በጀርመን ምርጫ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት
እሑድ፣ የካቲት 16 2017
ኤለን መስክ እና የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ዛሬ እየተደረገ ባለው የጀርመን ምርጫ ላይ ጫና ለመፍጠር ግልጽ ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዋል። ልክ እንደሃገራቸው ሁሉ ጀርመንና የአውሮፓ ሃገራት ወደ ፅንፈኛና ቀኝ ዘመም እሳቤወች እንዲያመሩ የሚያደርጉትን ጥረት፣ በግልጽ ለጀርመን አማራጭ ፓርቲ (ኤኤፍዲ) ባደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ እና ቅስቀሳ አስመስክረዋል። የጀርመን የፖለቲካ መሪወች ግን የጀርመንን እጣ ፈንታ የሚወስነው የጀርመን ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል። የኤለን መስክና የም/ል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የፖለቲካ ድጋፍና ጣልቃ ገብነትም አግባብ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ጀርመናውያን ወሳኝ ለሆነው ሀገራዊ ምርጫ ወደ ድምጽ መስጫ ጣምያወች እያመሩ ነው። ይሄ ምርጫ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ባልተለመደ መንገድ ከወደ አሜሪካ፣ ከኤለን መስክ በመጣ ተጸዕኖ ስር ወድቋል።
ቢሊዮነሩ የቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ኤለን መስክ ከንግዱ ዓለም አልፎ በቀጥታ ወደ ፖለቲካዊ ጡንቻነት ተሸጋግሯል። መስክ በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ያለው ተፅዕኖ ቀናት ባስቆጠረው የትራምፕ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የቀኝ አክራሪ እንቅስቃሴወችና አጀንዳወች ነፍስ ዘርተው እንዲንቀሳቀሱ ከሚሰሩ ሰዎች ውስጥ ቀዳሚው ኤለን መስክ ነው። የመንግስትን አስተዳደር ቀልጣፋና፣ ውጤታማ ማድረግ በሚል መርህ፣ የመንግስት ተቋማትን ማጠፍና መዝጋት፣ በርካታ ሰራተኞችን ማባረርና፣ አላስፈላጊ ያላቸውን የመንግስት ወጪወች ማስቆምን በከፍተኛ ፍጥነትና ስፋት ተያይዞታል።እውነትን ማጣራት ፦ የሩስያ ተጽእኖ በጀርመን ምርጫ
ይሂው የመስክ የፖለቲካ ተጽዕኖ በኋይት ሃውስ ብቻ አልተወሰነም። የዚሁ የፖለቲካ እምነቱ ነጸብራቅ ፍንትው ብሎ የተጫናት ሌላ ሃገር ደግሞ ጀርመን ሆናለች። ዛሬ በሚደረገው የጀርመን ምርጫ ላይ የጀርመኑ ቀኝ አክራሪ የጀርመን አማራጭ ፓርቲ (AfD)ን እንዲመረጥ በግልጽና በተደጋጋሚ ድጋፉን አሰምቷል። በቅርቡም በፓርቲው ዝግጅት ላይ ባስተላለፈው መልዕክት ኤኤፍዲ ፓርቲን የጀርመን ምርጥ ተስፋ በማለት አወድሷል።
አያይዞም የኤኤፍዲ ፓርቲ መሪ አሊስ ቫይደልን ምክንያታዊ መሪ ሲል ያወደሰ ሲሆን ይዘው የቀረቡት አጀንዳም ያን ያህል የሚያከራክር አለመሆኑን ተናግሯል።
ኤለን መስክ ይሄን ውዳሴና ድጋፍ ያደረገው ደግሞ ፓርቲው ከህዝብ በተሰበሰበ አስተያየት እያገኘ ያለው ድጋፍ እያደገ፣ ከሌሎች ፓርቲወች ጋ ሲነጻጸርም በሁለተኛ ደረጃ ላይ በተቀመጠበት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ ፓርቲው ባለው ጽንፈኛ አቋም ምክንያት አብሮት ሊሰራ ፈቃደኛ የሆነ ፓርት ባለመኖሩ ቢያሸንፍ እንኳን መንግስት የመመስረት እድሉ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገባ ነው የተነገረው።
የተፎካካሪው የክርስቲያን ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ሲዲዩ) ፓርቲ መሪ ፍሬድሪኽ ሜርትስ ፓርቲያቸው በምንም መልኩ ከኤኤፍዲ ፓርቲ ጋ እንደማይሰራ ተናግረዋል። ፍሬድሪኽ ሜርትስ አያይዘውም ኤለን መስክ ለኤኤፍዲ የሰጠው ድጋፍ እንደ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ሊመረመር ፣ ኤለን መስክም በጀርመን ምርጫ ውስጥ እጁን በማስገባቱ ሊጠየቅ ይገባል ብለዋል።
ኤለን መስክ ግን በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ጽንፈኛ ፓርቲ በመደገፍም አላበቃም። በሃገሪቷም ሆነ በአለም ታሪክ ውስጥ የማይሸር ጠባሳ ጥሎ ያለፈውን የናዚ ስርዓት በተመለከተ የጥፋተኝነት ስሜት ሊኖር አይገባም ብሏል።
ይሄው የኤለን መስክ መለዕክት ከያለበት በጣም ከፍተኛ የተቃውሞና የቅሬታ ምላሽን አስተናግዷል። በተለይም የናዚ ጭፍጨፋ ሰለባወች መታሰብያ ማዕከል ያድ ቫሸም ሊቀመንበር ይህን አይነቱ መለዕክት “የናዚ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ስድብ እና ለጀርመን ዴሞክራሲ ግልፅ የሆነ አደጋ” ሲሉ ኮንነውታል።
የኤለን መስክ የቀኝ ዘመም አክራሪወች ድጋፍ በጀርመን ብቻ የተገደበም አይደለም። በሌሎች አለም አቀፍ ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ውስጥም ድምጹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። አክራሪና፣ ቀኝ ዘመም የሆኑት የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጃ ሜሎ፟ኒ አድናቂ ነው።
የእንግሊዙን ቀኝ ዘመም ብሔራዊ ተሐድሶ ፓርቲን ጨምሮ በመላው አውሮፓ የሚገኙ ጽንፈኛ ቀኝ ፓርቲ መሪዎችም ዋና ደጋፊ ነው። በአሜሪካም መስክ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር ተሰልፎ ጽንፈኛ የሚባሉ ስደተኞችን የማባረር፣ ከአለማቀፋዊ ህብረት ይልቅ ቅድሚያ ለአሜሪካ የሚል መርህን ማስፈጸምና፣ በንግድና ቴክኖሎጂ ላይ የመንግስት ቁጥጥርን የመቀልበስ እርምጃወችን እየፈጸመም እያስፈጸመም ይገኛል።ስጋትና ተስፋ ያንዣበበት የጀርመን ምርጫ
ጠንካራ የብሄራዊ አቋም የሚጋሩት ምክትል ፕሬዚደንት ጄዲ ቫንስም የአውሮጳን የቀኝ ክንፍ እንቅስቃሴና አጀንዳወች ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው። ሙኒክ ውስጥ ባደረጉት ንግግር የቀኝ ዘመሙን ፓርቲ በስም ሳይጠሩ፣ ድጋፋቸውን መግለጽ ብቻ ሳይሆን በእንደዚህ አይነት ጽንፈኛ አቋም ባላቸው ግለሰቦች እና ፓርቲወች ላይ የሚደረግ ጫናም ሊቆም ይገባል ብለው ነበር።
ከትላንት በስቲያ እዚህ አሜሪካ ውስጥ ለአክራሪ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በተዘጋጀ መድረክ ላይ ይህንኑ ሃሳባቸውን አጠናክረው ደግመውታል። ም/ል ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ንግግራቸው የጀርመንን የመናገር መብት ህግ የተቹ ሲሆን፣ በተለይ የናዚ ጭፍች=ጨፋን የሚክዱና የናዚን ዘመን የሚያወድሱ ንግግሮች ላይ የተደረጉት ገደቦች አግባብ አይደሉም ብለዋል።
የጋራ እሴታችን ያሏቸውን ኘትቦች ካልተስተካከሉ በአሜሪካ ግብር ከፋይ የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ ዳግም ሊጤን የሚገባበት ሁኔታ ሊፈተር እንደሚችል ጭምር ነው የገለጹጥ
የትራምፕ፣ የጄዲ ቫንስም ሆነ የኤለን መስክ ትልምና ምኞታቸው፣ እነሱ አሜሪካ ከሁሉም በፊት እንዳሉት ሁሉ፣ ጀርመንን የሚያስቀድም የፖለቲካ አቅጣጫ ጀርመን ውስጥ መስመር ይዞ ማየት ነው።
የዛሬው የጀርመን የምርጫ ውጤት አውሮፓ በዚሁ የትራምፗ አሜሪካ አቅጣጫ የመጓዝ ያለመጓዟን እጣ ፈንታ ከወዲሁ እንደሚያመላክት ይጠበቃል። የኤኤፍ ዲ ፓርቲ የበለጠ እየተጠናከረ መምጣት ከቻለ፣ የጀርመንን አሁናዊ የመንግስት አስተዳደርና መርህ መገዳደር ብቻ ሳይሆን ጀርመን፣ ከኔቶና ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ጋር ያላትን ኝንኙነትም ሊያሻክረው ይችላል።
በቀድሞ ስሙ ትዊተር፣ በአዲሱ ስሙ ኤክስ በመባል የሚታወቀው የመስክ ማህበራዊ ገጽ በጀርመን ምርጫ ውስጥ ጫና ለመFጠር ጥቅም ላይ ከዋሉት መሳያወች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይነገራል። በጀርመን ፍርድ ቤት ከምርጫ ጋ የተያያዘ የተሳሳተ መረጃን ከማሰራጨት ጋ ለሚደረገው ምርመራ፣ ኤክስ ያሉትን መረጃወች በሙሉ እንዲያስረክብ ከታዘዘ ወዲህ፣ የብዙሃኑን ቀልብ ስቧል። የመስክ ተቃዋሚወች ትልቅ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት መሆኑ በጀርመንም ሆነ በሌሎች አለማቀፍ ፖለቲካዊ እውነታወች ላይ ከፍተኛ ጫናን የመፍጠር አቅም አጎናጽፎታል ይላሉ።
የጀርመኑ መራሂ መንግስት ኦላፍ ሾልትስ ግን የሃገራቸው ምርጫና የወደፊት እጣ ፈንታ በአንድ የማህበራዊ ድረገጽ ባለቤት ሳይሆን በጀርመን ህዝብ የሚወሰን ነው ባይ ናቸው።
እናም ዛሬ ጀርመናውያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን የሚሰጡበት ምርጫ ከወትሮው የተለየ ትኩረትን የሳበ፣ የሃገሪቷን ነገ በመውሰኑ ረገድም ወስኝ ሚና እንደሚኖረው ነው የሚጠበቀው። የዛሬው ምርጫ የAfD ግስጋሴ ወደ ተጨባጭ ድልና ስልጣን ተመንዝሮ፣ የምእራቡ አለም፣ ኤለን መስክንና ትራምፕን ተከትሎ አሰላለፉን ወደ ቀኝ የሚያደርግበት ይሁን ወይስ ይሄንኑ ጽንፈኝነት አይንህ ላፈር ብሎ የምያወላዳ ምላሽ የሚሰጥበት?
አበበ ፈለቀ
ኂሩት መለሰ