በጋምቤላ የደረሰው ጥቃት
ዓርብ፣ ጳጉሜን 3 2015በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ጎዳሬ ወረዳ እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ያልታወቁ የተባሉ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ዞኑ አስታወቀ። የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ገደሙ በስልክ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት በወረዳው በተከተሰው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋማት ተዘግተው ቆይተዋል። በአሁኑ ጊዜ በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል ማጃንጃግ ብሔረሰብ ዞን ጎዳሬ ወረዳ ባለፈው ሳምንት እሑድ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተዘግተው መቆየታቸውን ተናግረዋል። በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት መጠን ሊጨምር እንደሚችልም ነዋሪው አመልክተዋል። እሑድ ዕለት የደረሰው ጥቃት ወደ ዞን ዋና ከተማው መጢ ከተማ በመስፋፋቱ የፈዴራል ጸጥታ ኃይሎች ወደ ስፋራው መሰማራታቸውን አክለዋል። በዛሬው ዕለትም በወረዳው ያለው የጸጥታ ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑንም ተናግረዋል።
የማጃንግ ዞን ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳር በበኩሉ ከዞኑ ከተማ መጢ ከተማ በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ አካሺና ጎሽሜ በተባሉ ቀበሌዎች መካከል በሚገኝ አንድ ስፍራ ጥቃቱ መድረሱን አብራርተዋል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ገዳሙ በደረሰው ጥቃት በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ በስለታማ መሣሪያዎች ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ማንነታቸው በውል ያልታወቀ የተደራጁ ቡድኖች በስፍራው ጥቃት መፈጸማቸውንና ጉዳዩ የብሔር መልክ መያዙንም ጠቁመዋል።
ከባለፈው እሑድ አንስቶ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ዝግ ሆኖ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በአካባቢው የተሰማራው የጸጥታ ኃይል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር መቆጣጠሩንና የአካባቢውን ማኅበረሰብም ማወያየቱን አስታውቋል። በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን በመለየት ለሕግ ለማቅረብ ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር እየተሠራ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ አመልክተዋል። ከሐሙስ ዕለት ጀምሮም ባንክን ጨምሮ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ሥራ መጀመራቸውን አክለዋል።
በጎዳሬ ወረዳ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ኮሙነኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አመልክቷል። በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ተሻግሮ ጥቃት የሚያደርሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎችን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ በሚፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሚሊዮን የሚገመት ንብረትም ውድሟል። በጋምቤላ ከተማ ኢንታንግ ልዩ ወረዳ በሐምሌ 11 በተከሰተው ጸጥታ ችግር በሰው እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል። ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም የጸጥታ ችግሩን ለመቆጣጠር ሲባል የክልሉ መንግሥት የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ