በጋምቤላ ክልል በኮሌራ በሽታ 30 ሰዉ ሞተ፤ ከ1000 በላይ ታመመ
ማክሰኞ፣ የካቲት 25 2017
በጋምቤላ ክልል በተዛመተዉ የኮሌራ በሽታ ከአንድ ሺህ በላይ ነዋሪዎች መታመማቸዉን የክልሉ የጤና ባለሙያዎችና ባለስልጣናት አስታወቁ።ባለሥልጣናቱ እንዳሉት እስካሁን ድረስ በትንሹ 30 ሰዎች በበሽታዉ ሞተዋል።የክልሉ መንግሥትና የጤና ቢሮ የበሽታዉን መስፋፋት ለመቀነስ እየጣሩ መሆናቸዉን ገልጠዋል።ይሁንና የመድኃኒትና የተሽከርካሪዎች እጠረት መኖሩ በሚፈለገዉ ፍጥነት የበሽታዉን ሥርጭት ለመቀልበስ አልተቻለም።ዓለምነዉ መኮንን ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።
በሽታው በኑዌር ዞን 5 ወረዳዎች ተስፋፍቷል
ከየካቲት 3/2017 ዓ ም የኮሌራ በሽታ በጋምቤላ ክልል መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ በቤተ ሙከራ መረጋገጡን ቀደም ሲል ይፋ አድርጎ ቆይቷል። የበሽታው ስርጭት በተለይም በክልሉ ኑዌር ዞን ከደቡብ ሱዳን ተሻግሮ ወደ አዋሳኝ አኮቦ ወረዳ ሳይገባ እንዳልቀረ ግምት መኖሩን የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋትቤል ግርማል ተናግረዋል። በሽታው ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም ስርጭቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዞኑ 5 ወርዳዎች መስፋፋቱን ነው መምሪያ ኃላፊው ያስረዱት፡፡
እስከ ትናትና በኑዌር ዞን 1002 ሠዎች በበሽታው ተይዘዋል
በተለይ ወደ አኮቦና ዋንቱዋ ወርዳዎች ለመድረስ የመንግድ አለመመቻቸት፣ ከበሽታው ስርጭት መስፋፋት ጋር የምድኃኒት እጥረት፣ የተሽከርካሪ አለመኖር ችግሩን ለመቀልበስ አስቸጋሪ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ በሽታው ከተከሰተበት ከየካቲት 2017 የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስም በበሽታው 1002 ሠዎች የተያዙ ሲሆን 30 ህይወታቸው ማለፉን አቶ ጋትቤል ገልጠዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት በዋንቱዋና በአኮቦ ወረዳዎች የከፋ ነው
በጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ የመድኃኒትና የህክምና ቁጥጥር ዳይሬክተርና የዋንቱዋ ወረዳ የኮሌራ ህክምና አስተባባሪ አቶ ሉል ባንግ በበኩላቸው በወረዳው የበሽታው ስርጭት በስፋት እየታየ እንደሆነና በዋንቱዋ ብቻ 800 ያክል ሠዎች በኮሌራ መታመማቸውን ተናግረዋል፣ 20 ያክሉ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል ነው ያሉት። የግብዓት እጥረቶች ቢኖሩም የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለታመሙት ህክምና ለመስጠትና ህብረተሰቡ የመከላክል ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የተቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ እንደሆንም አስረድተዋል።
በሽታው በጋምቤላ ከተማም ታይቷል
በጋምቤላ ከተማም ከወረዳ መጡ የተባሉ 20 ያክል ታማሚዎች በጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና ወስደው ማገገማቸውንና ሌሎች 2 ታማሚዎች በሆስፒታሉ ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሮን ጎኝ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።
በኑዌር ዞን የጅካዎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንድሪው ቱት በወርዳው በሽታው ቀደም ሲል መከሰቱን አመልክተው ስርጭቱ ከነበረበት አሁን እየቀንስ መሆኑን ገልጠዋል፣ ግብዓት በተፈለገው ፍጥንት እየቀረበ እንዳልነበር ግን አልሸሸጉም፡፡
“የግብዓት አቅርቦት ችግር የለም” የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ
የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኜል የክልሉ መንግሥትና የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ችግሩን ለመቀልበስ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል። የመድኃኒት አቅርቦት የጎላ ችግር እንዳልሆነ ጠቁመው፣ የተሽከርካሪ እጥረት ግን እንደአጠቃላይ በክልሉ ያለ ችግር እንጂ በተወሰን ቦታ የሚጠቀስ እጥረት አይደለም ነው ያሉት።
የኮሌራ በሽታ ከየካቲት 3/2017 ዓ ም ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን አኮቦ፣ ዋንቱዋ፣ ጂካዎ፣ መኮይና ላሬ ወረዳዎች እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ ከ1000 በላይ ሠዎች በበሽታው ተይዘዋል፣ በሽታው ቀደም ሲል ስርጭት ከነበረበት አዋሳኝ ደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ አኮቦ ወረዳ ሳይመጣ እንዳልቀረ ባለስልጣናቱ ይገምታሉ፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ