በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ሰዎችን ያፈናቀለው ግጭት
ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2017
በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ዋላ በተባለ ቀበሌ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. አቶ ዛኪር አባኦሊ የተባሉ ባለሀብት መገደላቸውን ተከትሎ «ማንነት» ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና ግጭት መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
አንድ የጌራ ወረዳ ዋላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ በተለይም ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የባለሃብቱን መገደል ተከትሎ፤ በተፈጠረው ግጭትና ማኅበረሰብ መሃል በተከሰተው ውጥረት በርካታ ቤቶች ሲቃጠሉ በርካቶች ልጆች እና ከብቶቻቸውን ይዘው በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጫካ እንዲሁም አጎራባች አካባቢዎች ማምለጣቸውን ተናግረዋል።
ሌላው ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውም ሆነ ድምጻቸው እንዳይታወቅ ተማጽነው አስተያየታቸውን የሰጡን ተፈናቃይ ቤታቸውን ጨምሮ ንብረታቸው በመቃጠሉ ከለበሱት ውጪ ምንም ሳይዙ ቤተሰቦቻቸውን ብቻ ይዘው ማምለጣቸውን ገልጸዋል። እንደ ነዋሪዉ አስተያየት ከባለፈው ሳምንት ሐሙስ ማታ ጀምሮባለሃብቱ በተገደሉበት ቦሬ በተባለች አነስተኛ መንደር ባለሃብቱን ማን እንደገደላቸው በእርግጠኝነት ባልታወቀበት ሁኔታ ማንነት ላይ አነጣጥሮ ተፈጽሟል ባሉት ጥቃት መኖሪያ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ወፍጮ ቤቶች እንዲሁም የተዘራ እህል በተቆጡ የአካባቢው ወጣቶች መውደሙን ገልፀዋል።
በቡና ማምረት እና በሰፊው የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ነበር የተባሉት ባለሀብቱ አቶ ዛኪር ለኢንቨስትመንት መሬት ጠይቀው የ200 ገደማ የአርሶ አደሮች መሬት እንደተሰጣቸው የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ፤ አስቀድሞም በኢንቨስትመንቱ ተፈናቅለናል በሚል ያኮረፉ እንደነበሩም አስረድተዋል።
ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ 10 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የተናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ ነዋሪ በበኩላቸው፤ አሁንም ድረስ የገቡበት ያልታወቁ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ስለነዋሪዎቹ ስጋትና ስለተፈጠረው አለመረጋጋት ለመጠየቅ ዶቼ ቬለ ለጌራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃዊ ሰዒድ በመደወል ጉዳዩን እንደነገርናቸው ምንም ሳይሉ ስልካቸውን ዘግተዋል። ለጅማ ዞን ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊ ለአቶ ጁኔይዲን ብንደውልም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
እንደነዋሪዎች አስተያየት ግን መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን ሐሙስ ረፋድ ላይ ወደ ቀበሌው አሰማርቶ አካባቢውን ለማረጋጋት ቢጥርም እስካሁን የነዋሪዎች ስጋት አልተቀረፈም። በዚህም ነፍሰጡር እናቶች፣ ሕጻናት እና አረጋውያንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የጅማ ዞን ጌራ ወረዳውን ክስተቱን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ በዞኑ ጌራ ወረዳ የተፈጠረውን «ጭካኔ የተሞላበት» ያለውን የባለሃብቱ አቶ ዛኪር አባኦሊን ግድያ በማውገዝ፤ «የወረዳው ነዋሪዎች አስደንጋጩን ድርጊት አውግዘው መንግሥት ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በመያዝ ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል» ብሏል።
መንግሥትም ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ለሕግ እያቀረበ ይገኛል ያለው የክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ፤ በክስተቱ በመደናገጥ ከቀዬያቸው የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬያው እየመለሰ ይገኛል ነው ያለው። ቢሮው ጉዳዩን ወደ ሃይማኖት ግጭት የሳቡ ያላቸው በስም ያልጠቀሳቸው አካላትንም የሕዝብን ወንድማዊ መተሳሰብና አብሮ የመኖር እሴት በመሸርሸር ኮንኗል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ