሽታ ሥርጭት አንጻር የደቡብ ክልል በቀዳሚነት ይጠቀሳል ፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በክልሉ የወባ ሥርጭት ምጣኔ ከባለፈው የ2014 ዓ.ም የሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት በ28 በመቶ ጭማሪ ጨምሯል፡፡ ‹‹ በክልላችን የወባ በሽታ ሥርጭት እየጨመረ ይገኛል ›› የሚሉት አቶ እንዳሻው በክልሉ ከነሀሴ እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም ባሉት ሦስት ወራት ብቻ ከ94 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ለበሽታው ሥርጭት መጨመር ምክንያት የሆኑ ነገሮች በጥናት መለየታቸውን የሚናገሩት የቢሮው ሃላፊ ‹‹ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የህብረተሰቡ እና የባለድርሻ አካላት መዘናጋት፣ የግብአት መቋረጥ ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግር ፣ በየአካባቢው የሚገኙት የጤና ኬላዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች እንቅስቃሴ መዳከም ለወባ በሽታ ተጋላጭነት በር እየከፈተ መምጣቱን ለማረጋገጥ ተችሏል ›› ብለዋል ፡፡
የፀረ ወባ በሽታ ንቅናቄ
በክልሉ የወባ በሽታ ሥርጭት መስፋፋት ያሳሰበው የደቡብ ክልል መንግሥት ከባለፈው የጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በሽታውን ለመከላከል ያስችላል ያለውን የንቅናቄ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል ፡፡ የንቅናቄ ዘመቻው “ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል” በሚል መሪ ሀሳብ እየተተገበረ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ይናገራሉ ፡፡ ወባን ለማስወገድ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ የንቅናቄ ዘመቻው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የሚናገሩት የቢሮ ኃላፊዉ ‹‹ በሽታዉን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የወባ ኬሚካል ርጭት ላይ ከማተኮር ይልቅ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን ፡፡ በተለይ የወባ በሽታን ለመከላከል ፣ ጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ተሳትፎ ለማጠናከር፣ የአጎበር አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን ለማጥፋት ፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ ለማጠናከር ፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ለማፋሰስ ፣ ሰዎች የወባ በሽታ ምልክቶችን በጥንቃቄ ለይተው በማወቅ ምርመራ ለማድረግ የሚረዱ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን ›› ብለዋል፡፡
የግብአት እጥረት እንደችግር
በደቡብ ክልል የፀረ ወባ ንቅናቄ ከባለፈው የጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በክልሉ በሚገኙ አሥር ዞኖች እየተካሄደ ይገኛል ፡፡ በተለይም በሽታው ጎልቶ በሚታይባቸው የኮንሶና የደቡብ ኦሞ ዞኖች ሥርጭቱን ለመግታት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የየዞኖቹ የጤና መምሪያ ሃላፊዎች ለዶቼ ቬለ DW ተናግረዋል፡፡ ይሁንእንጂ ንቅናቄውን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ የግብአት እጥረት እንዳጋጠማቸው የመምሪያ ሃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በተለይም የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ዲካቶ ሩማሌ ‹‹ በዞኑ የፀረ ወባ ማጥፊያ ኬሚካል እጥረት ገጥሞናል ፡፡ የአልጋ አጎበርም ቢሆን እንዲሁ በቂ አይደለም ፡፡ አብዛኞቹ አጎበሮች በአባወራዎች ደረጃ ከሦስት ዓመት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው ትንኞችን ለመከላከል አይችሉም ፡፡ በመሆኑም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቁ አጎበሮችን በአዲስ መተካት ያስፈልጋል ›› ብለዋል፡፡
በወባ በሽታ ሥርጭት መከላከል ረገድ በዞኖቹ አጋጥሟል ሥለተባለው የግብአት አቅርቦት ችግር ዙሪያ በዶቼ ቬለ DW የተጠየቁት በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማሌ ማቴ የግብአት አጥረት በከፊል ማጋጠሙን አረጋግጠዋል ፡፡ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ምንምእንኳን አሁን ባለው ሁኔታ ከአካባቢ ብክለት አንጻር የሚመከር ባይሆንም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከፌደራል ጤና ሚንስቴር በኩል ለክልሉ አለመቅረቡን የሚናገሩት አቶ ማሌ ‹‹ ያም ሆኖ በግዢ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ገልጾልናል ፡፡ አልጋ አጎበርን በተመለከተ ግን አሁን እጃችን ላይ ከ2ሚሊዮን በላይ አለን ፡፡ ይህን ለ64 ወረዳዎች እያሠራጨን እንገኛለን፡፡ በቀጣይ ለሠላሳ ወረዳዎች ደግሞ ተጨማሪ አጎበር እተጓጓዘ ሥለሚገኝ እጥረቱ አይኖርም ›› ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ