1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በጀጎል ቅርሶች ላይ ስጋት የደቀነዉ የኮሪደር ልማት

ሐሙስ፣ ኅዳር 3 2019

በሐረር ከተማ በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈረዉ፤ ጀጎል እየተከናወነ ባለዉ የኮሪደር ልማት ሰበብ በግንቡ ዉስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ቤቶች መፍረሳቸዉ እየተነገረ ነዉ። የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከትዉልድ ትዉልድ፤ በቅብብሎሽ በታሪካዊ ቤቶች ዉስጥ ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችም ተፈናቅለዋል። አሁን ቦታዉ ባለሃብት እንዲገዛዉ ጥሪ እየቀረበ ነዉ።

የሐረር በር
የሐረር በርምስል፦ Mesay Tejkelu/DW

በጀጎል ቅርሶች ላይ ስጋት የደቀነዉ የኮሪደር ልማት

This browser does not support the audio element.

የጀጎል ታሪክ ጠገብ ቅርሶችዋ በኮሪደር ልማት አደጋ ላይ ወድቀዋል

በሐረር ከተማ በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈረዉ፤ ጀጎል እየተከናወነ ባለዉ የኮሪደር ልማት ሰበብ በግንቡ ዉስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ቤቶች መፍረሳቸዉ እየተነገረ ነዉ። የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከትዉልድ ትዉልድ፤ በቅብብሎሽ በታሪካዊ ቤቶች ዉስጥ ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችም ተፈናቅለዉ፤ መዉደቅያ አላገኙም። አሁን ቦታዉ ባለሃብት እንዲገዛዉ ጥሪ እየቀረበ ነዉ፤ ይህ ሁላችንንም ከታሪክ ተጠያቂነት አያድነንም ያሉን፤ የአንድ በሕያዊትዋ ሙዚየም በጀጎል ነዋሪ « ጀጎል የቅርስ ከተማ ነች። እያንዳንዱ ነገር በጀጎል ቅርስ ነዉ። መኖርያ ቤቱ፤   ህንጻዎች መስጊዶቹ፤ የእግር መንገዶቹ የበቀሉት ዛፎች ሳይቀር ቅርሶች ናቸዉ። ትንሽ የሚባለዉ በጀጎል ያለዉ የቅርስ እድሜ 100 ዓመት ነዉ። ረጅም እድሜ ያለዉ ቅርስ እድሜ ከ 600 ዓመት በላይ ነዉ። በድሪ በሪ ወይም ቡዳ በር በሚባለዉ ጀጎል ዉስጥ ረጅም እድሜ ያላቸዉን ቤቶች በቡልዶዘር አፍርሰዋል። ይህ ከ 600 ዓመት በላይ ያላቸዉ ቤቶች፤ የፈረሱት በኮሪደር ልማት ስም ነዉ። ይህ በታሪክ ላይ በቅርስ ላይ በማነት ላይ የሚሰራ ወንጀል ነዉ። አሁን ያሉ አመራሮች ታሪክ እንደሚፋረዳቸዉ አዉቀዉ ይህንን ነገር ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።»

በጀጎል ቅርሶች ላይ ስጋት የደቀነዉ የኮሪደር ልማት

በምስራቅ ኢትዮጵያ የምትገኘዉ እና በ 10ኛዉ ወይም በ 11ኛዉ ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደተመሰረተች የሚነገርላት  ሐረር ከተማ ፤ በዉስጧ በ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን በኤሚር ኑር የተገነባዉ እና በዓለም እዉቅናን ባስገኘላት በጀጎል ግንቧ ትታወቃለች። ጀጎል ግንብ በጎርጎረሳዉያኑ 2006 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፤ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ ጥበቃ እንዲደረግለት ተመዝግቧል። በእስልምና ሃይማኖት አራተኛው እጅግ የተቀደሰ ከተማ ተብሎ የሚጠቀሰው ሐረር ጀጎል፣ 82 መስጊዶችን (ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ ከ10ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበሩ) ከ 2000 በላይ ጥንታዊ እና ባህላዊ ቤቶች፤ እንዲሁም  102 መካነ መቃብሮችን  የያዘ ነው። ጀጎል ዉስጥ ያሉት ልዩ ቅርስን የያዙት እነዚህ ሕንጻዎች፤ የእግር መንገዶች እና የመኖርያ ቤቶች፤ በሐረር ከተማ ከሚታዩ እጅግ አስደናቂ ባህላዊ ቅርስ አንዱ ያደርገዋል። የአፍሪቃ እና የእስልምና ወጎች፤ በእይታ የማይጠገቡት የግንባታ አይነቶች ጀጎል ከተማ አቀማመጥ ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ፣ ሐረርን ልዩ አድርጓታል። በሐረር ብሎም የጀጎል ከተማ ነዋሪዎች ፤ በከተማዋ እየተሰራ ያለዉ የኮሪዶር ልማት ብሎም የተሰሩት ጽዳቶች ጥሩ ሆነዉ ሳለ  በልማት ስም ታሪካዊ ቅርስ ግን እየፈረሰ ነዉ ሲሉ አሳሳቢነቱን ገልፀዋል።

የጀጎል ታሪካዊ ቅርስ በተጀመረዉ የኮሪደር ልማት አደጋ ላይ ወድቋልምስል፦ Abdunasser Abdullahi

ቅርሶች መነካት አልነበረባቸዉም

“ሐረር በምስራቅ አፍሪቃ የረጅም ዘመናት ቅርሶችን የያዘች ከተማ ነች። በተለይ በጀጎል የሚገኙት፤ የኢስላም ሃይማኖት፤ የንግድ እንዲሁም የሥነ-ጥበብ ቅርሶች ለሐረሪ ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን፤ የመላዉ ኢትዮጵያዉያን ታሪክ ከዝያም አልፎ፤ የምስራቅ አፍሪቃ የንግድ ልዉዉጥ፤ የሃይማኖት መስተጋብር የጥበብ እድገት፤ የሚገኝባት ከተማ ናት። ይሁን እና በአሁኑ ወቅት በተለይ በጀጎል እየተካሄደ ያለዉ የኮሪደር ልማት፤ ቅርስ እየፈረሰ መሆኑ ያሳዝናል። ኮሪደር ልማቱ በሀረር ከተማ ብሎም በጀጎል፤ ብዙ ነገሮችን ጥሩ አድርጓል። ቆሻሻ ቦታዎችን አጽድቶ ሰዎች በደስታ እንዲጠቀሙበት አድርጓል። ይሁን እና በልማት ሰበብ ረጅም ዘመናት እድሜ ያላቸዉ ቤቶች ፈርሰዋል። ቅርሶች መነካት አልነበረባቸዉም።  ቅርሱ የፈረሰዉ ከጀጎል አምስት መግብያ በሮች መካከል በድሪ በሪ ወይም ባድሮ በሪ፤ በተለምዱ ቡዳ በር የተባለዉ በሙሉ ነዉ የፈረሰዉ። ይህ በጣም ያሳዝናል። ቅርሱ መፍረሱ ብቻ ሳይሆን፤ ቤታቸዉ ፈርሶ ከአካባቢዉ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችም ብዙ ናቸዉ። ሰዎቹ ከትዉልድ ትዉልድ ሲተላለፍላቸዉ የነበረዉን መኖርያ ቤታቸዉን ነዉ ያጡት።”

ጀጎል በኮሪደሩ ልማት የታደሰ ቦታ ምስል፦ Abdunasser Abdullahi

ትዉልድ እድገታቸዉ በሐረር ጀጎል እንደሆን የነገሩን አስተያየት ሰጭዉ በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን ከተገነባዉ የጀጎል ግንብ አምስት በሮች መካከል፤ በበስተ ምዕራብ ላይ በሚገኘዉ በር ጠገብ የሚገኙ ህንጻዎች መፍረሳቸዉን ተናግረዋል። የቅርስ መፍረሱ ስራ በዚህ ቢበቃ ስንል ጥሪ እናቀርባለን ያሉት፤ የጀጎል ከተማ ነዋሪ፤ የኮሪደር ልማት እቅዱ በሌሎች የጀጎል ከተማ አካባቢዎች እንደሚሰፋ መረጃ እንዳላቸዉ ተናግረዋል። አምስት በሮችን የያዘዉ የጀጎል በር በተለይ በበድሪ በሪ መንገዶችም ፈርሰዋል።  

ጀጎል  ላይ የፈረሰዉ እድሜ ጠገብ ቅርሳችን የማንነታችን መገለጫ ነዉ ያሉን፤ ሌላዉ የቀድሞ የጀጎል ነዋሪ፤ የጀጎል ቅርስ ይጠበቅልን ብለን ጥሪ በማሰማታችን እኛም ስጋት ላይ ነን ብለዋል።“የጀጎልን ነዋሪ ያስጮኸዉ እና ያበሳጨዉ፤  የማንነታችን ቅርሳችን ህልዉናችን የሆነዉ እድሜ ጠገብቅርስ በመፍረሱ ነዉ። ጀጎል ግንብ ማለት ከ 800 ዓመት በላይ ታሪክ ያለዉ ስለሆነ፤ ይህን አካባቢ ማፍረስ ቀስ በቀስ ማንነታችንን ማጥፋት ነዉ። የኮሪደር ልማቱን የሚያካሂዱት ሰዎች፤ እንደነበረ እንመልሰዋለን እያሉ ነዉ እያፈረሱ ያሉት። ግን ቅርስ ከፈረሰ በኋላ እንዴት ነዉ ወደነበረበት የሚመለሰዉ።”  

የጀጎል ታሪካዊ ቅርስ በተጀመረዉ የኮሪደር ልማት አደጋ ላይ ወድቋልምስል፦ Abdunasser Abdullahi

ለቅርሱ መፍረስ ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን

“እስካሁን የፈረሰዉ የጀጎል ቅርስ አይመለስምይሁን እና ከእንግዲህ ይህ ቅርስን የማጥፍት ርምጃ ይቁምልን” ሲሉ የጀጎል ነዋሪዉ ጥሪ አቅርበዋል። የሐረር እና የአካባቢዋ የቅርስ የባህል እና የታሪክ ባለሞያ የሆኑት አብዱናስር አብዱላሂ፤ ሐረር በዓለም የቅርስ ጥበቃ መዝገብ ለመመዝገብ የበቃችዉ፤ የባህላዊ ሃይማኖታዊ እና የታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት በመሆንዋ ነዉ።  ጀጎልም “ህያዊትዋ ሙዚየም በመባል ትታወቃለች“ ብለዉናል። የጀጎልን ቅርስ  በኮሪደር ልማት  ሰበብ ማፍረስ ግን “ሁላችንም  ከተጠያቂነት አናመልጥም“ ሲሉ የሐረር እና አካባቢዋ የቅርስ የባህል እና የታሪክ ባለሞያዉ አብዱናስር አብዱላሂ ተናገረዋል።  

የጀጎል ታሪካዊ ቅርስ በተጀመረዉ የኮሪደር ልማት አደጋ ላይ ወድቋልምስል፦ Abdunasser Abdullahi

በሽር አሕመድ የተባሉ የዶቼ ቬለ ተከታታይ ለዶቼ ቬለ በጻፉት አስተያየት«በሀረሪ ክልል፤  ሀረር ከተማ  በድሪ በሪ በረመዳን ፃም 2018 አረጋዊያን ሸማግሌዎችን በፃም አፋችው፤ በማሰገደድ በሀይል ከ1000 ዓመት በላይ ከኖሩበት ባህላዊ ቤቶች ውሰጥ አስወጥተዋቸዋል። የክልሉ መንግስት 64 ብርቂዬ እድሜ ጠገብ የሆኑ ባህላዊ ጌይ ጋሮችን አፍርሰዋል ።ይህ የተሰራው ግፍ አንሶ አልበቃ ብሎ መሬቱንም በማስተካከልና በመሸንሸን ለጨረታ በማቅረብ ለሌላ ሰው አሳልፎ ለመሰጠት የክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ።

ሰለሆነም ቅርፅን በማፍረስ ዜጋውን የማፈናቀል የማንነት የማጥፋት ሴራ መቆም አለበት። ጨረታውን የሚገዙ ስዎችም የወደመው ቅርስ ተመልሶ የሚሰራበት ቦታ መሆኑን በመረዳት፤ ሀብቱን ከብክነት እንዲያድን በማለት እንመክራለን። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ለዓለም ቅርስ ለተመዘገበው በድሪ በሪ የፈረሱ ቤቾች ተመልሰው በነበረበት መልኩ እንዲገነቡ»

ጀጎል የሚገኝ መስጎድ ምስል፦ Abdunasser Abdullahi

የጀጎል አምስት በሮች

በ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት የጀጎል ግንብ አምስት መግብያ በሮች አሉት። የመጀመርያዉ እና  በኮሪደር ልማት  እንደፈረሰ የተነገረለት በሐረሪ ቋንቋ በድሪ በሪ ወይም «የበድር በር» በመባል ይታወቃል። ይህ በር በተለያዩ ጊዜያት «ቡዳ በር» «ሐኪም በር»  ወይም በኦሮምኛ «ደራ ቡዳዋ» በመባል እንደሚታወቅ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ ። ሁለተኛ ዉ በር በሐረሪ ቋንቋ «አስማጂን በሪ» ሦስተኛዉ በር «ሱጉድአጥ በሪ» አራተኛዉ በር «አርጎባ በሪ» አምስተኛዉ በር «አሱሚይ በሪ በመባል ያታወቃሉ። ጀጎል የሚለዉ ቃል በራሱ ከለላ የሚል ትርጉም እንዳለዉም ይነገራል።

የጀጎል ታሪካዊ ቅርስ በተጀመረዉ የኮሪደር ልማት አደጋ ላይ ወድቋልምስል፦ Abdunasser Abdullahi

በጎርጎረሳዉያኑ 1551 -1552 ዓ.ም በአሚር ኑር ቢን ሙጃሂድ እንደተገነባ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ጀጎል፤ የተገነባዉ  ሐረር  ከተማን እና ነዋሪዎችዋን  ከዉጭ ወራሪዎችና ጦረኞች ለመጠበቅ ተብሎ የተሰራ እንደሆነ ይነገርለታል። በሐረር እየተካሄደ ባለዉ የኮሪደር ልማት በተለይም ደግሞ ጀጎል ዉስጥ ፈረሱ ስለተባሉት ታሪካዊ ቅርሶች፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም። ጥረታችንን እንቀጥላለን። 

ሙሉዉን ጥንቅር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW