1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እውነትን ማጣራት ፦ የሩስያ ተጽእኖ በጀርመን ምርጫ

ዓርብ፣ የካቲት 14 2017

የሩስያ ግቦች ከሁሉም በላይ አለመረጋጋትን ማሰፋፋትናና መራጮች ጽንፍ እንዲይዙ ማድረግ መሆኑን የሀሰት መረጃዎችን መታገያ መሣሪያዎችን የሚያቀርበው ኒውስጋርድ ባልደረባ ሊዮኒ ፋለር ለBR ተናግረዋል። ስለቀኝ ጽንፈኛው የአማራጭ ለጀርመን AFD እና ስለፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ አሊስ ቫይድል የሚወጡ ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ አዎንታዊ ናቸው።

 የሩሲያ የተሳሳተ መረጃ ተፅእኖ በጀርመን ምርጫ ማሳያ
የሩሲያ የተሳሳተ መረጃ ተፅእኖ በጀርመን ምርጫ ማሳያምስል፦ Christian Ohde/picture alliance

ሩስያ በተሳሳተ መረጃ በምርጫ ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ስትሞክር የመጀመሪያዋ አይደለም። ይህ ለምሳሌ በጎርጎሮሳዊው 2024ቱ የአሜሪካን ምርጫና በአውሮጳ ምርጫዎችም የደረሰ ነው። የጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ እንደሚለው የዛሬ ሦስት ዓመት በጀርመን በተካሄደው ምርጫ ላይም ጫና ለማድረግ ሞክራለች። ከአራት ዓመት በኋላ ዘንድሮም የተለየ ነገር የለም። የመስኩ ባለሞያዎች እንደሚሉት በመጪው ጎርጎሮሳዊው  የካትት 23 ቀን በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ላይ  ሩስያ በተለይ የመሀል አቋም ያላቸውን ፓርቲዎች በማሳጣት ተጽእኖ በማሳደር መጠነ-ሰፊ የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ዘመቻ ለማካሄድ ሞክራለች ።

አብዛኛዎቹ የሀሰት መረጃዎችም በአረንጓዴዎቹ ፓርቲ በክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና በሶሻል ዴሞክራት ፓርቲዎች ላይ በቀጥታ ያነጣጠሩ ነበሩ። ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ በነዚህ መሰል ስም ማጥፋቶች ላይ አይጠቀስም። ከተጠቀሰም በበጎ መሆኑን ከዶቼቬለ የክትትል፣ የትንተናና እና ስልት ማዕከል በምህጻሩ (CeMAS) ባልደረባ ሊያ ፍሩቪርትዝ አስረድተዋል። አትራፊ ያልሆነው ይኽው ማዕከል በሴራ አስተሳሰብ ፣ በጸረ-ሴማዊነትና በቀኝ አክራሪነት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።

የሀሰት ዘገባዎች የሆኑ ዋና ዋናዎቹ እጩ ተወዳዳሪዎች

ከቅርብ ጊዜ ምሳሌዎች ውስጥ ሁለቱን ስንመለከት በርካታ የ X ወይም የቀድሞው ትዊተር  ተጠቃሚዎች ካየካትት መጀመሪያ አንስቶ የCDUው እጩ መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ የአዕምሮ ህመም አለባቸው የሚል ቪድዮ ሲያጋሩ ነበር ።  ከቪድዮው አንዱ ሜርስ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም ራሳቸውን  ለማጥፋት ሞከረው ነበር የሚለው ነው። ከተጋሩት ቪድዮዎች አንዱም በ10 ቀናት ውስጥ ከ5.4 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል።

እውነቱን ማጣራት፦ የሩስያ ተጽእኖ በጀርመን ምርጫ ምስል፦ w-a-munchen

እንደ ማስረጃ የቀረቡትም የስነ ልቦና ሐኪም ናቸው የተባሉ አልበርት ሜርትንስ እና አንድ የህክምና ማዕከል ነው። የጀርመን የስነ ልቦና ሐኪሞች ምክር ቤት አልበርት ሜርትንስ በሚል ስም በተለይ በኖርድራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የተመዘገበ ሰው የለም ሲል ለዶቼቬለ አረጋግጧል። 

በቪድዮው ላይ በሚታየው አድራሻም የተጠቀሱት ሰው ይሰሩበታል የተባለ ክሊኒክ አልተገኘም። ቪድዮ በመጀመሪያ ቮኽንኡበርብሊክ አውስ ሙንሽን በተባለው ድረ ገጽ ላይ ነበር የወጣው ቪድዮ ለሌላ ሰው ሲጋራ ሜርስ ታውሩስ ሚሳይል ለዩክሬን እንዲሰጥ ጥሪ ሲያቀርቡ በተደጋጋሚ ይጠቁማል።

በቅርቡ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጩ መራኄ መንግሥት ሮበርት ሀቤክ እና የፓርቲያቸው አባል ክላውዲያ ሮት የሀሰት መረጃ ሰለባ ሆነው ነበር። ናሬቲቭ በተባለ ድረ-ገጽ ላይ ሁለቱ ፖለቲከኞች 100 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ በወጣበት የሙስና ቅሌት ተካፍለዋል የሚል ጽሁፍና ቪድዮ ወጥቶ ነበር ። መረጃው ወደ ዩክሬን የተወሰዱ የፐርሽያ የባህል ቅርስ ድርጅት ስዕሎችን ይመለከታል። ስለጉዳዩ የተጠየቀው የፐርሽያ የባህላዊ ቅርስ ድርጅት በዘገባው የቀረቡት ውንጀላዎች በሙሉ ሀሰት ወይም ሙሉ በሙሉ የፈጠራም ናቸው ብሏል።

ዘገባዎቹ የተሰናዱት የሀሰት ምስክሮች በሰጡት መግለጫና በተጭበረበሩ ሰነዶች ነው። መጀመሪያ የወጡትም ዜና ማሰራጫ መድረኮች በመሰሉ ነገር ግን የተሳሳተ መረጃ በሚነዙ ድረ ገጾች ነው። መሰል ዘገባዎች ስቶርም-1516 በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው የሩስያ የሀሰት መረጃ ዘመቻ ላይ የሚወጡት ዓይነት ዘገባዎች መሆናቸውን ግኒዳ የተባለው በድረ-ገጽ ምርምር የሚያካሂደው ፕሮጀክት ባልደረባ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

እውነቱን ማጣራት፦ የሩስያ ተጽእኖ በጀርመን ምርጫምስል፦ nrtv.online

ዘመቻዎቹ፦ ዶፕልጌንገር ማትርዮሽካ እና ስትሮም-1516

ኮሬክቲቭ እና ኒውስጋርድ በተባሉት መድረኮች ትብብር የዶቼቬለ የምርመራ ፕሮጀክት በሰው ሰራሽ አስተውሎት  የተሰሩ ሩስያን በሚደግፉ ይዘቶች የተሞሉ ከ100 በላይ የጀርመንኛ ቋንቋ ድረ ገጾች እንዳሉ አረጋግጧል። እነዚህ ድረ-ገጾችም ጥቂት ቆይተው የሀሰት ዘገባዎች ማቅረቢያ ይሆናሉ

እነዚህ መረጃዎችም ኤክስና ቴሌግራምን በመሳሰሉ የወዳጆች ወይም የተጽእኖ ፈጣሪዎች ገጾች ይሰራጫሉ። ዶፕልጌንገር የተባለው ዘመቻ የሚሰራውም በተመሳሳይ መንገድ ነው። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሩስያ ዩክሬንን ከወረረችበት ከጎርጎሮሳዊው 2022 በኋላ በዚህ ዘመቻ  በተለይ የምዕራባውያን ፖሊሲዎችንና በአጠቃላይ ለዩክሬን የሚሰጠውን ድጋፍ የሚያጣጥሉ የሀሰት መረጃዎችና  ፣ መፍቅሬ ሩስያ ትርክቶች ሲሰራጩ ቆይተዋል። ሩስያ በዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ጣልቃ ከገባች በኋላ ለዚህ ተጠያቂ የተባሉት የሩስያ ተዋናዮች ላይ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ማዕቀብ ጥሏል። ዘመቻው "doppelgänger" የሚለውን ስም ያገኘው ከመነሻው ድረ ገጾችንና ቪድዮዎችን የታዋቂዎቹ መገናኛ ብዙሀን የDW እና የBBC አስመስሎ በማቅረቡ ነው። 

ጉዳዩን የሚያጣራው የዶቼቬለ ቡድን በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት የማይባሉ እውነቱን የማረጋገጥ ስራዎችን ሰርቷል።አንዳንዶቹ የሀሰት መረጃዎች ወዲያውኑ ይታወቃሉ። ብዛት እንጂ ጥራት የላቸውም ትላለች CeMAS የተባለው እውነቱን የሚያጣራው የባቫርያ መገናኛ ብዙሀን የBRዋ ሊያ ፍርዩቪርስ።ማትርዮሽካ የሚባለው ዘመቻም የሚጫወተው ሚና አለው። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው የቦቶች ሠራዊት አቅጣጫ የሚያስቱ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፣ጋዜጠኞች እንዲያጣሯቸው በሚሰራጭላቸው የሀሰት መረጃዎች ይጨናነቃሉ። በዚህ መንገድ እውነታውን የሚያጣሩት በስራ እና በዘገባዎች ይጠመዳሉ።  የማትርዮሽካ ቦቶች በጥቂት ቀናት ውስጥ ቢያንስ 15 የሀሰት ቪድዮዎችን ከጥር መጨረሻ ጥቂት ቀናት በፊት  እንዳሰራጩ ገለልተኛ መሆኑ የተጠቀሰው የሩስያ የመገናኛና ብዙሀን ፕሮጀክት አገንትስቱ ጽፏል።ለምሳሌ  እነዚህ ቪድዮዎች ዶቼቬለ እና የጀርመኑ ቢልድ ካወጣቸው ጋር  ተመሳሳይ ነበሩ።

በእንግሊዘኛ በፈረንሳይኛ እና በስፓኝ ቋንቋዎች የሚወጡ ዘገባዎች ጀርመን ከሽብር ፣ እየጨመረ ከመጣ ወንጀል፣ እና የመራጮች ፍርሀት ስጋት ጋር እየታገለች ነው ይላሉ።

እውነታውን ማጣራት፦ የሩስያ ተጽእኖ በጀርመን ምርጫምስል፦ x.com

ሩስያ በተለይ ሁለት ፓርቲዎችን ትደግፋለች

የሩስያ ግቦች ከሁሉም በላይ አለመረጋጋትን ማሰፋፋትና እና መራጮች ጽንፍ እንዲይዙ ማድረግ መሆኑን የሀሰት መረጃዎችን መታገያ መሣሪያዎችን የሚያቀርበው ኒውስጋርድ የተባለው መስሪያ ቤት ባልደረባ ሊዮኒ ፋለር ለBR በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ስለቀኝ ጽንፈኛው የአማራጭ ለጀርመን AFD እና ስለፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ አሊስ ቫይድል የሚወጡ ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ አዎንታዊ ናቸው። 

የነዚህ ዘመቻዎች ዓላማ AFD የሚያገኘው ድምጽ ቢያንስ ሀያ በመቶ እንዲደርስ ማድረግ ነው። በቅርብ ጊዜዎቹ የአስተያየት መመዘኛዎች ፓርቲው ከአጠቃላዩ ምርጫ በፊት ያለው የህዝብ ድጋፍ 20 በመቶ ገደማ ነው። ይህ ከዘመቻው ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ግን ማረጋገጥ አልተቻለም። ፋለር  AFD በሩስያ ይደገፋል ብለው ይጠረጥራሉ። እርሳቸው እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ከሌሎች ይልቅ ከሩስያ ጋር ይበልጥ ወዳጅ መሆኑን ነው። ፓርቲው ለምርጫ ባዘጋጀው ማኒፌስቶ የምርጫ መመሪያ በሩስያ ላይ የተጣለው የኤኮኖሚ ማዕቀብ እንዲነሳ ጥሪ ያቀርባል። ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው በዩክሬን ላይ የሚካሄደውን ጦርነትም አያወግዝም።  

የCeMASዋ ሊያ ፍሩቪርትስ በሩስያ ፕሮፓጋንዳ የሚደገፍ ሌላ የጀርመን ፓርቲም አለ ይላሉ። ይኽውም የሳራ ቫግን ክኔሽት ኅብረት በምህፃሩ BSW የተባለው ፓርቲ ነው። የፓርቲው የምርጫ መመሪያ  የዩክሬኑን ጦርነት ሊቆም የሚችል የሩስያ እና የዩናይትድ ስቴትስ የእጅ አዙር ጦርነት ይለዋል። BSW ጀርመን ከሩስያ እንደገና የተፈጥሮ ጋዝ ማግኘት መቻል አለባት ይላል። ሜርካተር  የተባለው ድርጅት ባልደረባ ፌሊክስ እንደተናገሩት በነዚህ የሀሰት መረጃ የማሰራጨት ዘመቻዎች ከጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ይልቅ የሩስያ ዘላቂ ስልት ነው ለአደጋ የሚጋለጠው ።ክሬምሊን ለዓመትት ስታስተጋባ የቆየችው የወረራ ትርክት የጀርመን ህዝብ ሲከራከርበት የቆየ ጉዳይ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

በአውሮፓ የሚገኙ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎችም የአውሮጳ መንግሥታት በሙሉ ሙሰኛ ናቸው የንግግር ነጻነትን ይጨቁናሉ የሚሉ ትርክቶችን ያሰራጫሉ። ሆኖም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ የሚኒስቴሩ የስራ ቡድን እነዚህን መሰል የሀሰት መረጃዎችን ስጋት ለመቀነስ እንደሚሰራ መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።  ትኩረቱም ኅብረተሰቡን ስለሀሰተኛ መረጃ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ስለዜና እና መገናኛ ብዙሀን ለማሳወቅ  እየተሰራ ነው ሲል ሚኒስቴሩ ከBR ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የሩስያን የሀሰት መረጃ ለመከላከል ከሌሎች መንግሥታትና ማኅበራዊ ትስስሮች ጋር በጋራ እየሰራ ነው። የዲጂታል ኤክስፐርት ለሆኑት ለፌሊክስ ካርተ የሀሰት መረጃዎች ለመከላከል እውነታውን ማሳወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ፖለቲካው ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ ስሜታዊ ፍላጎቶች እውቅና መስጠት አለበት። በአጭሩ «የተሻለ ፖለቲካ ስሩ» ብለዋል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW