በጀርመን ምርጫ ሶሻል ዴሞክራቶች በጠባብ ውጤት አሸነፉ
ሰኞ፣ መስከረም 17 2014በጀርመን የምክር ቤት ምርጫ ይፋ ጊዜያዊ ውጤት መሠረት የመሀል ግራው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በጠባብ ውጤት አሸንፏል። የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምርጫ ከተሰጡ ድምጾች 25.7 በመቶ አግኝቷል። ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት (CDU) እና የክርቲያን ሶሻል ኅብረት (CSU) ጥምረት 24.1 በመቶ ድምጽ አግኝቷል።
ለአካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆረው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ (Greens) 14.8 በመቶ እንዲሁም ነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ (FDP) 11.5 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።
መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ለመተካት የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በእጩነት ያቀረባቸው ኦላፍ ሾልዝ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ አዲስ የሚመሠረተውን መንግሥት የመምራት ሥልጣን እንዳላቸው ዛሬ ሰኞ ተናግረዋል። ኦላፍ ሾልዝ ከአረንጓዴዎቹ እና ነጻ ዴሞክራቶች ጋር ጥምር መንግሥት መመሥረት እንደሚፈልጉም ጥቆማ ሰጥተዋል።
"መራጮች በግልጽ ተናግረዋል። ማን የሚቀጥለውን መንግሥት መመሥረት እንዳለበት ተናግረዋል" ያሉት ኦላፍ ሾልዝ በምርጫው ውጤት መሠረት ድምጽ ሰጪዎች ሶሻል ዴሞራቶች፣ አረንጓዴዎቹ እና ነጻ ዴሞክራቶች መንግሥት እንዲመሠርቱ ኃላፊነት እንደሰጡ አስረድተዋል።
የ63 አመቱ ኦላፍ ሾልዝ ተሳክቶላቸው ጥምር መንግሥት ከመሰረቱ በአንጌላ ሜርክል ካቢኔ ውስጥ የፋይናንስ ምኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት እና የቀድሞው የሐምቡርግ ከተማ ከንቲባ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንን የሚመሩ አራተኛው የሶሻል ዴሞክራት መራሔ-መንግሥት ይሆናሉ።
የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል አስተዳደርን የሚተካውን ጥምር መንግሥት ታኅሳስ 16 ከሚከበረው የምዕራባውያኑ የገና በዓል በፊት ለመመስረት ተስፋ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።
በታሪኩ የከፋ ውጤት የገጠመው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት (CDU) እጩ መራሔ-መንግሥት አርሚን ላሼት ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጡም። ላሼት "መራጮች የሚሰራውን ሥራ ሰጥተውናል። ምን አልባት በሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የጋራ ነገሮች ማግኘት አለብን" በማለት ተናግረዋል።
ጥምር መንግሥት ለመመሥረት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ድርድር ሳምንታት ምንአልባትም ወራት ሊወስድ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ከተካሔደው ምርጫ በኋላ ነጻ ዴሞክራቶች አንጌላ ሜርክል ከሚመሩት ፓርቲ እና ከአረንጓዴዎቹ ጋር ተጀምሮ የነበረ ድርድር ረግጠው በመውጣታቸው ጥምር መንግሥት የመመሥረቱ ሒደት ስድስት ወራት ፈጅቷል። መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል አዲሱ ጥምር መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ በሥልጣን ይቆያሉ።