በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ በደረሰው ጥቃት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2016
በጋምቤላ ክልል አኙዋ ብሔረሰብ ዞን አቦቦ ወረዳ ውስጥ ከትናንት በስተያ ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ሀይሎች ባረደረሱት ጥቃት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናገሩ። በደረሰው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ሦስቱ ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ሴት እንደሆኑም ገልጸዋል። በጥቃቱ ሦስቱ በስለት መሣሪያ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን አንዱ ደግሞ በሚሊሻ ሀይሎች በተተኮሰው ተባራሪ ጥይት ሕይወቱ ማለፉ ተነግሯል። የጋምቤላ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን በበኩሉ በወረዳው የሰዎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠው ጥቃት አድርሾችን ለመያዝ በጸጥታ ሀይሎች ክትትል እየተደረገ ነው ሲል አስታውቋል።
በአቦቦ መንደር 17 በ1977 ዓ.ም የሰፈሩ የከንባታ ማኅበረሰብ በብዛት ይኖራሉ
በአኙ ብሔረሰብ ዞን አቦቦ ወረዳ መንደር 17 በሚባል ስፍራ ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች በከብት ጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩና፤ አንድ ሰው ደግሞ በተባራሪ ጥይት ተመቶ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል። ከወረዳው መንደር 17 አስተያየታቸውን የሰጡት የዓይን እማኝ ጥቃቱ በሰፈራ ጣቢያ የሚኖሩ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጸው በአካባቢው በከብትና ሌሎች የቁም እንስሳት የሚዘርፉ ሀይሎች ጥቃቱን ሳያደርሱ እንዳልቀረ ጠቁመዋል። እነዚሁ ሀይሎች ጥቃት ያደረሱቱም በስለታማ መሣሪያዎች እንደሆነም አብራርተዋል።
ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በአቦቦ ወረዳ ደርሷል በተባለው ጥቃት የ16 ዓመት ልጃቸው ሕይወት ማለፍን የነገሩን ሌላው ነዋሪም ጥቃቱ የደረሰው ከቀኑ 9 ፡00 ሰዓት ገደማ መሆኑን ገልጸዋል።፡ ልጃቸው የ8ኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን የነገሩን ነዋሪው በከብት ጥበቃ ላይ ተሰማርቶ በነበረበት ወቅት ማንነታቸውን በውል ያልገለጹት ሀይሎች ባደረሱበት ጥቃት ሕይወቱ ማለፉን አመልክተዋል። ልጃቸውን ጨምሮ ሕወታቸው ያለፈው አራቱም ሰዎች ሰርዓተ ቀብር በትናንትናው ዕለት መፈጸሙንም ገልጸዋል። በስፍራው ከዚህ ቀደምም አልፎ አልፎ የቁም እንስሳት የሚዘርፉ ሽፍቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። እንደነዚህ ዓይነት ድንገተኛ ጥቃቶችን ለመከላከል በአካባቢው በቂ የሚሊሻ አባላት መሰማራት አለባቸውም ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በአኙዋ ብሔረሰብ ዞን አቦቦ ወረዳ ያልታወቁ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት የአራት የሰዎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። የጥቃት አድራሾች ማንነት እንደማይታወቅ የገለጹት ኃላፊው በአካባቢው የጸጥታ ሀይሎች ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ፤ ነገር ግን እስካሁን የተያዘ ተጠርጣሪ አለመኖሩን አብራርተዋል።
በጋምቤላ ክልል በሙርሌ ታጣቂዎችና በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶች በሰው እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ሲዘገብ ቆይቷል። በተለይም ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም አንስቶ በክልሉ ዋና ከተማ አካባቢና ኢታንግ ልዩ ወረዳ የተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የክልሉ መንግሥት በወቅቱ ገልጿል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ