በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰራው የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ ደረጃ ተሸላሚ ሆነ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 22 2015
ግሎባል ኢንዴክስ ኢንሹራንስ ፋሲሊቲ (GIIF) የተሰኘው የዓለም ባንክ መርሃ ግብር የ2022 የ«Africa AgTech and Inclusive insurance Challenge » ሶስት አሸናፊዎችን በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
ኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው እና ከ23 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 208 የፈጠራ ስራዎች በተሳተፉበት በዚህ በውድድር የሁለተኛ እና የሶስተኝነትን ደረጃ የያዙት የናይጄሪያ እና የኬንያ አግሮቴክ የፈጠራ ስራዎች ሲሆኑ፤ 25 ሺህ ዶላር ሽልማት የሚያስገኘውን የአንደኝነት ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች የሰሩት ተንቀሳቃሽ የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ አሸናፊ ሆኗል።
ይህ ቴክኖሎጂ ከሶስት ዓመታት በፊት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኤለክትሪክ እና የኮምፒዩተር ምህንድስና ተማሪዎች በነበሩ ጥጋቡ አብርሃም ፣ሄኖክ አምባዬ እና አብዲዋቅ በቀለ እንዲሁም ቡኤዝ ብርሃኑ /አማካሪ/ የተባሉ ወጣቶች በ2013 ዓ/ም ለመመረቂያ የሰሩት ነው።
በአሁኑ ወቅት የኦሚሽቱ ጆይ ጀማሪ የቴክኖሎጀ ኩባንያ ምክትል ማኔጅግ ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ አብርሃም እንደገፁት ተመርቀው ከወጡ በኋላም የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጅ ሚንስቴር ከኮሪያ መንግስት ጋር በትብብር ባዘጋጀው የኢንኩቤሽን ማዕከል የስምንት ወር ስልጠና በመውሰድ መሳሪያውን የማሻሻል እና ወደ ገበሬው ወርደው ውጤታማነቱ የመሞከር ዕድል አገኝተዋል።
እንደ አቶ ጥጋቡ ይህ ስራቸው በውድድሩ አሸናፊ የሆነው አንድም የፈጠራው አዲስነት /originality/ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተሰራ አጋዥ የግብርና ቴክኖሎጂ በመሆኑ ነው።
«የዲቫይሱ ሁኔታ ነው አሽናፊ ያደረገን።የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘብ ነው።»አፍሪካ ወሰጥ አንደሚታወቀው መሰረተ ልማት የለም።ያለውም ቢሆን የሚቆራጥ ነው።ፓወር አነዱ ኮንስትሬንት ነው።ቴሌኮሚነኬሽን ሌላኛው ኮንስትሬንት ነው። »ካለ በኋላ ይህንን ችግር ታሳቢ በማድረግ ቴክኖሎጀው በአነሰተኛ የኤለክትሪክ ሀይል አንዲሁም ያለ ኢነተርኔት ግንኙነት የሚሰራ መሆኑን ገለጿል።አጠቃቀሙም በቀላል ስልጠና በአጅ ስልክ መጠቀም አነዲቻል ተደርጎ የተሰራ ነው በማለት አብራርቷል።
ይህ የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ የአንድን የእርሻ መሬት አሲዳማነት፣የንጥረ ነገር ይዘት፣ የእርጥበት እና የሙቀት መጠን በመለካት መሬቱ ለየትኞቹ አዝርዕቶች ተስማሚ ነው የሚለውን ለይቶ ያቀርባል። የደረሰበትን ውጤት በስማርት ስልኮች አማካኝነት በጥቂት ደቂቃዎች ወደ ተገልጋዩ ይልካል።ለዚህም የሰው ሰራሽ አስተዉሎትን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጅዎችን ተጠቅመዋል።
በሌላ በኩል ገበሬው በአፈር ምርመራ ውጤቱ መሰረት እንዲያመርት ከተመከረው ሰብል ውጭ ሌላ ሰብል የማምረት ፍላጎት ካለውም መሳሪያው ሌላ አማራጭ እና መፍትሄ ያቀርባል።
አቶ ጥጋቡ እንደሚሉት ቴክኖሎጅው በዚህ ሁኔታ የሰብል ምርታማነትን የሚጨምር ሲሆን ፤ የገበሬውን የማዳበሪያ አጠቃቀም ለመመጠን እንዲሁም ተስማሚውን የማዳበሪያ አይነት ለመምረጥ ዕድል ይሰጣል። ይህም የገበሬውን የማዳበሪያ አጠቃቀምን በማዘመን ምርትን ከጉዳት ይታደጋል።
ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝቧ በግብርና በሚተዳደርባት ኢትዮጵያ የአፈር ምርምር ጥናት የሚካሄድባቸው ማዕከላት ጥቂት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።አንደ አቶ ጥጋቡ ገለፃ ደግሞ በእነዚህ ማዕከላት ለአፈር ጥናት የሚውሉ መሳሪያዎች በመጠን ትልልቅ በመሆናቸው ከቤተሙከራ አውጥቶ ማሳ ላይ ለመጠቀም አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የእነሱ ፈጠራ አነስተኛ መጠን ያለው እና በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።በአጠቃቀም ረገድም ኦሚሽቱ ጆይ ማንበብ እና መጻፍ ለማይችሉ ገበሬዎች በድምጽ ትዕዛዝ መቀበል እንዲችል እና ውጤቱንም በድምጽ መግለጽ እንዲችል ተደርጎ መሰራቱን አመልክተዋል።የተለያዩ ቋንቋዎችም ተካተውበታል።
ይህ ቴክኖሎጅ በጅማ እና በአካባቢው በሚገኙ 5ሺህ በሚጠጉ ገበሬዎች የተሞከረ ሲሆን ፤በብዛት ለማምረት እና ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን የማምረቻ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የቴክኖሎጅ አምራች ኩባንያ በሀገር ውስጥ አለመኖር እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀው ችግሩ ከተፈታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለተጠቃሚ በሰፊው እንደሚደርስ ተናግረዋል።
ተደራሽነቱን በተመለከተ የቻለ ገዝቶ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ገበሬዎች ደግሞ በተመጣጣኝ ክፍያ አገልግሎቱን ለመስጠት በየ አካባቢው የአገልግሎት ማዕከል የመክፈት ዕቅድ ይዘዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።
ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ