በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስሞታ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12 2014
ላለፉት 30 አመታት በጅቡቲ የስደተኞች ካምፕ ተጠልለው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራችን ለመመለስ አስፈላጊውን መስፈርት ብናሟላም ወደ አገራችን መመለስ አልቻልንም ሲሉ አማረሩ። ስደተኞቹ ለDW እንደተናገሩት የመመለስ ሂደቱ በኮረና ስርጭት ምክንያት ቢቋረጥም እስካሁን መፍትሔ አላገኙም።
የመቶ አለቃ አብርሃም ቆኖ በቀድሞው የጦር ሰራዊት አባልነት ሲያገለግሉ ነበር። የደርግ መንግስት መውደቅን ተከትሎ ጅቡቲ በአለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ሥር ተጠልለው መኖር ከጀመሩ ድፍን 30 አመት ሞላቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ከተመሰረተ ቦኋላ እንደሳውዲ ስደተኞች ሁሉ ወደአገራቸው ለመመለስ ከ1ሺ በላይ ስደተኞች መመዝገባቸውን ነግረውናል። እስካሁን ግን መፍትሄ እንዳለገኙ በማከል
በቋሚ በሽታ እንደሚሰቃዩ የነገሩን አቶ አህመድ አብዱላሂ በበኩላቸው የ30 አመታት የስደት ኑሮ አንዳንገሸገሻቸውና ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የዛሬ 30 አመት ወደ ጅቡቲ ሲሰደዱ የ9 አመት ህጻን የነበሩት ወይዘሮ ፋጡማ እንድሪስ እንደሌሎቹ ሁሉ ትመለሳለችሁ ተብለው እስካሁን ቢጠባበቁም ጉዳያቸው ቸል በመባሉ እንደመረራቸው ገልጸውልናል
ለመንግስት ቅርበት ባለቸው መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር የጂቡቲ ስደተኞች በቅርቡ ይመለሳሉ ተብሎ በዜና የተነገረለት ጉዳያችን በኮረና ስርጭት ምክንያት ቢጨናገፍም አሁንም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ወዳገራችን ይመልሰን ብሏል የመቶ አለቃ አብርሃም።
በጉዳዩ ላይ አንድ በቀጥታ ይመለከታቸዋል የተባሉ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባ ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ከሰጡን ቦኋላ በቀጠሮአችን መሰረት ስንደውል ስልክ ባለማንሳት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ