በጋምቤላ ክልል የኮሌራ ስርጭት እየጨመረ ነው
ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017
የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ነው
በጋምቤላ ክልል ኑዌር ብሔረሰብ ዞን ውስጥ በስፋት እየተስተዋለ ነው የተባለው የኮሌራ በሽታ የስርጭቱን አድማስ በማስፋት በጋምቤላ ከተማ እና ሶስት የስደተኞች ጣቢያዎች ውስጥ በሽታው መከሰቱን የክልሉ መንግስት አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ መሰረት እስካሁን በክልሉ ደረጃ ከ3 መቶ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ይፋ ተደርገዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል እስከ ትናንት ምሽት በዋንቱዋ ወረዳ በጤና ተቋማት ውስጥ በበሽታው የሰው ህይወት ማለፉን ያነጋርናቸው ጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ በኮሌራ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ለማከም የሚያስችል የተለያዩ ጊዜያዊ ማከሚያ ቦታዎች ተዘጋጅቶ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡የኮሌራ በሽታ በጋምቤላ ኑዌር ዞን መከሰቱ ተረጋገጠ
በጋምቤላ ክልል እስካሁን 23 ሰዎች በበሽታው ህይወታቸው ማለፉን በዝርዝር የተናገሩት አንድ የጤና ባለሙያ በሽታውን ለመከላከል አንድ የግል ተቋም ድጋፍ ማድረጉን እና በዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ የተደረገላቸውን ስፍራዎች የህክምና ድጋፍ መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን አጎራባች በሆነው አኮቦ በተባለ ወረዳ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ መከሰቱን የተነገረው በሽታው በብዛት ብዙ ሰዎች የተጠቁት ደግሞ ዋንቱዋ የተባለ ወረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አብዛኛው ሰዎች በበሽታው ክፉኛ ከተጎዱ በኀላ ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚመጡ በመጥቀስ ከክልና ሌሎች ዞኖች የጤና ባለሙያዎችም ለህክምና እገዛ በተለያዩ ቦታዎች እንዲሰማሩ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡በጋምቤላ ኮሌራ መሰል በተባለ በሽታ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ
ከ3 መቶ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል
በጋምቤላ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ አስመክልቶ መረጃን እንዲሰጡን ከክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ኃላፊ ኝኪዎ ጊሎ ከዚህ ቀደም በሰጡን መረጃ በክልሉ በሽታውን ስርጭት ለመከላል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ በበሽታው የደረሰውን ጉዳት ግን ለጊዜው መግለጽ አልፈለጉም፡፡
የክልሉ መንግስት ከአምስት ቀን በፊት የካቲት 15/2017 ዓ.ም በሽታው ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ 334 ሰዎች በበሽታው መጠቃቻውንና 15 ሰዎች ደግሞ ህይወት ማለፉን አመልክተዋል፡፡ ስርጭቱም ስደተኞች ካምፕን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መስፋፋቱን የክልሉ መንግስት መረጃ ያመልክታል፡፡ ከዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ በተጨማሪም በሽታውን ለመከላል የክልሉ መንግስት 5 ሚሊዩን ብር መድቦ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጸዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር