1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በደቡብ ክልል ውስጥ የነበሩ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሌላ አዲስ ክልል ሊመሰርቱ ነው

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 23 2014

በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች አንድ የጋራ ክልል ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ውሳኔ ሳለፉ፡፡ ምክር ቤቶቹ ውሳኔውን ያሳለፉት ዛሬ በየፊናቸው ባካሄዱት ጉባዔ ነው ፡፡

Äthiopien SNNPR Entscheidung über neu errichtete Zonen
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በክልልነት ሊደራጁ ነው

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች አንድ የጋራ ክልል ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ውሳኔ ሳለፉ ፡፡ ምክር ቤቶቹ ውሳኔውን ያሳለፉት  ዛሬ በየፊናቸው ባካሄዱት ጉባዔ ነው ፡፡ 

የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳቸውን በቻሉ ክልሎች ከተደራጁ በኋላ በክልሉ የተቀሩት 11 የዞን መስተዳድሮች ተመሳሳይ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘው ገዢው የደቡብ ብልጽግና ፖርቲ ‹‹ ዞኖቹ ኩታ ገጠምን መሠረት ባደረጉ ሁለት ክልሎች ቢደራጁ ይሻላል ›› ያለውን ምክረ ሀሳብ ሲያራምድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ምክረ ሀሳቡ በአንዳንድ ወገኖች ተቃውሞ ቢገጥመውም ፖርቲው በአደረጃጀቱ አስፈላጊነት ላይ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በአጀንዳነት ሲወያይ መክረሙን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዞኖች በኩታ ገጠም ወይስ ራሳቸውን በቻሉ ክልሎች ይደራጁ የሚለው አከራካሪ ጥያቄ ታዲያ ዛሬ ምላሽ ያገኘ ይመስላል፡፡

የዎላይታ ፣ የጋሞ፣ የጌዲኦ ፣ የኮንሶና የደቡብ ኦሞ ዞን ም/ቤቶች ዛሬ በየራሳቸው ባካሄዱት ጉባኤ በአንድ የጋራ ክልል ለመተዳደር የሚያስችላቸውን ይሁንታ ሰጥተዋል፡፡

ዶቼ ቬለ DW  በም/ቤቶቹ ውሳኔ ላይ ያነጋገራቸው የኮንሶና የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግሥስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊዎች አቶ ሠራዊት ዲባባ እና አቶ መላኩ ለማ  ምክር ቤቶቻቸው ዛሬ ባካሄዱት ጉባኤ ኩታ ገጠም የሆኑ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የጋራ ክልል ለመመስረት የሚያስችላቸውን ውሳኔ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ም/ቤቶቹ ውሳኔውን ያሳለፉት የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ የከፋ ፣ የጌዲኦ ፣ የኮንሶና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የአማሮ ፣ የደራቬ ፣ የአሌ፣ የቡርጂ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል ለመደራጀት ነው ፡፡

በክልሉ በተለምዶ የማዕከላዊ ዞን የሚባሉት የሃድያ ፣ የከንባታ ፣ የሀላባ ፣ የሥልጤና የጉራጌ ዞኖች ምክር ቤቶቻቸውን በመጥራት በጉዳዩ ላይ ይመክራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

የራሱን ተናጠላዊ ክልል ለማደራጀት ከፍተኛ ግፊት ሲያደርግ የቆየው የወላይታ ዞን ም/ቤት አፈጉባኤንም ሆነ የጽ/ቤት ሀላፊዎችን ለማነጋገር ዶቼ ቬለ DW  ጥረት ቢያደርግም ሃላፊዎቹ በውሳኔው ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የዎላይታ ዞን ዋንኛ ተቀዋሚ ፖርቲ የሆነው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ዎብን ኘሬዘዳንት አቶ አማኑኤል ዶጊሶ ግን የም/ቤቱን ውሳኔ ተገቢ ያልሆነ ሲሉ ተቃውመውታል፡፡ ‹‹ የዛሬው ውሳኔ የገዢው ብልጽግና ፖርቲ ውሳኔ እንጂ በህዝብ  ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው ብለን አናምንም ፡፡ ህዝቡ ይበጀኛል ያለውን አማራጭ በህዝበ ውሳኔ ሊወስን ይገባል ›› ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል በክልል የመደራጀት ጥያቄ ጎልቶ መታየት የጀመረው በአገሪቱ በ2010 ዓ.ም. የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ነው ፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄው በተለይ በአንዳንድ ዞኖች ያስከተለው ግርግር ለሰው ህይወት መጥፋት ፣ ለፖለቲከኞችና የአንቂዎች መታሰር ምክንያት እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW