በጋምቤላ አምስት ስደተኞች ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ክልሉ ፖሊስ አስታወቀ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 5 2017
በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ዉስጥ የሠፈሩ አምስት የደቡብ ሱዳን ስዴተኞች በታጣቂዎች መገደላቸዉን የአካባቢው ነዋሪዎችና የክልሉ ፖሊስ አስታወቁ፡፡ ስደተኞቹ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ጉኝየል ስደተኞች ጣቢያ የሠፈሩ ነበሩ።ነዋሪዎቹ እንዳስታወቁት ሟቾቹ አምስቱም ሴቶች ናቸዉ።የተገደሉት ከሚኖሩበት ሠፈር አስራ አምስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ጫካ በእንጨት በመልቀም ላይ እንዳሉ ነዉ።የክልሉ ፖሊስ ገዳዮችን ለሕግ ለማቅረብ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡የአሶሳዉ ወኪላችን ነጋሳ ጊዳዳ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል
በክልሉ ከሚገኙ ሰባት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያው መካከል አንዱ በመሆነው ጉኝየል ስዴተኞች ጣቢያ 110ሺ ገደማ ስደተኞች እንደሚኖሩ የስዴተኞችና ተመላሾች አገልግሎት መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህ ስደተኞች ጣቢያ ይኖሩ ነበር የተባሉት አምስት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ባለፈው አርብ በአንድ ጫካ ውስጥ ሞቶ መገኘታቸውን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ አምስቱም ሴቶች መሆናቸውን አንድ አስተያየታቸውን የሰጡን የአካባቢው ነዋሪ አመልክተዋል፡፡
‹‹በጋምቤላ በሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በእጅጉ ቀንሶ ቆይተዋል›› ነዋሪ
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን የአካባቢው ነዋሪም በጋምቤላ የጸጥታ ችግር ተሻሽለው መቆየቱን ገልጸው ባለፉት አምስት ወራት በሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በእጅጉ ቀንሶ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንበበኩሉ አምስት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡጉላ ኡጁሉ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ ሞቶ ተገኙ የተባሉ ስደተኞችን ጉዳይ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው የድርጊቱ ፈጻሚዎችን በመለየት ለህግ ለማቅረብ ከፌደራል ተቋማት በጋራ ጉዳዩ እየተጣራ ነው ብሏል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመበት ስፍራም ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከሶስት እስከ የአራት ሰዓት ርቀት ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽነር ኡጉላ ተናግረዋል፡፡ ከሞቱት አምስት ሰዎች መካከል አራቱ ከስደተኛ ጣቢያ መታወቂያ ያላቸው እንደሆኑም ኮሚሽነሩ አክልዋል፡፡
‹‹የተገደሉ ስደተኞች አምስቱም ሴቶች ናቸው››
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞች ከመጠለያ ውጪ ለእንጨት ለቀማ በተንቀሳቀሱበት ባለፈው ሳምንት አርብ ተገድለው መገኘታቸውን አስታውቋል፡፡ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ መዝገበወርቅ ገብር ማርያም ጉኝየል ካምፕ ይኖሩ የነበሩ አምስት ሴት ስደተኞች ከካምፑ ከ2 እስከ 3 ሰዓት በምርቅ ቦታ ሞቶ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በየካቲት 2016 ዓ.ም የኢትዮጰያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ቦታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በካምፕ ውስጥና ውጭ ለተለያዩ ምክንያቶች ሲንቀሳቀሱ ጥቃቶች እንደተፈጸመባቸውን እና ከዚህ ቀደም ህይወታቸው ያለፈው ስደተኞች እንዳሉም በወቅቱ ባወጣው በዘገባው አመልክተዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል ከ3 መቶ 78 ሺ በላይ ስደተኞች በ7 ጣቢያዎች እንዲገኙ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት መረጃ ያሳያል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ