1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በጅማ ከሰማይ ስለወረደው ባዕድ ነገር ምንነት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2016

ባለፈው ዓርብ ሰኔ 05 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ሌሊት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የቡ ከተማ ከሰማይ ከፍተኛ ድምፅ ተሰምቶ ወድቋል የተባለው ባዕድ ነገር በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተቀናጀ መልኩ እየተጠና መሆኑ ተነገረ ። ስለባዕድ ነገሩ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው የቤተሙከራ ጥናት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም ባለሞያዎቹ መክረዋል ።

ኮሜትስ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
ኮሜትስ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Photoshot/picture alliance

የባዕድ ነገሩ ምንነት ቅድመ ግምት

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ዓርብ ሰኔ 05 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ሌሊት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የቡ ከተማ ከሰማይ ከፍተኛ ድምፅ ተሰምቶ ወድቋል የተባለው ባዕድ ነገር በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተቀናጀ መልኩ እየተጠና መሆኑ ተነገረ ።  አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኅዋ ሳይንስና ስነ ቴክኒክ ሠነደ-ምድር ተቋም(space science and geospatial institute)እንዲሁም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ባለሞያዎች ነገሩ አልፎ አልፎ የሚከሰት መሆኑን ገልጠዋል ። በሥርዓተ ፀሐይ ውስጣዊ ክፍል የሚሽከረከሩ ንዑስ ፕላኔት መሳይ ቁሶች አለያም ዓለታማ አካላት (Asteroid) የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ብለዋል ። ይሁንና ስለባዕድ ነገሩ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው የቤተሙከራ ጥናት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም ባለሞያዎቹ መክረዋል ። 

የባዕድ ነገሩ ምንነት ቅድመ ግምት

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የስፔስና ፕላኔተሪ ሳይንስ ክፍል የአትሞስፌሪክ ሳይንስ ተመራማሪ ዶ/ር ገመቹ ፋንታ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በመረጃ ደረጃ ስለ ባዕድ ነገሩ እስካሁን የታወቀው ነገር በላቦራቶሪ ጥናት ባይረጋገጥም ሊሆን የሚችለውን ባለሞያቸው አብራርተዋል ።

ዶ/ር ገመቹ እንዳሉት፦ «ስፔስ ውስጥ በፀሐይ ዙሪያ የምንቀሳቀሱ አለታማ ነገሮች አሉ ። እነዚህ አለቶች በተለይም በጁፕተር እና ሳተርን መካከል በጉልኅ ይታያሉ ። እነዚህ በትንንሽ እና ትልልቅ በብዙ መጠን ያሉ አለቶች አስትሮይድ ይባላሉ ። ልክ እንደ ፕላኔቶች በፀሐይዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው» ብለዋል ።

በእነዚህ አስትሮይድ በተባሉ ግዑዝ ነገሮች ውስጥ በመሬት ላይ ያሉም ሆነ የሌሉ ማዕድናት መኖራቸውንም ባለሞያው አስረድተዋል፡፡ እነዚህ አለታማ ቁሶች በተለያዩ ጊዜያት በግፊት ኦርቢታቸውን በመልቀቅ እየተወረወሩ መሬትን ጨምሮ የተለያዩ ፕረላኔቶች ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡  አስትሮይድ የተባሉት አለታማ ነገሮቹ ወይም ኮሜት ቁርጥራጮች ምድር ላይ ሲወድቁ ወይም ልክ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገቡ ሜትሮይትስ (Meteorites) እንደሚባሉም ባለሞያው አክለው አብራርተዋል፡፡

ፎቶ ከማኅደር፦ አስትሮይድ የተባሉት ዓለታማ ነገሮች ወይም ኮሜት ቁርጥራጮች ምድር ላይ ሲወድቁ ወይም ልክ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገቡ ሜትሮይትስ (Meteorites) እንደሚባሉም ባለሞያው አክለው አብራርተዋልምስል Pond5 Images/IMAGO

ወደ ምድር የሚወድቁበት ክስተት

እነዚህ አስትሮይዶች ጥቃቅን ከሆኑ ልክ ወደ ከባቢ አየር ሲገቡ ግጭት ስለሚፈጥሩ በተለምዶ የከዋክብት ጅረቶች እንደሚባሉት አይነት ብርሃናማ ክስተት እንደሚፈጥሩም ተነግሯል፡፡ ከከባቢ አየር ውስጥ ፍጭት ውስጥ የሚነዱት ሜትሮይትስ (Meteorites) በብዛት ከወደሙ በኋላ የተረፈው ወደ ምድር ሲወድቅ ጥቃቅን ከመሆናቸው አንጻር በራዳርም ለመከታተል አስቸጋሪ ይሆናሉ ተብሏልም፡፡

ከሰሞኑ ከጅማ ከተማ 18 ኪ.ሜ. ወደ አጋሮ አቅጣጫ ወጣ ብሎ በሚገኘው የቡ ከተማ አከባቢ የወረደው ባዕድ ነገርም በመጠን አነስ ያለ ሲሆን በተወሰነ ወደ ምድር ገባ ማለቱ ተነግሯል፡፡ ይህ ነገር ሜትሮይትስ ነው ወይስ ሌላ ምድር ላይ የነበረ እንደ ቮልካኖ ባለ ክስተት የተፈጠረ የተለመደው አለት ወይም ድንጋይ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን የላቦራቶሪ ውጤት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የስፔስና ፕላኔተሪ ሳይንስ ክፍል የአትሞስፌሪክ ሳይንስ ተመራማሪ ዶ/ር ገመቹ ፋንታ ገልጸውልናል።

እነዚህ አስትሮይዶች ከመብረቅ እጅግ ሰፊ ልዩነት እንዳላቸውና ምናልባት በሰው ወይም ቤቶች ላይ ቢወድቁ ግን የከፋ ጉዳት ማድረስ እንደሚችሉም ባለሞያው አስረድተዋል፡፡ «መብረቅ በተለያየ አቅጣጫ በሚሄድ እርጥበት አዘል ከባባድ ደመና ውስጥ በሚፈጠር ግጭት የሚፈጠር ሲሆን አስትሮይድ ግን ከዚያ ፍጹም ይለያል» ብለዋልም፡፡ 

አስትሮይድ እንደመጠኑ ቢለያይም አንዳንድ ቦታ ላይ፤ ለአብነትም በቅርቡ ከአምስት ዓመት ወዲህ በሳይበሪያ በመውደቅ ሐይቅ እስከመፍጠር የደረሰ በከፍተኛ ደምፅና አቅም ወደ መሬት ሰርጎ መግባቱን ባለሞያው ነግረውናል ። አስትሮይድ በብዙ አጋጣሚ በውኃ ውስጥ የመውደቅ አዝማሚያ ስላለው ብዙውን ጊዜ ሰው ላይ ወድቆ ጉዳት የማስከተሉ አጋጣሚ አነስተኛ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ፎቶ ከማኅደር፦ አስትሮይድ ከተባሉት ዓለታማ ነገሮች አንዱምስል NASA, ESA

የጅማ ዩኒቨርሲቲው የጥናት ሂደት

በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስትሮፊዚስቲ ኮስሞሎጂስት የሆኑት የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ዶ/ር ቶሉ ብረሳ ከሰሞኑ በጅማ በከፍተኛ ድምፅ ስለወደቀው ቁስ ከላቦራቶሪ ውጤት በፊት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚሰጡት መረጃዎች መላምት ብቻ ናቸው ይላሉ ። «ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ ስለወደቀው አለታማ ነገር ከማቴሪያል ሳይንስ፣ ከፊዚክስ፣ ከኬሚስትሪ፣ ከጂኦ-ፊዚክስ እና ከጂኦሎጂ የባለሙያዎች ቡድንን አዋቅሮ በላቦራቶሪ እያስጠና ይገኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እርግጠኛ መሆንም የሚቻለው” ብለዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ
 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW