1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ግጭት ሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2015

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ ውስጥ በሃይማኖት ሰበብ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ። በግጭቱ ሰዎች ከመጎዳታቸውም በላይ ሱቆችና የመኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ DW ገልጸዋል ። በከተማው ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በሰዎችና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት ገደብ ተጥሏል ።

Äthiopien | Konflikt in Gunchere
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት ለወራት ሲብላላ ነበር

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ ውስጥ በሃይማኖት ሰበብ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ። በግጭቱ ሰዎች ከመጎዳታቸውም በላይ ሱቆችና የመኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ DW ገልጸዋል ። ግጭቱን ተከትሎ በከተማው ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በሰዎችና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት ገደብ ተጥሏል ። ግጭቱ በአንድ ጊዜ ትናንት ድንገት የተከሰተ ሳይሆን በተማሪዎች ኒቃብ እና ነጠላ እንለብሳለን ፉክክር ለበርካታ ወራት ሲብላላ የቆየ መሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

መረጃዎች እንዳመለከቱት ግጭቱ ከትናንት ጀምሮ የተከሰተው በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በምትገኘው የጉንችሬ ከተማ ውስጥ ነው ። ግጭቱ ሊከሰት የቻለው በሁለት ወጣቶች መካከል የተፈጠረው ፀብ ሃይማኖታዊ መልክ በመያዝ ወደ ማኅበረሰቡ በመዛመቱ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት የከተማይቱ ነዋሪዎች በከተማው ለዘመናት አብረው በኖሩ የእስልምና እና የክርስቲያን ኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮች መካከል ለተከሰተው ግጭት መንስኤ ያሉትን ለዶቼ ቬለ DW ገልጸዋል ።  

የግጭቱ መነሻ የሁለት ወጣቶች ፀብ መሆኑን የጠቀሱት የዐይን አማኞቹ «ትናንት ምሽት ዳቦ ለመግዛት ወደ ሱቅ በመሄድ ላይ በነበሩ ወጣቶች መካከል ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ፀብ ተነሳ ። የሁለቱ ወጣቶች ፀብ ወደ ማኅበረሰቡ በመስፋት ድንጋይ መወራወርና አንዳቸው የሌላኛቸውን ሱቆችና መኖሪያ ቤቶችን የማውደም ድርጊት ፈጽመዋል ። ይህን ተከትሎም ምሽቱን ከፍተኛ የጥይት ድምፅ ሰምተናል» ብለዋል ። 

በግጭቱ በሰው ሕይወት ላይ የሞት አደጋ አለመድረሱን የጠቀሱት የአይን አማኞቹ ነገር ግን ሰዎች መጎዳታቸውንና በሁለቱም ወገኖች ሱቆችና የመኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ተናግረዋል ።  
የወጣቶቹ ፀብ ወደ ማኅበረሰቡ ሊሰፋ የቻለው ቀድሞውኑ በሁለቱ እምነት ተከታይ ወጣቶች መካከል የከረሙ ቁርሾዎች በመኖራቸው የተነሳ መሆኑን የከተማይቱ ነዋሪዎች ተናግረዋል ። በተለይም በከተማው በሚገኘው የጉንችሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች ኒቃብ ፤ የክርስቲያን ኦርቶዶክስ ደግሞ ነጠላ እየለበሱ ወደ መማሪያ ክፍሎች በመግባት የሃይማኖት ፉክክር ያደርጉ ነበር የሚሉት የአይን እማኞቹ ይህ ሁኔታ በሁለት ወጣቶች መካከል የተነሳውን ተራ ፀብ ምክንያት አድርጎ ወደ ትናንቱ ግጭት ሊመራ መቻሉን ገልጸዋል ። 

ዶቼ ቬለ DW በጉንችሬ ከተማ በተከሰው ግጭት ዙሪያ ያነጋገራቸው የጉራጌ ዞን ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮማንደር ጠጄ መሐመድ «ጉዳዩን እያጣራን እንገኛለን» የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል ። 
የጉራጌ ዞን እና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ከተማው በመግባቱ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ መረጋጋት መታየቱ የጠቀሱት ነዋሪዎቹ ከዛሬ ጀምሮ በሰዎችና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የምሽት የሰዓት ገደብ እንደተጣለ በድምፅ ማጉያ መታወጁን ተናግረዋል ። 

ፎቶ ፡ እንአማራጭ ከጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ኮሚኑዩኬሽን የተወሰደ ።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW