በጋምቤላ ዲማ ወረዳ የቻይናውያንን ጨምሮ በርካታ የወርቅ አምራቾች እና ነጋዴዎች ፈቃድ ተሰረዘ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 2015
የወርቅ ሀብት ካለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዱ የጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ ሲሆን ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በወርቅ ማውጣት ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በጋምቤላ ክልል የዲማ ወረዳ ማዕድን ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኡቦንግ ኡቶው ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ግን የተሰጣቸውን ፈቃድ ለህገወጥ ተግባር አውለዋል የተባሉና በወርቅ ማውጣት ሥራ ተሰማርተው የነበሩ አካላት ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡
እንደ አቶ ኡቦንግ በወረዳው ከነበሩ 47 አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ውስጥ 36ቱ የተሰጣቸው ፈቃድ ተሰርዞ ከስራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፣በወርቅ ግብይት ማእከል ከተሰማሩት 34 ማዕከላት መካከል 33 በህገወጥ ስራ ተሰማርተው በመገኘታቸው ፈቃዳቸው መሰረዙንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ያመረቱትን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መላክ ያልቻሉ 18 ቻይናውን ፈቃዳቸው ተሰርዟል፣ የወርቅ መፍጫ ባለቤቶች የመጨረሻ መስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፣ የሌሎች የወርቅ መመርመሪያ መሳሪያዎች ደረጃቸው እንደገና እንዲመረመር ህጋዊነታቸው እንዲረጋገጥ መወሰኑንም አቶ ኡቦንግ ተናግረዋል፡፡
ውሳኔው በወረዳው ኮማንድ ፖስት ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑንም አብራርተዋል፡፡ በወረዳው የሚመረተው ወርቅ ህጋዊነቱን ተከትሎ እንዲመረትና ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲላክ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡም ተመልክቷል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ