1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በደቡብ ጎንደር ዞን በድርቅ ምክንያት ከ175ሺህ በላይ ሠዎች እርዳታ ይፈልጋሉ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8 2017

በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ነዋሪዎቹ ተናገሩ። የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በዞኑ በሚገኙ 7 ወረዳዎች በሚገኙ 57 ቀበሌዎች 175ሺህ በላይ ወገኖች ለድርቅ መጋለጣቸውን አመልክቷል ።

Äthiopien | Bilder zur Warnung der Meteorologischen Agentur | Ernte in Gefahr
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

«በደቡብ ጎንደር ዞን የተከሰተው ድርቅ ጉዳት እያደረሰ ነው » አርሶአደሮች

This browser does not support the audio element.

 

“ድርቁ ነዋሪዎች እንዲሰደዱ እያደረጋቸው ነው” ነዋሪዎች

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ከመቀጠዋ፣ ከጋይንትና ከእብናት ወረዳዎች አስተያየታቸውን የሰጡን አረሶ አደሮች እንዳሉት በአካባቢዎቹ በተደጋጋሚ የተከሰተው ድርቅ ነዋሪዎቹ አካባቢያቸውን እንዲልቁ እያደረጋቸው ነው፡፡ ከላይ ጋይንት ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ  የአካባቢው ነዋሪዎች የሚቀምሱት ነገር የለም፣ እርዳታ መጣ ቢባልም በቂ ባለመሆኑ ነዋሪው ስደቱን መርጧል ሲሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፣ በተለይ ምጥራባ፣ ዳባ ወቶክሶስ፣ ላይ ነጋላና ታች ነጋላ በተባሉ ቀበሌዎች ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ማየታቸውን አስረድተውናል፡፡

ሌላው አረሶ አደር በበኩላቸው ቁመና (እንስሳት ማለታቸው ነው) ያላቸው ሠዎች እየሸጡ ለጊዜው ከሩቅ ቦታ እህል በውድ ዋጋ እየሸመቱ ለመመገብ ቢሞክሩም ዘላቂ ሊሆን እንዳልቻለ አመልክተዋል፣ የሚሽጥ እንስሳት የሌላቸው ወገኖች ግን በርህብ እየተሰቃዩ እንደሆነ ነው የገለጡት፡፡

ወጣቶች የቀን ሥራ ሰርተው ለማደር ቢሞክሩም የሚሰራ ሥራ ባለመኖሩ ምርጫቸው ወደ ሌላ አካባቢ መሄድና ስደት ሆኗል ሲሉ ነው ያስረዱት፡፡

በዋግህምራ በድርቅና በምግብ እጥረት እየተፈናቀሉ ያሉት አርሶደሮች

“እንኳን ሠው እንስሳቱ በድርቁ ምክንያት እየተጎዱ ነው” አስተያየት ሰጪ

በስልክ ያገኝናቸው አንዲት እናት እንዳስረዱን “እንኳን ሠው እንስሳቱ በድርቁ ምክንያት እየተጎዱ ነው” ብለዋል፡፡ የሚሰጠው እርዳታም ከጥራትም ከመጠንም እጅግ ያነስ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የበላሳ ወረዳ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት ሳሚ፣ ላቫ፣ ሳውጋሪ፣ አጃንዳብ፣ ላየና ሴራ በተባሉ ቀበለኤዎች የሚኖሩ በሺህ የሚጠሩ ነዋሪዎች በድርቅ ተጠቅተዋል ብለዋል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን  አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን በስልክ ብንጠይቅም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

ነዋሪዎቹ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለችግራቸው እንዲደርሱላቸው ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ

“175ሺህ 915 ነዋሪዎች በድርቅ ትጥቅተዋል” የደቡብ ጎንደር ዞን አድጋ መከላከል ጽ/ቤት

በአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ አበባው አየነው በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በዞኑ በሚገኙ 7 ወረዳዎች በሚገኙ 57 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ 175ሺ 915 ሠዎች መጠቃታቸውን ጠቅሰው በምንግሥት ለእብናት፣ ለስማዳ፣ለሰዴ ሙጃና መቀጠዋ ተረጂዎች 12ሺ 419  ኩንታል የምግብ እህል ተከፋፍሏል ነው ያሉት፣ የኢተዮጵያ ቀይ መስቀልም 1ሺህ 500 ለሚሆኑ የእብናትና መቀተዋ ተርጂዎች ይፊኖ ዱቄት እርዳታ ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

ድርቅ፣ረሃብ እና የምግብ ዋስት እጦት በኢትዮጵያ

“በድርቁ ምክንያት የተፈናቀል ሠው የለም” ስለመባሉ

በድርቁ ምክንያት ቤቱን ዘግቶ የተፈናቀለ ሠው የለም ሲሉ የተናገሩት አቶ አበባው፣ ሆኖም ሥራ ለመፈለግ ወደሌሎች ቦታዎች የተንቀሳቀሱ ሠዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

ለድርቁ መባባስና ለምርት መቀነስ ከዝናብ እጥረቱ በተጨማሪ በክልሉ ያለው ወቅታዊ የሠላም እጦት ሌላው ምክንያት እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጠዋል፡፡

በደቡ ጎንድር ዞን 13 የገጠር ወረዳዎች ሲኖሩ 398 ቀበሌዎች ይገኛሉ፣  ድርቅ የተከሰተባችው ቀበሌዎች በላይ ጋይንት፣  በታች ጋይንት፣ በእብናት፣ በስማዳ፣ በመቀጠዋ፣ በሰዴ ሙጃ፣ በጉና በሚገኙ 57 ቀበሌዎች መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክያል፡፡

ለአማራ ክልል አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር  ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ዘውዱ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን ከትናንት ጀምሮ እሰክ ዛሬ ቀትር ድረሰ በስልክ ያደረነው ጥሪና አጭር የፅሁፍ መልዕክት ምላሽ አላገኘም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW