1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በጅቡቲ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ጭንቀት

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23 2017

ጅቡቲ ውስጥ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ጭንቀት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ። የጅቡቲ መንሥስት ሕጋዊ የመኖሪያ ሠነድ ሳይኖራቸው በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በፈቃደኝነት ወደየ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሰጠው ጊዜ ነገ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ይጠናቀቃል።

ጅቡቲ ውኃ ዳርቻ
ምስል፦ Solomon Muche/DW

በጅቡቲ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ጭንቀት

This browser does not support the audio element.

ጅቡቲ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ጭንቀት የተጋለጡት የሀገሪቱ መንግሥት የሁሉም ሀገር  ሕገ-ወጥ ስደተኞች  እስከ ነገ ሜይ 2 በፈቃዳቸው ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በጥብቅ በማሳሰቡ ነው። 

32 ዓመታት በጅቡቲ መኖራቸውን የሚገልፁት አቶ ሱልጣን መሐመድ በሀገሪቱ ዜጎች ቀና ትብብር ሱቅ ከፍተው የሚሠራ በርካታ ኢትዮጵያዊ መኖራቸውን በመግለጽ የጅቡቲ ዜጎች ደጋፊያቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል። "አጠቃላይ ጅቡቲ ሲባል ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ሕዝብ አለ። ግን በርካታው የሚኖረው ዘበኝነት ይሠራር፣ የቤት ሠራተኛ ሆኖ ይሠራል፣ ጋራዥ ውስጥ ይሠራል" ብለዋል።


"ማሕበረሰቡ አሁን ጭንቅ ላይ ነው ያለው" አቶ ሱልጣን መሐመድ 

ወይዘሮ ሙና የተባሉ ኢትዮጵያዊት ምንም እንኳን እሳቸው የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው መሆኑን ቢገልፁም የሌሎች ወገናቸው ኹኔታ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ያብራራሉ። "በአጭር ቀን ውስጥ ዕቃችሁን፣ ንብረታችሁን፣ ራሳችሁን ይዛችሁ ውጡ ማለት ምን ያህል እንደሚከብድ እኔ አላውቅም። በጣም ያሳዝናል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጅቡቲ ያለው" ይላሉ። ኢትዮጵያዊያኑ የተሰጠው ጊዜ ገደብ እንዲራዘም የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት አድርጎ በጅቡቲ ላይ ጫና ያድርግልን ብለዋል።

ምስል፦ Solomon Muche/DW

"የሀገሪቱን ሕግ አክብሮ እንዲወጣ የጊዜ ቀጠሮ መጨመር አለበት"

ጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ምዝገባ እያደረገ መሆኑን ከቀናት በፊት አስታውቋል። ኢትዮጵያዊኑ ግን በዚህ አጭር ጊዜ ይህ ሥራ የሚጠናቀቅ አይደለም በሚል አቤት ብለዋል። ትናንት ረቡዕ የተወሰኑ ሰዎች አዲስ አበባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄደው ሥጋታቸውን መግለጻቸውንና የሚቻለውን ለማድረግ "ጥረት እናደርጋለን" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አቶ ሱልጣን ገልፀዋል።

ጅቡቲ "ጸጥታ እና የጤና ችግሮች" የዚህ ውሳኔ መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑ አስታውቃለች። በሀገሪቱ ይኖራሉ ተብሎ ከሚታመኑት ከ200 እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን መካከል ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው በውል ባይታወቅም ጥቂት እንደሆነ ግን ይነገራል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW