1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በዳሰነች ወረዳ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2018

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዳሰነች ወረዳ መስተዳድር ለሁለተኛ ጊዜ የህዝብ እንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን አስታወቀ። መስተዳድሩ ገደቡን የጣለው በማርበርግ ቫይረስ የአንድ ሰው ህይወት ማለፍን ተከትሎ ነው። ከወረዳው የሚወጡና የሚገቡ የህዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ተቋርጧል፤ መጠጥ ቤቶች፣ መዝናኛን ጨምሮ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች ተዘግተዋል።

የማርቡርግ ተዋህሲን ተከትሎ በዳሰነች ወረዳ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ
የማርቡርግ ተዋህሲን ተከትሎ በዳሰነች ወረዳ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብምስል፦ The Dasanech district administration in the Southern Ethiopian region via Shewangizaw Wegayehu/DW

በዳሰነች ወረዳ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዳሰነች ወረዳ መስተዳድር ለሁለተኛ ጊዜ የህዝብ እንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን አስታወቀ ፡፡ መስተዳድሩ ከትናንት እሁድ ጀምሮ የእንቅስቃሴ ገደቡን የጣለው በማርበርግ ቫይረስ በሽታ  የአንድ ሰው ህይወት ማለፍን የጤና ሚንስቴር ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ማስታወቁን ተከትሎ ነው ፡፡ አሁን ላይ ከወረዳው የሚወጡና የሚገቡ የህዝብ መጓጓዣ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን መጠጥ ቤቶች ፣  መዝናኛዎችና የእግር ኳስ ማሳያ ቤቶችን ጨምሮ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች ተዘግተዋል። 

በሽታው ዳግም ያሳደረው ሥጋት

የእንቅስቃሴ እገዳውን መጣል ያሥፈለገው በወረዳው በበሽታወ የሞት ሪፖርት በመመዝገቡ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና የፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ዑመር ነኩኤል ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ ከሟቹ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን በመለየት ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ዑመር “ በወረዳው በሽታው የቀነሰ መስሎ ዳግም በመታየቱ ጊዜያዊ የእንቅስቃሴ እገዳ መጣል አሥፍላጊ ሆኗል ፡፡ በእኛ በኩል በቀጣይ ቀናት ሁኔታውን እያየን እንሄዳለን የሚል አቅጣጫ ነው ያስቀመጥነው “ ብለዋል ፡፡

የወረዳው ነዋሪዎች ምን ይላሉ ? 

ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የወረዳው ነዋሪዎች በአካባቢው አሁንም የበሽታው ሥጋት ቢኖርም በሥጋቱ ልክ ግን ጥንቃቄ ሲያደረግ አይታይም ይላሉ። ህዝቡ አሁንም በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ  ንክኪ ባለው ሀኔታ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደሚስተዋል የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ “ ሦስትና አራት ሆነው በባለ ሁለት እግር ሞተር እየተገለገሉ የሚገኙ አሉ ፡፡ እገዳው ብዙም ለውጥ ያመጣል ሚል ተስፋ አይታየንም ፡፡ ከዛ ይልቅ ክትባት የሚገኝበት ሁኔታ ቢኖር የተሻለ ይመስለናል  “ ብለዋል። 

የተቋሙ ጥሪ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቀውስ ክስተት አስተዳደር በሽታው የሚገኝበትን ሁኔታ ገምግሟል። በህብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋት እንደሚስተዋል የገለጹት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ተቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት መልካ መንግሥት በሽታውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን እስከሚገልጽ ጥንቃቄ እንዳይለየው ሲሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ ዶ/ር ቴዮድሮስ አድኃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር - በሩዋንዳ የተቀሰቀሰ የማርቡርግ ተዋህሲን ተከትሎ ኪጋሊ ላይ መግለጫ ሲሰጡ -20.10.2024ምስል፦ Jean Bizimana/REUTERS

ማርበርግ ቫይረስ ባለፈው የህዳር ወር መግቢያ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ መከሰቱን የጤና ሚንስቴር መግለጹ ይታወቃል። እስከ ትናንት ታህሳስ 5 2018 ዓም በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ አሥራ አራት ሰዎች መካከል የዘጠኙ ሕይወት ሲያልፍ አምስቱ በህክምና ዕርዳታ አንዲያገግሙ መደረጉን ሚንስቴሩ በበሽታው የዕለታዊ ሁኔታው መግለጫው አመልክቷል። 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW