1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ ጎርፍ ከ185 ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቀለ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 17 2015

በጋምቤላ ክልል በጣለው ከፍተኛ ዝናብ በተከሰተው ጎርፍ ከ185 ሺህ በላይ ህዝብ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እና የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር አስታወቁ ። ተፈናቃዩች በከባድ ችግር ውስጥ ናቸው ተብሏል።

Äthiopien | Überschwemmung in der Region Gambela
በጋምቤላ ክልል የደረሰ የጎርፍ አደጋ ምስል Itang woreda administration

ከባድ የንብረት ውድመትም አድርሷል

This browser does not support the audio element.

 ጋምቤላ ክልል ውስጥ ከሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት 12 ወረዳዎች ላይ በተከሰተው  ከፍተኛ መጠን ያለው ጎርፍ  ከ185,000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደ ተፈናቀሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት OCHA በዚህ ሳምንት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። ኦቻ (OCHA) በዘገባው ተፈናቃዩቹ ባለባቸው የምግብ እጥረት የተነሳ ስራስር እና ቅጠላቅጠልን እየተመገቡ ነው ሲል ገልጿል።  የጋምቤላ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋድቤል ሙን  በበኩላቸው የወጣው የተፈናቃዩች ቁጥር ትክክል መሆኑን አረጋግጠዋል። እንደ ኃላፊው ገለፃ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተከሰተው ከፍተኛ በጎርፍ ምክንያት ነዋሪዎች እየተቸገሩ ነው ተብሏል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቀንድ ከብቶች እንደሞቱ የተናገሩት ኃላፊው እርዳታ እንዲደርሰን እየተደረገ ቢሆንም አሁንም የምናገኘው እህል ካለው ሰው ተፈናቃይ ጋር ሲነፃፀር  በቂ አይደለም ነው ያሉት። በደረሰው ጎርፍ የጤና ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

« ሐምሌ 17 ቀን ነው ጎርፉ የተከሰተው ከ185 000 ሺህ በላይ ሰዎች ከ 11ወረዳዎች ተፈናቅለዋል  ። የክልሉ መንግሥት የተወሰነ 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርግዋል። እንዲሁም የፌደራል መንግሥት 4 ጊዜ በተከታታይ ምግብ ነክ የሆኑ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ ልኳል። በዩኒሴፍ በኩል የተወሰነ እርዳታ አለ ቢሆንም በቂ አይደለም ያሉት አቶ ጋድቤል «በርካታ የእህል ሰብል እና ከብቶች በጎርፉ ተወስደዋል አብዛኛው ማህበረሰብ በበቆሎ ምርት ነው ሚተዳደረው የተከመረም እህል ይሁን በእርሻ ላይ የነበረው ወድምዋል» ብለዋል።


ከአስራ ሁለት የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር  ጋር ከመኖሪያቸው ተፈናቀለው በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት አቶ ተስላጅ ኡር  አሁን ስለሚገኙበት  ሁኔታ ጠይቀናቸው ፤ «በመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው ተጠልለን ነው ያለነው ምክንያቱም ቤታችን ውኃ ነው» ብለዋል። እርዳታ በበቂ ሁኔታ እየደረሳቸው ስላለመሆኑም «በቂ እርዳታ አላገኘንም መንግሥት ትንሽ ነው ያመጣው ለሁሉም ሰው አልደረሰም በጣም ከባድ ሁኔታ ላይ ነን ያለነው ኅብረተሰቡ እየታመመ ነው።»  ነው ያሉት።  


የጂካዎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቻል አሁር በወረዳቸው የሚገኙ 28 ቀበሌዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሙሉ በሙሉ ተፈናቅለው ነው ሚገኙት ብለዋል። «ሙሉ ለሙሉ የ28 ቀበሌ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል ወደ ሌላ ቦታ ሄደዋል  እስካሁን አልተመለሱም» ሲሉ እርዳታ ላይ ያለውንም ችግር አልሸሸጉም። « እርዳታ በበቂ  ሁኔታ እየደረሰ አይደለም ። ህክምናም ቢሆን የተወሰኑ ደርሰዋል ግን በቂ አይደለም። የከብት እንስሳት መድኃኒት በጭራሽ የለም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነን ያለነው ። ወባ በጣም ነው እንደወረርሽኝ የተከሰተው» ብለዋል። 

በጋምቤላ ክልል ተከስቶ የነበር የጎርፍ አደጋ ምስል Itang woreda administration


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኦቻ ትናንት ባወጣው ዘገባ 72 በመቶ የሚሆነው ሰብል በጎርፉ መዉደሙን 8 በመቶ የሚሆን የቤት እንስሳትም መሞታቸዉን ገልጿል።  77 የጤና ተቋማት በጎርፉ ምክንያት አገልግሎት መስጠት እንዳቆሙ ሲገልጽ ማኅበረሰቡ በውኃ ወለድ እና በንጽህና ጉድለት በሚከሰቱ  በሽታዎች ሊጠቁ እንደሚችሉ ስጋቱን አመልክቷል።

ማኅሌት ፋሲል 
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW