በጀርመን ድርጅት የሚደገፈዉ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ታካሚዎች
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2015
ሰሞኑን በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የነበረባቸው ወገኖች ከህክምናው በኋላ የዓይን ብርሀናቸው በመመለሱ ደስታቸውን እገለፁ ነው፣ የታካሚው ቁጥር ከታሰበው በላይ በመጨመሩ የህክምና ጊዜው ሊራዘም እንደሚችል ሀኪሞቹ ተናግረዋል፡፡ የዓይን ሞራ ችግር በተለይ አብዛኛውን የገጠር ነዋሪ እንደሚያጠቃ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፣ ችግሩ ከእድሜ መግፋት ጋር የተያያዘ ነው ቢባልምየስኳር ህመምና የአንዳንድ መድኃኒቶች ተፅዕኖ እንዳለበትም ይገለፃል፡፡
ትናንት በደብረታቦር የተጀመረው የዓይን ሞራ ህክምና የቀጠለ ሲሆን ዶይቼ ቬሌ የአነጋገራቸው ታካሚዎች የዓይን ብርሀናቸው እንደተመለሰ አመልክተዋል፡፡ አንድ ዓይናቸው ከዓመት በላይ ማየት አቁሞ እንደነበር የሚናገሩት ከላይ ጋይንት ወረዳ የመጡት እማሆይ እማወይ ደረሰ ታክመው ማየት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
ከዚህ በፊት የተወሰነ ያማቸው እንደነበረና ከአንድ ዓመት ወዲህ እንደባሰበቸው ገልፀዋል፣ ዛሬ በተደረገላቸው ህክምና ግን ያለምንም ችግር ታሞ በነበረውና ህክምና ባገኘው ዓይናቸው መለየት መቻላቸውን ነው የገለፁት፡፡ ከአንዳ ቤት ወረዳ ለህክምና የመጡት አቶ ጋሻዬ ጥሩነህ ለሶስት ዓመታት ዓይናቸው ተሰውሮ የነበረ ቢሆንም በተደረገላቸው ህክምና ማየት መቻላቸውን አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በህመማቸው ምክንያት ሥራ መስራት አቁመው የነበረ ቢሆንም፣ ከእንግዲህ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱም አስረድተዋል፡፡
አቶ ሙጨየ አመራ ለ4 ዓመታት ዓይናቸው በሞራ ተሸፍኖ እንደቆየ ገልፀዋል፣ ከህክምናው በኃላ ማየት በመቻላቸው በእጅጉ እንደተደሰቱ ነግረውናል፣ ሌሎችም ህክምናውን እንዲያገኙ እንደሚናገሩም አመልክተዋል፡፡
አቶ ሙጨየ ባህላዊ ዘፈን በመዝፈን ጭምር ነው የዓይን ብርሀናቸው ከ4 ዓመታት በኋላ በመመለሱ የተደሰቱት፡፡ የሀቱኔ ግብረሰናይ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሀቱኔ ዶጋን በህክምና ውጤቱ እንደተደሰቱ አመልክተው በስራው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“የታማሚዎች የዓይን ብርሀን እንደገና በመመለሱ በእጅጉ ተደስቻለሁ፣ በስራው ላይ ተሳተፉትን የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎችን አካላትም አመሰግናለሁ፣ እንኳን ደስ አላችሁም፣ ወደፊትም እገዛችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፣ መንግስት የህክምና ቁሳቁሶችን እንድናስገባ በምናደርገው ጥረት እንዲተባበረን እጠይቃለሁ፣ አመሰግናለሁ፡፡”
ህክምናውን ከሚሰጡ ኃኪሞች መካከል በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ማቲያስ ጥላሁን በ6 ቀናት ውስጥ 600 ሰዎችን ለማከም ቢታቀድም ከታማሚው ቁጥር ብዛት አንፃር የህክምና ቀኑን ለማራዘምና ተጨማሪ ህሙማንን ለማከም መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ ህክናው በቡድን የሚከናወን ሲሆን የተለያየ የጤና ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች በየቀኑ እስከ 100 ሰዎችን እንደሚያክሙም አብራርተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ