1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመኖቹ በዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

አማራጭ ለጀርመን የጀርመን ጥምር መንግሥትን የመሰረቱት ሦስቱ ፓርቲዎች፣በምርጫው ካገኙት ውጤት ከእጥፍ በላይ በሆነ ድምጽ አሸንፏል። AFD በአንድ ፌደራዊ ግዛት ምርጫ ከተሰጠው ድምጽ ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጠውን ሲያገኝ የባለፈው እሁዱ የመጀመሪያው ነው።ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሀገሪቱ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ሲያሸንፍ AFD የመጀመሪያው ነው።

Deutschland | Landtagswahl in Thüringen 2024 | Höcke
ምስል Daniel Vogl/dpa/picture alliance

በጀርመኖቹ የዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ

This browser does not support the audio element.

በዛክሰን አንሀልትና ቱሪንገን በተባሉት በምሥራቅ ጀርመኖቹ ግዛቶች እሁድ በተካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ፣ የጀርመን ጥምር መንግሥት አባላት የሆኑት ሦስት ፓርቲዎች ጉድ ሆነዋል። በነዚህ ፌደራዊ ግዛቶች ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከሦስቱ ፓርቲዎች ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ድምጽ ማግኘቱ አስደንግጧቸዋል። ይህ ውጤት የዛሬ ዓመት በሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝም ከወዲሁ እያነጋገረ ነው። ይህ ውጤት በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ለሚካሄደው የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ ምን ማለት ነው? በጥምሩ መንግሥት እጣ ፈንታ ላይ ሊያሳድር የሚችለውስ ተጽእኖ ይኖር ይሆን? 

ዳግም የጀርመንን ምርጫ ያስተናገደችዉ በርሊን ከተማ
በጀርመን ፌደራዊ ግዛቶች የሚካሄዱ ምርጫዎች ከአካባቢያዊ ምርጫነት ባሻገር ብዙ ትርጉም አላቸው ። የምርጫዎቹ ውጤት የፌደራል መንግሥቱ የስራ አፈጻጸም መለኪያዎችም ናቸው። ለዚህም ነው ባለፈው እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች በዛክሰን አንሀልት እና ትዩሪንገን ግዛቶች ብቻ የተካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ውጤት የጀርመናውያን በሙሉ ጉዳይ የሆነው።

የ(አማራጭ ለጀርመን) ፓርቲ ድል የጥምሩ መንግሥት አባል ፓርቲዎች ሽንፈት  


በነዚህ ምርጫዎች ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን  ፓርቲ AFD ፣ የጀርመን ጥምር መንግሥት የመሰረቱት ሦስቱ ፓርቲዎች ፤ በምርጫው ካገኙት ውጤት ከእጥፍ በላይ በሆነ ድምጽ አሸንፏል። በዚህ ምርጫ AFD በአንድ ፌደራዊ ግዛት በተካሄደ ምርጫ ከተሰጠው ድምጽ ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጠውን ሲያገኝ የባለፈው እሁዱ የመጀመሪያው ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሀገሪቱ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ሲያሸንፍ የAFD ድል የመጀመሪያው መሆኑም ተገልጿል። የጥምሩ መንግሥት አባላት የመሀል ግራው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር SPD ፣ለአካባቢ ጥበቃ የሚሟገተው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እና ለዘብተኛው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር FDP በጀርመን ግዛቶች አካባቢያዊ  ምርጫ እንደእሁዱ ዓይነት መጥፎ ውጤት አምጥተው አያውቁም።  ትናንት ታርሞ በወጣው ውጤት መሠረት ከዛክሰን አንሀልት ፌደራዊ ክፍለ ሀገር 120 መቀመጫዎች የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ CDU 41 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ አማራጭ ለጀርመን AFD ደግሞ በማስተካከያው ተቀንሶ 40 መቀመጫዎችን ይዟል። SPD 10 ፣አረንጓዴዎቹ ደግሞ 7 መቀመጫዎች ብቻ ሲያሸንፉ ግራዎቹ 6 መቀመጫዎች የነጻ መራጮች ፓርቲ የተባለው ደግሞ 1 መቀመጫ ብቻ ነው ያገኘው። 
በትዩሪንገን ደግሞ አማራጭ ለጀርመን አብላጫ ድምጽ ሲያገኝ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ በትዩሪንገን የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ደግሞ በትዩሪንገንና በዛክሰን አንሀልት ፌደራዊ ግዛቶች ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ለመያዝ ማግኘት  የሚጠበቅባቸውን 5 በመቶ ድምጽ ማግኘት እንኳን አለመቻላቸው ማነጋገሩ ቀጥሏል። ታዲያ በነዚህ ፌደራዊ ግዛቶች ህዝቡ ለአንጋፋዎቹ የጀርመን ፓርቲዎች ድምጽ ነፍጎ የዛሬ 12 ዓመት የተመሰረተውን ቀኝ ጽንፈኛው ፓርቲ «አማራጭ ለጀርመንን ለምን መረጠ? ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ምክንያቱ የህዝቡ የተጠራቀመ ብሶት ውጤት ነው ሲሉ መልሰዋል።   

መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በጀርመን ፓርላማምስል Hannes P. Albert/dpa/picture alliance

የበርሊኑ መንግሥት በምርጫው ተቀጥቷል

 

ከምርጫዎቹ በፊት በተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ከግዛቶቹ ፓርላማዎች ሊወጣ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ነበሩ። በስተመጨረሻ ግን ከዚህ ተርፏል። ከአምስት ጀርመናውያን አራቱ በጀርመን ፌደራል መንግሥት ስራ ደስተኛ አይደለንም ብለዋል። ይህም ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ ሲባል የቆየ ጉዳይ ነው። በቅርቡ ፖልስተርስ ኢንፍራትሴት ዲማፕ የተባለው አጥኚ በሚያካሂደው መደበኛ ወርሀዊ የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው በጥናቱ የተሳተፉ ፣ስለጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና ሚኒስትሮቻቸው ተጠይቀው የሰጧቸው ደረጃ አነስተኛ ነው። የጥምር መንግሥቱ አባላት በቋሚ ጸብ የተጠመዱ እና እርምጃ መውሰድም የተሳናቸው ተደርገው ነው የሚታዩት። በምዕራብ ጀርመንዋ በዞሊንገን ከተማ አንድ ተገን ጠያቂ የስለት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ መንግሥት ወንጀለኛ ናቸው ተብለው ሀገራቸው እንዲመለሱ የተወሰነባቸውን የአፍጋኒስታን ስደተኞች በአፋጣኝ  ወደ ሀገራቸው ቢጠርዝም፣ ህዝቡ ላይ ያመጣው ለውጥ የለም።  ባለፈው ሳምንት ጥብቅ የፍልሰትና የደኅንነት እርምጃ እንደሚወስድ መንግሥት ካሳወቀ በኋላ  ወንጀለኛ ያላቸውን 28 ተገን ጠያቂዎች በድንገት ወደ አፍጋኒስታን አባሯል። 
በአሁኑ ምርጫ AFD ሰፊ የድጋፍ መሠረት እንዳለው ማረጋገጡን ይናገራል። ከፓርቲው መሪዎች አንዷ አሊስ ቫይድል ፓርቲያቸው AFD ያገኘውን ድል ታሪካዊ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው ህዝቡ የፌዴራል መንግሥቱን ቀጥቷል ሲሉ ተናግረዋል። ውጤቱ ለፌደራል መንግሥቱ ሞት ነው ካሉ በኋላ ከዚህ ቀደም የፌደራል መንግሥቱ ይውረድ ያሉበትን ጥያቄ በድጋሚ አቅርበዋል። 
«ለኛ ታሪካዊ ስኬት ነው።ለመጀመሪያ ጊዜ በፌደራዊ ግዛቶች እና በዛክሰን አንሀልት ካለፈው ምርጫየተጠናከረ ውጤት ማግኘት ችለናል።በምርጫዎቹ እየጠነከረን ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የምርጫው ውጤት ተጣምረው ሀገሪቷን ለሚመሩት ፓርቲዎች ደግሞ ቅጣት ነው። ጥምሩ መንግሥት ማስተደደር መቀጠል መቻሉን አለመቻሉን ራሱን መጠየቅ አለበት። ይህ አዲስ ምርጫ ይካሄድ የሚለው ጥያቄ ቢያንስ በብራንድቡርግ ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ መነሳት አለበት።ምክንያቱም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ልንቀጥል አንችልም።»
ውጤቱ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲን ቢያስፈነድቅም ዶክተር ለማ እንደሚሉት ምርጫ በተካሄደባቸው ግዛቶች መንግስት መመስረቱ እንዲህ ቀላል አይሆንም 
 

ከእሁዱ ምርጫ አሸናፊ የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ መሪዎች አንዱ ቲኖ ቹርፑላምስል Lisi Niesner/AFP/Getty Images

ዓይኖች ሁሉ ብራንድቡርግ ፌደራዊ ግዛት ላይ አትኩረዋል

 

በሌላኛው የምሥራቅ ጀርመን ፌደራዊ ግዛት ብራንድቡርግ ከ19 ቀናት በኋላ አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ ታቅዷል። በዳሰሳ ጥናቶች መሰረት እዚያም AFD እየመራ ነው። ሆኖም SPD በቅርበት እየተከተለው ነው። በብራንድቡርግ የሚያስፈልገውን ድምጽ ማግኘት ለሚሻው SPD የሚያሸንፈው ድምጽ ለህልውናው ወሳኝ ነው። SPD ከጎርጎሮሳዊው 1990 አንስቶ የብራንድንቡርግን መንግሥት ሲመራ ቆይቷል። የፓርቲው ዋና ጸሀፊ ኬቪን ኩኽንነርት አደጋው አዲስ ሳይሆን የነበረ መሆኑን አስረድተዋል።የጀርመን ምርጫ ውጤትና የአዲስ መንግሥት ምስረታ ዝግጅት
«በግልጽ እንናገረው ፣ ከግዛቶቹ ፓርላማዎች የመባረር እውነተኛ አደጋ ነበር።  በዚህ ረገድ ለፓርቲዬ የማስተላልፈው መልዕክት ይህን ለመለወጥ ትግል ማካሄድ ይገባል ፤እኛ እንፈለጋለን የኛን ፖሊሲዎች የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፤ እናም በመጪው ዓመት የሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ትኩረት ይህ ነው የሚሆነው። ተጨማሪ ጥንካሬ ለማግኘት መታገል አለብን።»
SPD ፣የብራንድንቡርግን መንግሥት ለ35 ዓመታት የመራ ፓርቲ ነው።ፓርቲው በቱሪንገንና በዛክሰን አንሀልት አይሸነፉ ሽንፈት ቢገጥመውም መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በፓርቲያቸው ድጋፍ ስራቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ የሚናገሩ አሉ።  ይሁንና የብራንድቡርግን ግዛት ለ11 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ዲትማር ቮይድከ ካልተመረጡ ፓርቲው የነበረው የአንድነት መንፈስ በፍጥነት ሊፈረካከስ ይችላል የሚል ስጋት አለ። በዚህ ጉዳይ ላይም ከሾልስ ይልቅ ይበልጥ በህዝብ የሚታወቁት የመከላከያ ሚኒስትሩ ቦሪስ ፒስቶርየስ በመጪው ዓመት በሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ  የፓርቲው እጩ ተወዳዳሪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ወሬዎች መናፈስ ጀምረዋል። 

ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓም በዛክሰን አንሀልትና በትዩሪንገን በተካሄዱት ምርጫዎች የAFD የCDU እና የቡንደስ ዛራ ቫግንክሬሽት ፓርቲዎች እጩ ተወዳዳሪዎች መግለጫ ሲሰጡ ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance


የጥምሩ መንግሥት ፈተናዎች 

አሁን ጥያቄው የSPD የአረንጓዴዎቹ እና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጥምር መንግሥት  እስከ ሚቀጥለው ዓመት ድረስ መዝለቅ ይችላል ወይ? ነው። ጥምር መንግሥቱን ሊፈትኑ ይችላሉ ከሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በቅርቡ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥበት የጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. የሀገሪቱ በጀት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ መንግሥት ያሳወቀውን ጥብቅ የፍልሰት ፖሊሲ አወጣለሁ ያለውን  ገቢራዊ ያደርገዋል ወይ የሚለው ጉዳይም ሌላው ፈተና መሆኑ ይነሳል። በተለይ በፍልስተት ጉዳይ መንግሥት እወስዳለሁ ያለው እርምጃ ማጠራጠሩ አልቀረም። የዚህ ምክንያቱም ከSPD ውስጥ የግራ ክንፎች እንዲሁም አረንጓዴዎቹ ፍልሰትን ለመገደብ በወጣው እቅድ አለመስማማታቸው ነው። የሦስቱ አፍሪቃውያን የጀርመን ም/ቤት አባላት ማንነት

ሦስቱም ፓርቲዎች የጥምር መንግሥቱ እንዲሳካለት ፍላጎታቸው ቢሆንም ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ በብሔራዊ ደረጃ የሚካሄድ ከሆነ አሁን በተካሄዱት የዳሰሳ ጥናቶች መሠረት ከአሁን በኋላ አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም። አሸናፊዎቹ ተቀናቃኞቻቸው AFD እና እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት CDUና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ CSU መሆናቸው አይቀርም። በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዋነኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እህትማማቾቹ CDU እና CSU ጥምሩ መንግሥት ይውረድ ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል። ታዲያ የጥምሩ መንግስቱ እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ወደፊት የምንመለስበት ጉዳይ መሆኑ አይቀርም።


ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW