1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በበርካታ የአውሮጳ ከተሞች ሰልፎች መካሄዳቸው

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2016

የቀጠለው የእስራኤል ሃማስ ግጭት የመላውን ዓለም ትኩረት እንደሳበ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ በአውሮጳ ሕብረት መዲና ብራስልስ ጨምሮ በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ሃማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ከባድ ጥቃት፤ እስራኤልም በአጸፋው በጋዛ የከፈተችውን ጥቃት በማውገዝ ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል።

ብራስልስ፤ በአውሮጳ ኅብረት ፊት ለፊት የተካሄደው ሰልፍ
በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ከተሞች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከተካሄዱት ሰልፎች አንዱ፤ በብራስልስ የተደረገው ነው ብራስልስ፤ በአውሮጳ ኅብረት ፊት ለፊት የተካሄደው ሰልፍምስል Omar Havana/AP Photo

በአውሮጳ የተካሄዱት ሰልፎች

This browser does not support the audio element.

 

ያለፉት ቅዳሜና እሑድ የአውሮጳ ከተሞች በጋዛ፤ ባስቸኳይ የተኩስ ቁም እንዲደረግና ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ በመጠየቅ በርካታ ሰልፈኞች ድምጻቸውን አሰምተዋል። በሎንደን፤ በርሊን፤ ሮም፤ ፈረንሳይ ማርሴል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየአደባባዮቹ በመውጣት  ሀማስ በእስራኤል ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸመውን ጥቃትና የእስራኤል መንግሥት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ በብዙ ሺህ ስለማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱንና ከተማዋን ማወደሙን አጥብቅው አውግዘዋል። ቅዳሜ ዕለት በሎንደን  ለፍልስጤም ህዝብ ድጋፍ የወጣው ህዝብ ብዛት ከአንድ መቶ ሺህ  የሚበልጥ እንደነበር ከፖሊስ የተገኘውን መረጃ ጠቅሰው ጋዜጦች ዘግበዋል።

በትናንቱ ዕለት በብራስልስ የተደረገው ሰልፍም እንደዚሁ በዋናነት በጋዛ እየተፈጸመ ያለው የቦምብ ድብደባ እንዲቆምና የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቁ ድምጾች ናቸው ሲሰሙበት የዋሉት። «ፍልስጤም ነጻ ይሁን! ጋዛ ነጻ ይሁን፣ በፍልስጤም ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ያብቃ! የተኩስ ማቁም ስምምነት አሁኑኑ!» የሚሉት ሲስተጋቡ የዋሉ መፍክሮች ናቸው። ሰልፉን ያስተባበሩት በቤልጀየም ያሉ ከ30 በላይ የሚሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማሕበራትና የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እንደሆኑ ተገልጿል። ከአስተባባሪዎቹ አንዷ የሆኑት አስራ አንድ አስራ አንድ የተባለው ድርጅት ተወካይ ወይዘሪት ናታሊን ጃን፤  የስልፉን አላማ፤ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎችና ያስተላለፏቸውን መልክቶች ለዶቼ ቬለ ሲናገሩ «እዚህ የመጣነው  በቤልጅየም ሲቪል ድርጅቶች ስም ለቤልጀየም መንግሥትና የአውሮጳ ሕብረት በሃማስና ኢስራኤል መክከል ባስቸኳይ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ ገፊትና ተጽኖ እንዲያደርጉ ለመጠየቅ ነው። የእስራኤል የቅኝ አገዛዝ መሰልና የዘር አድልዎ ፖሊሲ የችግሩ ምንጭ መሆኑ ታውቆም ችግሩ እንዲፈታ ለመጠየቅ ነው » በማለት የፍልስጤም ችግር የቆየና ያደረ ግን ችላ የተባለ መሆኑን  አንስተዋል። ሌላዋ ሄይዲ የተባሉት የስልፉ አስተባባሪና ተሳታፊ እንደዚሁ፤ « ዛሬ እዚህ የተገኘነው በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለመቃወም ነው። ከሰላሳ  ሺህ ህዝብ ለላይ ዛሬ እዚህ ተገኝቶ፤ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግና ለጋዛ ሰብአዊ እርዳታ እዲገባ፤ የጋዛ ህዝብም በመንግሥታቱ  ድርጅት ጥበቃ እንዲደረግለት ተጠይቋል» ብለዋል። ስልፉ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎችና ትውልዳቸውም ከብዙ አገሮች የሆኑ የቤልጅየም ብራስልስ ነዋሪዎች የተሣተፉበት ነበር። ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኑርዲን ግርማ ከሰልፉ ተስታፊዎች አንዱ የነበር ሲሆን  በጋዛ እየተፈጸመ ያው ኢሰብአዊ  ድርጊት አስቆጥቶት ወደ ሰልፉ እንደመጣ እሱም ለዶቼ ቬለ አስረድቷል። ሀማስ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰላማዊ የእስራኤል ዜጎች ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከ1,400 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን ፤ እስራኤል ባጸፋው በጋዛ ላይ እየወሰደችው ባለው ወታደራዊ  እርምጃ እስከ 5,000 የሚደርሱ ብዙዎቹ ሕጻናትና ሴቶች የሆኑ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ እየተገለጸ ነው። አውሮጳ በችግሩ ላይ አንድ አይነትና ሚዛናዊ አቋም በመውሰድ የመፍትሄው አካል አልሆነም በማለት የሚተች ሲሆን፤ በሳምንቱ  መጨረሽ የሚደረገው የ27ቱ አባል መንግሥታት የመሪዎች ጉባኤ አይነተኛ አጀንዳም ይኸው የእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ጋዛ ውስጥ ራፋ ላይ ምሽቱን ጥቃት የተፈጸመበት አካባቢ ቢያንስ 55 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ተነግሯል። ፎቶ፤ ጋዛ ራፋ ምስል Said Khatib/AFP

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW