በጋሞ ዞን የተፈጸመ የሕጻናት አሰቃቂ ግድያ ኢዜማን ከአካባቢው ባለሥልጣናት ለምን አወዛገበ?
ሰኞ፣ መጋቢት 22 2017
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሁለት ህጻናት ባለፈው ቅዳሜ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የወረዳው የፀጥታ ሃላፊዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ “በቡድን የተደራጁ “ ያላቸው አካላት በወረዳው ዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ ግድያውን የፈጸሙት ህጻናቱን በቤት ውስጥ አስገብተው በመቆለፍ በእሳት እንዲቃጠሉ በማድረግ ነው ብሏል።
ሕይወታቸው ያለፈው የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የአራት እና የሰባት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናት መሆናቸውን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኮሜ ኮታ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡
ግድያውን ማን ፈፀመው ?
“ሕጻናቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዘግናኝ ፣ ከሰብአዊነት ያፈነገጠ እና አረመኔያዊ ነው “ ያሉት አቶ ኮሜ ጥቃት አድራሾቹ በዛው ቀበሌ በአንድ የወረዳ አመራር መኖሪያ ቤት ላይም የተኩስ ሩምታ ከፍተዋል ፡፡ ነገር ግን በህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም በመኖሪያ ቤቱ ላይ ግን መለስተኛ ውድመት አድርሰዋል “ ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሁለት ህጻናት ተገደሉ
በአሁኑ ወቅት የጋሞ ዞን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ አካላት በአካባቢው ተሠማርተው የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኮሜ ገልጸዋል ፡፡ እስከአሁን ከዋነኛ የድርጊቱ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የተያዘ መሆኑንም የጠቀሱት ሃላፊው “ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየተሠራ ይገኛል ፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙት ከመዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ናቸው “ ብለዋል ፡፡
የወረዳው መስተዳድር እና የኢዜማ እሰጥ-አገባ
በወረዳ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት ሁለቱ ህጻናት አሟሟት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ መስተዳድር እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማን ውዝግበ ውስጥ ከቷል ፡፡ ውዝግቡ የተነሳው የወረዳው መስተዳድር “ ከድርጊቱ ጀርባ የኢዜማ ጽንፈኛ አባላት እጅ አለበት “ ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡ የወረዳው መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት የህጻናቱን ግድያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን የፈጸሙት “ ጽንፈኛ “ ሲል የጠራቸው የኢዜማ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ናቸው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ በበኩሉ በወረዳው መንግሥት ኮሚኒኬሽን የሥም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ “ ወረዳው ወንጀሉን በህጋዊ መንገድ መመርመር ሲገባው ወደ ጅምላ ፍረጃ ግብቷል “ ሲሉ ነው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት፡፡
በ2013 ዓም በተደረገው ምርጫ ኢዜማ በአካባቢው የገዢውን ፓርቲ እጩ በማሸነፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን ያስታወሱት ዶክተር ሙሉዓለም “ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአባላቶቻችን እና በደጋፊዎቻችን ላይ ጫና እየተደረገ ይገኛል ፡፡ በሰበብ አስባቡ የማሰር ሁኔታም ይስተዋላል “ ብለዋል ፡፡
የወረዳው መስተዳድር ምላሽ
በኢዜማ የቅሬታ መግለጫ ዙሪያ ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጡ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሶፌኒያስ ቲቶስ ኢዜማ የራሱ ራዕይና ሜኒፌስቶ ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ መሆኑን በመጥቀስ “ነገር ግን በዘይሴ አካባቢ የሚገኙ አባላቱ እና አመራሮች ከፓርቲው ሰላማዊ መርህ ውጭ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፡፡
ባለፈው ምርጫ ደምፅ ከሰጣችሁን የዘይሴ ማህበረሰብ የራሱን ወረዳ እንዲመሠርት እናደርጋለን ሲሉ የነበረውን አሁን በአካባቢው ትርምስ በመፈጠር ለማስፈጸም እየሠሩ ይገኛሉ ፡፡ የቅዳሜውን ግድያ የፈጸሙት ታጥቀው በዙሪያው በሚገኙ ጫካዎች ውስጥ የመሸጉ በሥም የሚታወቁ የዚሁ ፓርቲው አባላት ናቸው ፡፡ መንግሥት የወረዳውን ሰላም የመጠበቅና በፓርቲ ሽፋን ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን በህግ ለመጠየቅ እየሠራ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ