1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በደቡብ ወሎ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩ

ሰኞ፣ ሰኔ 23 2017

የደቡብ ወሎ ዞን ለወባ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጤና ለመታደግ ከ600 ሺ በላይ የአልጋ አጎበር እና ለርጭት የሚያገለግሉ መከላከያ ኬሚካሎች ቢያስፈልጉትም ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስቱም ባለፉት 3 ዓመታት ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገልንም ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን ጤና መመሪያ የወባ መከላከል ፕሮግራም አስተባባሪ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

Macroaufnahme einer weiblichen Stechmücke
ምስል፦ J. Meul-Van Cauteren/blickwinkel/picture alliance

በደቡብ ወሎ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን 2.2 ሚሊየን ህዝብ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ሲሆን የወባ ስርጭቱም ከአመት አመት እየጨመረ ዘንድሮ 26,000 ሰዎች የወባ በሽታ ታማሚ ሆነዋል፡፡ በዞኑ ባሉ ቆላማ አካባቢዎችም ስርጭቱ ሲጨምር በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ እና የወባ ትንኝን ለመከላከል የሚረዱ አጎበር እና ኬሚካል በበቂ ሁኔታ አለመገኘት ለስርጭቱ መባባስ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ከላላ ወረዳ የወባ ማስወገድ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ታደሰ አህመድ ለአመታት የመከላከያ ግብዓት ማጣታችን ለበሽታው መባባስ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ 

‹‹በዚህ ዓመት ወባ ጨምሯል ከባለፉት አመታቶች የጨመረበት ምክንያት የጸጥታ ችግር የአካባቢው ቁጥጥር ስራውን እንደ ልብ መስራት አላስቻለንም፤ አጎበር ማግኘት የሚገባን ከ2 ዓመት በፊት ነበር እስካሁን አላገኘንም በተጨማሪም የኬሚካል ርጭት የሚካሄድባቸው 13 ቀበሌዎች በዚህ 2 ዓመት ተደራሽ አላደረግንም፡፡›› 

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፉት ሁለት አመታት ምንም አይነት የወባ ትንኝ መከላክያ ድጋፍ አልተደረገም 

የደቡብ ወሎ ዞንለወባ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጤና ለመታደግ ከ600 ሺ በላይ የአልጋ አጎበር እና ለርጭት የሚያገለግሉ መከላከያ ኬሚካሎች ቢያስፈልጉትም ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስቱም ባለፉት 3 ዓመታት ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገልንም የሚሉት በደቡብ ወሎ ዞን ጤና መመሪያ የወባ መከላከል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አሊ ሁሴን ናቸው፡፡ 

‹‹ከ600 እስከ 800 ሺ የመኝታ አጎበር ያስፈልጋል ለዞኑ አሁን አንድም አጎበር የለም ይህ ትንሽ ያሳዝናል የሚመለከተው አካልም ሊልክ አልቻለም፡፡›› 

የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምስል፦ Alemnew Mekonnen-Bahirdar/DW

በክልሉ ያለዉ ጦርነት ለወባ በሽታ መባባስ ምክንያት ነዉ

በዞኑ ከዚህ ቀደም ወባን ለመከላከል ከሚረዱ ሳይንሳዊ መንገዶች በተጨማሪ ማህበረሰቡ እና የጤና ባለሙያው ባህላዊ የመከላከያ መንገዶችን ተጠቅመው ስርጭቱን ለመቀነስ ቢችሉም አሁን ላይ በክልሉ ያለው ጦርነት እና የበጀት እጥረት ይህንን ማድረግ አላስቻለም ይላሉ አስተባባሪው፡፡ 

‹‹እኛ እራሱ ወደ ምዕራብ ወረዳ ሄደን ስራውን በአግባቡ መስራት፣ መከታተል፣ አልቻልንም የሰላሙ ሁኔታ ይታወቃል፡፡ የበጀት እጥረትም አለ በየጊዜው አስፈፃሚ አካላትና ኦፊሰሮችን መገምገም አልተቻለም፡፡›› 

26000 ሰዎች በወባ በሽታ የተያዙበት ዞኑ የስርጭት መጠኑ አነስተኛ ነዉ

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በበኩሉ በደቡብ ወሎ ዞን 26,000 ሰዎች በወባ ቢያዙም ይህ ስርጭት አነስተኛ በመሆኑ አጎበርም ሆነ ኬሚካል ርጭት ማግኘት አይችሉም ምክንያቱም ከ1000 ሰው 50 ሰዎች የወባ በሽታ አልተገኘባቸውም አቶ ዳምጤ ላንክር በኢንስቲቲዩቱ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ፡፡ ‹‹ደቡብ ወሎ ዞን ለርጭትም ለአጎበርም ብቁ አይደለም፤ የዞኑ የስርጭት መጠን ከፍተኛ አይደለም፡፡ ከፍተኛ ስርጭት የምንለው ደግሞ አመታዊ የስርጭት መጠኑ ከ1000 ሰው 50 ሰው በላይ ሲሆን ነው፡፡›› 

አሁን ላይ በአማራ ክልል ከፍተኛ የኬሚካል እና አጎበር እጥረት በመኖሩ ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ካለባቸው 40 ወረዳዎች ኬሚካል ርጭት መከወን የተቻለው በ16ቱ ወረዳዎች ብቻ ነው ይላሉ አቶ ዳምጤ ላንክር፡፡ 

‹‹የደቡብ ወሎ ዞን ብቻ አይደለም አጎበር ያላገኘው ሌሎችም ዞኖች በመስፈርቱ መሰረት አጎበር አላገኙም የኬሚካል ርጭትም አልተረጩም፤ እንደ ክልል ኬሚካል የምናስረጫቸው 16 ወረዳዎች ብቻ ናቸው፡፡ መረጨት የነበረባቸው ግን 40 ናቸው፡፡ ከፍተኛ የኬሚካል፣ የአጎበርም እጥረት አለብን፡፡››

ኢሳያስ ገላው

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW