1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በዱባይ አራት ሺሕ ኢትዮጵያውያን ዕርዳታ ይፈልጋሉ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 14 2012

በዱባይ የሚኖሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ሳቢያ ሥራቸው በመስተጓጎሉ ዕርዳታ ይፈልጋሉ። በዱባይና ሰሜናዊ ኤሚሬቶች የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ከመጋቢት 27 ጀምሮ 4 ሺሕ ዕርዳታ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን መዝግቧል። በወርሽኙ ሳቢያ የተጣለው ገደብ በዚሁ ከቀጠለ እስከ 20 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ችግር ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ሥጋት አለ

Arbeitsbedingungen für Frauen Ethiopische Frau im Libanon bei der Arbeit
ምስል፦ AP

በዱባይ ብቻ 20 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ችግር ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ

This browser does not support the audio element.

በዱባይ እና ሰሜናዊ የኤሚሬት አካባቢዎች የሚኖሩ አራት ሺሕ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ፍለጋ በአካባቢው የኮሮና ወረርሽኝ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመግታት ከተቋቋመ ኮሚቴ ዘንድ ተመዝግበዋል። ኮሚቴው በኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እና በዱባይ እና በሰሜናዊ ኤሚሬቶች የሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበር (Ethiopian Community UAE) የተቋቋመ ነው።

ኮሚቴውን በበላይነት የሚመሩት እና የማኅበሩ የቦርድ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ መንሱር መሐመድ «ከመጋቢት 27 እስካሁን ወደ 4 ሺሕ ሰዎች አካባቢ እርዳታ ይድረሰን የሚሉ የስልክ ጥሪዎች ደርሰውናል። ከአራት ሺሕ ሰዎች ወደ 1890 አካባቢ እርዳታ እንዲደርሳቸው አድርገናል። በየቀኑ ለ250 ሰዎች እርዳታ ለማድረስ እየሰራን ነው። የአስራ አምስት ቀን የምግብ እርዳታ እየሰጠን ነው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ለእርዳታ ከተመዘገቡት መካከል ከሰባት ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ ቤት የምትኖረው አስቴር አንዷ ነች። አስቴር የቤት ኪራይ የምትከፍለው ገንዘብ የላትም። ለአራት ወር ልጇ ወተት እንኳ አጥታለች።

ለልጄ «ጡቴን ነው የምሰጣት፤ ሌላ ምንም ነገር የለኝም። ዳይፐር፣ ወተት፣ ሳሙና ያስፈልጋኛል። አዋቂ እንደ ምንም መቋቋም ይችላል። ልጅ ነው የሚያስቸግረው። የቤት ኪራይ እንኳ የምከፍለው የለኝም፤ ከሰው ተጠግቼ ነው ያለሁት። [ከኢትዮጵያ] የወጣሁት ያልፍልኛል ብዬ ነበር፤ አልሆነልኝም» ስትል አስቴር ሕይወቷ የገባበትን ምስቅልቅል ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

አስቴር በሰው ቤት ተቀጥራ ለመስራት ወደ ዱባይ ካቀናች ሶስት አመታት ተቆጠሩ። «ከኢትዮጵያ መጥቼ ሰው ቤት ገባሁ። የሚከፍሉኝ በራሴ ቀለብ ስለሚያልቅ እሱን ጠልቼ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ከምሰራበት ቤት ጠፍቺያለሁ» የምትለው አስቴር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሞከረችው ሥራም ፈተና የበዛበት ነበር።

ወረርሽኙን ለመከላከል በተጣለ ገደብ የዱባይ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟልምስል፦ picture-alliance/AP Photo/J. Gambrell

ለስምንት አመታት በዱባይ የኖረችው ሰዓዳ እንደ አስቴር ሁሉ አንድ ልጇን ብቻዋን የምታሳድግ እናት ነች። ባለፉት ስምንት አመታት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዛ የማታውቀው ሰዓዳ «ይደውላሉ፤ ሔጄ አጸዳለሁ፤ በሰዓት ይከፍላሉ» ስትል ከዚህ ቀደም ትተዳደርበት የነበረ ሥራዋን ትገልጻለች። በቀን ከሁለት በላይ ቦታዎች የሚያጉዛት ሥራ ግን የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የሚቀጥል አልሆነም። «ሥራ የለም። እኔ አሁን ሥራ ካቆምኩ አንድ ወሬ ነው።አሁን ሁሉም ነገር ተቆላልፎ ቤት ውስጥ ነው ያለንው» ትላለች ሰዓዳ። 

ኤልሳቤጥ አዱኛ ሁለት አመት በዱባይ ሰርታ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ነበር። በኢትዮጵያ በጀመረችው ሥራ የቤት ኪራይ ሲጨመርባት ተመልሳ ዱባይ ከተመች። ኮሮና ሲበረታ ግን አሰሪዎቿ ውላቸውን አቋርጠው አሰናበቷት።

«በበሽታው የተነሳ እኛ ቤት ስለሆንን ገቢ የለንም። ይኸ በሽታ እስኪረጋጋ ድረስ ሰራተኛ አንፈልግም ነው የሚሉት። ስለዚህ [ተቀጥሬ ከምሰራበት ቤት] ወጣሁ» የምትለው ኤልሳቤጥ በእጇ የነበረ የአንድ ወር ደሞዟን ይዛ በዱባይ ከተማ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ስድስት ጓደኞቿን ሰባተኛ ሆና ተቀላቀለች። «እኛ ብቻ አይደለንም። ልጆች አሉ፤ ከእኔ በፊት ሁለት ወር ሶስት ወር ሥራ ፈተው የተቀመጡ ልጆች አሉ። ብቻችንን አንበላም። የእነሱን የቤት ኪራይ እና የምግብ ወጪ መሸፈን አለብን» ስትል ለዶይቼ ቬለ አኗኗራቸውን አስረድታለች። 

"አይመሽባት" ትባል በነበረችው ዱባይ የከተሙት አስቴር፣ ኤልሳቤጥ እና ሰዓዳ ላለፉት አመታት በኖሩባት ከተማ ኮሮና ሥራ-አጥ አድርጓቸው የሰው እጅ ለማየት ሲገደዱ ለዕርዳታ ከተመዘገቡ መካከል ናቸው። አቶ መንሱር የሚመሩት ኮሚቴ በሚሰጠው ለ15 ቀናት የሚበቃ የምግብ ዕርዳታ ሕፃን፣ቤተሰብ እና የተለያየ ሕመም ያላቸው እንዲሁም የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ቅድሚያ ያገኛሉ። ኢትዮጵያውያኑ «ቁጠባቸው ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ነበር» የሚሉት አቶ መንሱር ችግሩ እየተባባሰ ሊሔድ እንደሚችል ሥጋት ገብቷቸዋል።

«ካሁን በፊት የኢሚሬትስ መንግሥት የምኅረት አዋጅ ሲያውጅ የተመዘገቡ በዱባይ እና በሰሜን ኤሚሬትስ የሚኖሩ እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች አሉ። እነዚህ ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው» ሲሉ ቁጥሩ ሊያሻቅብ እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከ7 ሺሕ ሰባት መቶ በላይ ሰዎች በኮሮና መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧልምስል፦ Getty Images/AFP/K. Sahib

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከ7 ሺሕ ሰባት መቶ በላይ ሰዎች በኮሮና መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል። 46 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአገሪቱ መንግሥት የተሕዋሲውን ሥርጭት ለመግታት ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ገቢራዊ ያደረገው ገደብ ጠበቅ ያለ ነው። እነ አስቴር እንደከዚህ ቀደሙ ከደንበኞቻቸው ለስራ የስልክ ጥሪ አይደርሳቸውም። አስቴር ከዚህ ቀደም «ስልካችንን በትነን በሱ ነው ሥራ የምናገኘው። በአሁኑ ጊዜ ስልክ የተፃፈበትን ወረቀት እንኳ አያነሱም። ስለዚህ ሥራ የሚቀጥር የለም። ኮንትራት ቤት እንገባለን ብለን እንኳ ብናስብ `እነሱ በሽታ አለባቸው` የሚል ሥጋት ስላለ ላይቀጥሩን ይችላሉ» ስትል ተናግራለች።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግሥት የከተሞች አውራ መንገዶችን በኬሚካሎች ርጭት በማጽዳት ጭምር ወረርሽኙ የሚስፋፋበትን ፍጥነት ለመቆጣጠር ጥረት ላይ ነው። ተጥለው የነበሩ ገደቦች በተወሰነ መንገድ መላላት ጀምረዋል። ይኸ ግን ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሥራ ገበታቸው የሚመልሳቸው አይደለም። አቶ መንሱር መሐመድ የመንግሥት ገደብ ከቀጠለ የኢትዮጵያውያኑ ችግር ሊበረታ እንደሚችል ያሰጋቸዋል።

«እንደ ድሮውም ባይሆን የተወሰነ የሥራ ዕድል አለ። ነገር ግን የሰው ቤት ሔዶ ለመስራት ክልከላው አለ። ቀጣሪውም የመፍራት አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ምክንያቱም ብዙ ቦታ ነው እነሱ የሚሔዱት ብዙ ቦታ በሔዱ ቁጥር የበሽታው ተጋላጭነት ከፍ ስለሚል ፤ አሰሪዎችም ቤታቸው ቁጭ ስለሚሉ ራሳቸው የማብሰል፣ የማጽዳት ነገር ይኖራል። ስለዚህ የሥራ ፍላጎቱ እየቀነሰ ይሔዳል። ስለዚህ ክልከላው በቀጠለ ቁጥር አስከፊ ይሆናል ብለን ነው የምፈራው» ብለዋል

በዱባይ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን ለዕርዳታ ተመዝግበዋልምስል፦ picture-alliance/360-Berlin/J. Knappe

ሰዓዳ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ትሻለች። አስቴር እና ኤልሳቤጥ በበኩላቸው «ምን ይዤ?» የሚል የከረመ ጥያቄ ያብከነክናቸዋል። «ኢትዮጵያም ብሆን ምን ሰርቼ ነው የምኖረው? ገብቼ ምን እሰራለሁ? ምን እበላለሁ?» ስትል አስቴር ትጠይቃለች። ኤልሳቤጥ ግን «እኔ ሁለት አመት መስራት እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ መመለስ አልፈልግም» ስትል ፈርጠም ብላ ትመልሳለች። «በጣም ከባሰ እና ግዴታ ከሆነ» መመለሷ እንደማይቀር ግን አልጠፋትም። ለአስቴር፣ ሰዓዳ፣ ኤልሳቤጥ እና በዱባይ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚኖሩ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር መመለስ እንደ ከዚህ ቀደሙ በፍላጎታቸው የሚሳካ ጉዳይ አይደለም። ከቻይና ተነስቶ ዓለምን ባቃወሰው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በረራዎች ተቋርጠዋል፤ አገራትም ድንበሮቻቸውን ዘግተዋል።

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW