በጋምቤላ ክልል በደረቅ ሳሙና ምርት የተሰማሩት ደቡብ ሱዳናውያን
ዓርብ፣ ሰኔ 13 2017
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በ ኢትዮጵያጋምቤላ ክልል ይኖራሉ። ጋች እና ናኮም እጎአ በ 2013 ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደዱት ደቡብ ሱዳናውያን መካከል ናቸው። ጋች 31 ዓመቱ ሲሆን ናኮም ደግሞ የ 23 ዓመት ወጣት ናት። ስለ ስደት ኑሯቸው እና እንዴት ራሳቸውን ከሰብአዊ ርዳታ ጥገኝነት እንዳላለቀቁ አጫውተውናል።
የስደት ትውስታ
« ወደ እዚህ የመጣነው ደቡብ ሱዳን ውስጥ በ 2013 በነበረው የእርስር በእርስ ጦርነት ምክንያት ነው። በስደት ላይ ሳለን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR)እና ዓለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት IOM ታደጉን። ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው ህይወታችንን ለማዳን ብለን ነው። » ይላል ጋች።
በጎርጎረሳዊው 2011 ሰኔ ወር ነፃነትዋን የተጎናፀፈችዉ ደቡብ ሱዳን ወደ ዕርስ በእርስ ጦርነት የገባችው ብዙም ሳትቆይ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር። ልክ እንደ ጋች ከእነ ቤተሰቧ በዛን ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የተሰደደችው ናኮም ገና 11 ዓመቷ ነበር። « የማስታውሰው ነገር ስንጓዝ ምንም እቃ አልነበረንም። ድንበር ከደረስን በኋላ ወደ ጀዊ ስደተኞች መጠለያ ገባን። በዛ ወቅት ገና ልጅ ነበርኩ።»
የደረቅ ሳሙና አሰራር ስልጠና
ከሁለት ዓመታት በፊት ናኮምም ሆነች ጋች የሰብዓዊ ርዳታ ላይ ጥገኛ ነበሩ። አሁን ግን በኖርዌይ ቤተክርስቲያን ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ አማካኝነት ሰልጥነው ሳሙና መስራት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ህይወታቸው በመጠኑም ቢሆን ተቀይሯል። « ከዚህ በፊት እንደ ስደተኛ ስንኖር ምንም የምንሰራው ነገር አልነበረም። የራሳችን የገንዘን አቅምም አልነበረንም። የአካባቢው ማህበረሰብም ሳሙና በቀላሉ የሚያገኝበት ሁኔታ አልነበረም። አሁን ግን ሳሙና ከእኛ ያገኛሉ። እኛም የምንፈልገውን ማድረጊያ ገንዘብ እናገኛለን። ስለዚህ ማህበረሰቡ፤ እኛም ሆንን ቡድኑ ትርፋማ የሚሆኑበት አቅም ሊኖረን ችሏል። »
በወቅቱ ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት እና ያስተባበሩት የ NCA ወይም የኖርዌይ ቤተክርስቲያን ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ ባልደረባ አቶ በቃሉ ዳኜ ናቸው።
የኖርዌይ ቤተክርስቲያን ተራድኦ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት እንደ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻ የመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ሲሰራ የቆየ ድርጅት ነው። ይህ የሳሙና ፕሮጀክት ደግሞ ተራድኦ ድርጅቱ የህብረተሰቡን እና የስደተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ብሎ ከጀመራቸው መርኃ ግብሮች አንዱ እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ የገለፁት አቶ በቃሉ ስለ ፕሮጀክቱ አጀማመሩን በተመለከተ ሲናገሩ « ፕሮጀክቱ ጀዊ የሚባል የስደተኛ ጣቢያ ውስጥ ነው። ጋምቤላ ክልል ውስጥ ይገኛል። ከ 68 ሺ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ተጠልለውበት የሚገኙበት መጠለያ ነው። እዛ እኔ የምሰራበት ድርጅት የውኃ፤ የአካባቢ እና የግል ንፅህናን የተመለከቱ ፕሮጀክቶች ይሰራል። አንደኛው የማህበረሰቡ ችግር የነበረው ሳሙና የማግኘት ችግር ነበር።»
ችግር መፍትሔ ሲወልድ
በዚህም ምክንያት ስደተኞቹ ከሌላ ቦታ ተገዝቶ የሚመጣውን ሳሙና ራሳቸው ተደራጅተው ማምረት የሚችሉበት መንገድ ሊመቻች ችሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት በጀመረው ፕሮጀክት ዛሬ ጋች እና ናኮምን ጨምሮ 50 ስደተኞች ተሳታፊ ናቸው።« 27 ቱ ወንዶች ናቸው። 23 ደግሞ ሴቶች ነን። የአንድ ወር ስልጠና ወስደናል። 15 ቀናት የቃል ትምህርት ፤ 15ቱ ደግሞ በተግባር። ስትል ናኮም ታስረዳለች።
ዛሬ ናኮም «ጎበዝ ሳሙና ሰሪ» ሆኛለሁ ትላለች። ጋችም እንዲሁ፤ ምንም እንኳን ጋች ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቅ የነበረ ቢሆንም በተማረበት የስራ መስክ ስራ አላገኘም ነበር። « ከዚህ በፊት ሳሙና እንዴት እንደሚመረት አናውቅም ነበር። » የሚለው ጋች «የወደፊት እቅዴ ልጆቼን የማስተዳድርበት እና ማህበረዘቡን የማግዝበት፣ የግል ቢዝነስ እንዲኖረኝ መስራት ነው። ወደ ደቡብ ሱዳን ብመለስ እንኳን ይህንን ስራ እዛ ለመጀመር ሀሳብ አለኝ።» ይላል።
ጋች ዛሬ የሁለት ወንዶች እና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው። የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮቹ እንደገለፁልን ምንም እንኳን በስደተኝነት በርካታ አመታትን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያሳልፉም ሁለቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገር ማንኛውንም ቋንቋ አይችሉም። ስለሆነም እንግሊዘኛ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ብቸኛው መግባቢያ ቋንቋቸው ነው። « ለመጀመሪያ ጊዜ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት እየኖርን ነው። እነሱ ወደ ካምፕ ይመጡ እና ያለንን ገዝተው ወደ መጡበት ይመለሳሉ። እኛም እነሱ ያላቸውን እንገዛለን። እና በአሁኑ ሰዓት ጥሩ የተዋሀደ አኗኗር ነው ያለው።»
በአሁኑ ሰዓት እያንዳንዳቸው የሳሙና አምራች አባላት ከ 1800 እስከ 2200 ብር ድረስ የወር ገቢ እንዳላቸው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የነበሩት አቶ በቃሉ ገልጸውልናል። «በስደተኛ ጣቢያ ውስጥ ሳሙና መመረቱ ለበርካታ በጣቢያው የሚኖሩ ወጣቶች የስራ እድል ብቻ ሳይሆን የፈጠረው ሌሎች ወጣቶችም በፈጠራ ስራ እንዲሰማሩ በር ከፋች» ሆኗልም ይላሉ።
የስደተኞች የመስራት መብት
ወጣቶቹም በሁለት አመት እድሜ ውስጥ 170 000 የሚደርሱ ሳሙናዎችን ማምረት ችለዋል። ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆ የገንዘብ ድጋፍ ካደረገው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት (UNHCR) በተጨማሪ የኖርዌይ ቤተክርስቲያን ተራድኦ ድርጅቱ ፕሮጀክቱን ለመተግበር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስራት ነበረበት። ይህም የስደተኞችን የስራ ፍቃድ በተመለከተ ነው። « ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋት ለስደተኞች ስራ ሰርቶ ገቢ የማግኘት መብትን ሰጥታለች። (እጎአ በ2019) እና መንግሥት የመስራት እድል ሰጥቷቸው ነው። የስደተኛ ጣቢያ ውስጥ በጣም ወጣት አምራች ኃይል አለ። እና ይህንን አምራች ኃይል ወደ ስራ ማስገባት እና እንዲሳተፋ ማድረግ እዛ የሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ ለአካባቢው አስተዋፅዎ ያደርጋል። ተረጅነትንም ያስቀራል። እንዲሁም ደግሞ የሚመረተው ምርትም ለአካባቢው ማህበረሰብ ወጥቶ ይሸጣል። ያ ከአካባቢው ማህበረሰቡ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እና ሰላማዊ መስተጋብርም ያሻሽላል።»
በደረቅ ሳሙና ምርት የተሰማራው ደቡብ ሱዳናዊ ጋች ለወጣቶች ማስተላለፍ የሚፈልገው አንድ መልዕክት አለው፣ «ወጣቶች ቢዝነስ የማራመድ ሀሳቦች አሏቸው። ወጣቶች ጠቅላላ ማህበረሰቡ ትርፋማ ሊሆን የሚችልበት ነገር መፍጠር ይችላሉ። ስለዚህ እያንዳንዳቸውን መደገፍ ያሻል። ምናልባት ቢዝነዝ የሚጀምሩበት በቂ ገንዘብ የላቸውም። ሁለቱን አንድ ላይ እስካላደረግን ድረስ በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልም። ስለዚህ አንድ ላይ እንስራ። እንደጋገፍ ነው የምለው።»