1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችሱዳን

በዳርፉር ሱዳን ያገረሸው የጅምላ ግድያ እና የሴቶች ጾታዊ ጥቃት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 22 2016

በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ውስጥ ተዳፍኖ የከረመው የጎሳ ጥቃት ዳርፉር ውስጥ እንዳዲስ መቀስቀሱ እየተነገረ ነው። የሰላም ድርድሩ መክሸፉን ተከትሎም በሱዳን ተቀናቃኝ ጀነራሎች የሚመሩት ኃይሎች በዋና ከተማ ኻርቱም እና አካባቢው ሲታኮሱ መሰንበታቸው ተሰምቷል።

ፎቶ ከማኅደር ፤ የሱዳን መንግሥት ወታደሮች
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ዳግም ያገረሸው የጅምላ ግድያ እና ጥቃት ትኩረት ስቧል። ፎቶ ከማኅደር ፤ የሱዳን መንግሥት ወታደሮች ምስል AFP

በዳርፉር ያገረሸው ጥቃት

This browser does not support the audio element.

በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ውስጥ ተዳፍኖ የከረመው የጎሳ ጥቃት ዳርፉር ውስጥ እንዳዲስ መቀስቀሱ እየተነገረ ነው። በሱዳን ወታደራዊ መሪዎች በአብደል ፈታህ አልቡርሀን እና በመሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ኃይሎች መካከል ተባብሶ ውጊያ ተባብሶ መቀጠሉ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ከዚህ ቀደም በርካቶች በተጨፈጨፉባት ምዕራባዊ የሱዳን ግዛት በሴቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይፋ አድርገዋል። ሂውማን ራይትስ ዎች ዳርፉር ውስጥ የፈጥኖ ደራሽ ታጣቂዎች በያዝነው ኅዳር ወር በርካታ ሲቪሎችን መግደላቸውን በማመልከት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በተጠቀሰው አካባቢ ለሰላማዊ ዜጎች ከለላ የሚሰጥ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪውን አቅርቧል።  የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በምትገኘው አርዳማታ በተባለች መንደር ሰሞኑን ቢያንስ 800 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል። የቡድኑ ታጣቂዎች መንደሮችን መዝረፋቸውን፤ ጥቃት ማድረሳቸውን እንዲሁም በተጠቀሰችው መንደር በብዛት የሚኖሩትን የማሳሊት ማኅበረሰብ በርካታ አባላትን ማሰራቸውንም ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

ዳርፉር ውስጥ ከሰፊው ምዕራባዊ ግዛት የመንግሥት ወታደሮች መልቀቃቸውን ተከትሎ የፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች አካባቢውን መቆጣጠራቸው ነው የሚነገረው። ቀደም ሲል ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ኤል ፋሽርን በመልቀቅ የምሥራቅ ዳርፉር ዋና ከተማ የሆነችው ኤል ዳይን መያዛቸውን አስታውቀው ነበር ነበር። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የረድኤት ሠራተኞች፤ የመንግሥታቱ ድርጅት እና ምሁራን ኤል ፋሽር የጥቃት ኢላማ ልትሆን እንደምትችል ሲያስጠነቅቁ ነበር። የመብት ተሟጋቾች ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የጅምላ ግድያ መፈጸሙን የሚያመለክቱ ዘገባዎችን ይፋ አድርገዋል።

የአካባቢው የመብት ታዛቢዎች የሟቾችን ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ ያደርሱታል። ከጥቃቱ የተረፈው ባለፉት ቀናት ወደ ቻድ የተሰደዱት ስምንት ሺህ የሚሆኑት ሱዳናውያን ጎሳን መሰረት ያደረገ ግድያ፣ የጅምላ ግድያና እስራት፤ ማሰቃየት፤ ጾታዊ ጥቃት እና ዘረፋ መፈጸሙን ይናገራሉ። ሂውማን ራይትስ ዎች እንደገለጸው ታጣቂዎቹ መሣሪያ ያልያዙ የማሳሊት ጎሳ ወንዶችን ከቤተሰቦቻቸው በመለየት አሰልፈው በጥይት መምታታቸውን፤ እያቆራኙ በማሰርም እንደበደቡ ወይም እንደገደሏቸው ወደ ቻድ ተሰደው የተረፉትም ይናገራሉ። ከአርዳማት መንደር ከተሰደዱት አንዷ ናዚፋ ኢብራሂም የሆነውን ተመልክታለች።

ምዕራብ ዳርፉር ውስጥ በደረሰ ጥቃት በርካቶች ከወራት በፊትም ተገድለዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ በምዕራብ ዳርፉር ጥቃት የደረሰበት የኤል ገኒና ከተማ ገበያ ስፍራምስል Str/AFP

«ሐሙስ እና ዓርብ ዕለት የጦሩን አንድ ክፍል አመራር ተቆጣጠሩ፤ ከዚያም በሞተር ብስክሌት እና ፈረስ የመጡት ጃንጃዊዶች በየቤቱ እየገቡ፤ እጆቻቸውን ወደኋላ በማሰር ጭንቅላታቸው ላይ እየተኮሱ ሰዎችን ገደሉ። አልጋ ሥር ተደብቀን ነበር፤ ከምሽቱ አምስት ሰዓት በሸለቆው አቅርጠን ወጣን። በእሾህ ውስጥ በባዶ እግራችን መሄድ ነበረብን፤ እግርና እጆቻችን ተጎድተዋል።»

የማሳሊት ጎሳ ተዋጊ የሆነው አባ ያዚድ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ተባባሪያቸው ናቸው ያላቸው አረብ ሚሊሻዎች በመንደሩ እያደረጉ ነው ያለውን ያስረዳል።

«በአሁኑ ሰአት ወንዶችን መግደል ላይ አተኩረዋል፤ ሌላው ቀርቶ ሕጻን ወይም ትንሽ ልጅም ቢሆን። አርዳማታ ላይ እየተደረገ ያለው ይህ ነው። ሴቶቹን ልጆች በተመለከተ፤ አንዳንዶቹን ይደፍራሉ አንዳንዶቹን ይተዋሉ፤ ወይም በዋናነት ወንዶቹን ይገድላሉ፤ የጅምላ ግድያ ማለት ነው። ወንዶቹን ትላልቅ መኪናዎች ላይ ይጭናሉ፤ ለወጣቶቹ ወንዶች እንዳይሰጉ፤ ሊሸኟቸው መሆኑን ይነግሯቸዋል። ወንዶቹ ልጆቹ መኪናው ውስጥ ሲገቡ፤ እየተኮሱ ሁሉንም ይገድላሉ፤ የጅምላ ግድያ ነው፤ ያ ነው የተደረገው።»

ከማሳሊት ጎሳ መሪዎች አንዱ አልኑር መሀመድ አህመድ ወደ ቻድ ስለተሰደዱት የሱዳን ወታደሮች እና የጎሳቸው ተዋጊዎች ቁጥር ትክክለኛው መረጃ ገና በእጃቸው እንደሌነ ነው የተናገሩት።

«እስካሁን ከእኛ ኃይሎች የተረፉትን ትክክለኛ ቁጥር አናውቅም። በየማለዳው እነሱን ለመመልከት እንመጣለን። እስካሁን ከ10 ሺህዎቹ መካከል እዚህ ያሉት 340 ብቻ ናቸው። የተቀሩት የት እንደደረሱ እስከዛሬ ማወቅ አልቻልንም።»

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የዳርፉርን ሰላማዊ ነዋሪዎች ከጥቃት እንዲከላከል ጠይቋል። ፎቶ ከማኅደር፤ የሂውማን ራይትስ ዎች አርማምስል John MacDougall/AFP/Getty Images

ሱዳንተቀናቃኝ ጀነራሎች የሚመሩት ኃይሎች በዋና ከተማ ኻርቱም ውስጥ ከአባይ ወንዝ ማዶ በዚህ ሳምንትም ሲታኮሱ መሰንበታቸውን እማኞች ይገልጻሉ። ኦምዱርማን የሚገኘው የመንግሥት ጦርም እንዲሁ በፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች ላይ ሮኬትና ከባድ መሣሪዎችን ባሕሩን አሻግሮ መተኮሱንም አመልክተዋል። የሁለቱን የሱዳን ኃይሎች መሪዎች ለማሸማገል በዩናይትድ ስቴትስ እና በሳውድ አረቢያ የተሞከረው ጥረት በያዝነው ወር ከከሸፈ በኋላ ተቀናቃኞቹ ኃይሎች አንዱ የያዘውን ስፍራ ሌላው ለማስለቀቅ ፍልሚያ ቀጥለዋል። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በዋና ከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል ስልታዊ ያለው ስፍራ ላይ ከባድ ጥቃት ማድረሱን ገልጿል። በምዕራብ ኮርዶፋን የነዳጅ ክምችቱ አካባቢ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ሙግላድ የተባለችውን ከተማ የመንግሥት ኃይሎች ለቅቀው መውጣታቸውን እማኞች ለዘጋቢዎች ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የአንድ ከፍተኛ የሱዳን ጀነራል የተባበረው አረብ ኤሜሬት ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል የጦር መሣሪያ እያቀረበች ነው በሚል ከሰዋል። ጀነራል ያሲር አል አታ ለስለላ አገልግሎት አባላት ባደረጉት ንግግር አረብ አሜሬት ለቡድኑ በአውሮፕላን ድጋፍ መላኳን የሚያስረዳ መረጃ ከወታደራዊ የስለላ ተቋም፤ እንዲሁም ከዲፕሎማቶች ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል። አረብ ኤሜሬት በበኩሏ ሱዳን ውስጥ ግጭቱ እንዲቆምና ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ መጠየቋን ገልጻለች። በምዕራብ ዳርፉር ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው የአረብ ሚሊሻዎች የተቀዳ መሆኑ የሚነገርለት ፈጥኖ ደራሹ ኃይል የሱዳን ጦር ዳርፉር ውስጥ አማጽያንን ለማስወገድ ሲንቀሳቀስ ማገዙ ይነገራል። በጎርጎሪዮሳዊው 2000 ዓ,ም የተፈጸመው ጥፋት ተጠያቂዎች ለሕግ ባልቀረቡበት ዳርፉር አሁን ያገረሸው አዲስ ጥቃት ትኩረት ስቧል።

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW