1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግጭት የታጀበው የኤርትራውያን የባህል ዝግጅት በጊሰን፣ ጀርመን

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 8 2015

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት በጀርመኗ ጊሰን ከተማ የተካሄደው የኤርትራውያን የባህል ድግስ ግጭት በመፈጠሩ አነጋጋሪ ሆኗል። ፀጥታ ለማስከበር ከተሰማሩ ፖሊሶች ከ20 በላይ ተጎድተዋል። የጀርመን መንግሥት ሰኞ ዕለት ከፖሊስ ጋር የተፈጠረውን ግብግብ እና ያስከተለውን ጉዳት በመግለጽ ድርጊቱን አውግዟል።

Eritrea-Festival in Gießen
ምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

የጊሰኑ የኤርትራውያን በዓል

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት በጀርመኗ ጊሰን ከተማ የተካሄደው የኤርትራውያን የባህል ድግስ ግጭት  በመፈጠሩ  አነጋጋሪ ሆኗል። የጀርመን መንግሥት ሰኞ ዕለት ከፖሊስ ጋር የተፈጠረውን ግብግብ እና ያስከተለውን ጉዳት በመግለጽ ድርጊቱን አውግዟል። ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከበዓሉ አስቀድሞ 80 ሺህ ነዋሪ ባለባት ጊሰን ከተማ አንድ ሺህ የሚገመቱ ፖሊሶች ለጥበቃ እና ጥንቃቄ ተሰማርተው ነበር። በየዓመቱ የሚካሄደው በአል አዘጋጅ በጀርመን የኤርትራውያን ማዕከላዊ ምክር ቤት ሲሆን፤ አዘጋጆቹን በኤርትራ መንግሥት ደጋፊነት የሚከሱት የዝግጅቱ ተቃዋሚዎች ወደ ስፍራው ለመግባት ሲሞክሩ ከፖሊሶች ጋር መጋጨታቸውን፤ ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ እና ውኃ ተጠቅሞ ለመበተን ሲሞክር በድንጋይ እና ጠርሙስ ውርወራ 26 ፖሊሶች መጎዳታቸውን ፖሊስ በትዊተር ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። ከዚያም ፖሊሶች ዱላና የሚረጭ በርበሬ ለመጠቀም መገደዳቸውም ተነግሯል። ፖሊሶቹ የደረሰባቸው ጉዳትም የከፋ ባለመሆኑ ወደሥራ መመለሳቸውም ተገልጿል። የጀርመን የዜና ወኪል ዲፔአ እንደዘገበው በተሳታፊዎችም ሆነ በአላፊ አግዳሚው ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተሰማ ነገር የለም። በወቅቱም ከመቶ በላይ የሚሆኑት የብጥብጡ ተሳታፊዎች መታሰራቸውና ሰላምን በማደፍረስ ክስ እንደተመሰረተባቸው የፌደራል ጀርመን ፖሊስ አስታውቋል። የኤርትራውያን የባህል ድግስ በብጥብጥ መታጀቡን አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠመ ያስታውሳሉ። ሁኔታው ያሰጋው የጊሰን ከተማ አስተዳደርም የባህል ድግሱ በከተማው እንዳይካሄድ በፍርድ ቤት ለማሳገድ ሞክሮ እንዳልተሳካለትም ያመለክታሉ።

 የጀርመን ኤርትራውያን ማኅበረሰብ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በዓሉን ለማደናቀፍ በርካታ ጥረት ቢደረግም፤ «በተሳካ ሁኔታ» መካሄዱን ያመለክታል። ዝግጅቱ በውጪ የሚኖሩ ኤርትራውያን ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን ለማክበር፤ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸውን እንዲሁም የድሮ ወዳጆቻቸውን ለማግኘት የሚሰባሰቡበት፤ ጀርመኖችም ሆኑ ሌሎች ተጋባዥ የውጪ ዜጎች የሚገኙበት መድረክ እንደሆነ ነው የገለጸው። ከጎርጎሪሳዊው 2011 ጀምሮም በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ሲቀር ጊሰን ከተማ ላይ ለ11ኛ ጊዜ ያለምንም ችግር በሰላም መዘጋጀቱንም ጠቁሟል። ይኽ በዓል ቀደም ብሎ ኤርትራ ለነጻነት በምትታገልበት ወቅት በጣሊያኗ ቦሎኛ ከተማ ሲካሄድ የቆየ መሆኑንም መግለጫው ያወሳል። የበቀደሙ በዓል ምንም እንኳን በአዳራሽ ውስጥ በደስታ እና በሰላም እየተካሄደ የነበረ ቢሆንም ከውጭ ግን ዝግጅቱ እንዳይካሄድ ከፍተኛ ሙከራ ይደረግ ነበርም ብሏል፣ የጀርመን ኤርትራውያን ማኅበረሰብ በመግለጫው። መጀመሪያ የጀርመን ሕግን በሚጻረር መልኩ ከጊሰን የከተማ ዝግጅቱ እንዳይካሄድ ለማገድ ተሞከሮ፤ በተለያዩ የፍርድ ቤት ደረጃዎች የእገዳው ውሳኔ መሻሩን፤ በሁለተኛ ደረጃ «ብርጌድ ና ሃመዱ» የተሰኘ ቡድን ቅዳሜ ዕለት የእርስበርስ ጦርነት የመሰለ በዓሉ በሚካሄድበት ስፍራ እንደሚያደርግ በግንኙነት መስመሩ ባሰራጨው መሠረት በተግባር በዓሉ በሚካሄድበት እና በከተማው መሀል በርካታ ሲቪሎችና ፖሊሶች ላይ ጉዳት መድረሱንም ይዘረዝራል። ድርጊቱን አጥብቆ ያወገዘገው በጀርመን፤ የጀርመን ኤርትራውያን ማኅበረሰብ፣ ዝግጅቱ «ለአምባገነን ድጋፍ» ነው መባሉ እንዳሳዘነውም ገልጿል።

በጊሰን ከተማ በተካሄደው የኤርትራውያን ዝግጅት ከነበረው የውጪው ገጽታ በከፊልምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

የጊሰኑን የኤርትራውያን ዝግጅት ተቃውመው በስፍራው ከነበሩት አንዷ ፌበን ጌዶን፣ ኤርትራውያን እናቶች እና አባቶች በልጆቻቸው ሞት ሀዘን ላይ እያሉ የባህል ድግሱ አያስፈልግም ባይ ናት።

« ፌስቲቫል ብለው ነው የተዘጋጁት። ሰኔ 20 ቀን የሰማዕታት ቀን ብለው ሻማ ነው የሚያበሩት። ለእነዚህ የኤርትራ ነጻነትን ለማምጣት ታገሉ ለሚሏቸው የውሸት ሻማ ነው ያበሩት። በዚህ ሁለት ዓመት ደግሞ ብዙ ወጣቶች በነበረው የኢትዮጵያና የትግራይ ጦርነት ሁላችንም እንደምናውቀው ኤርትራም ገብታ ጦርነት አድርጋለች ብዙ ወጣቶችም እዚያ ሞተዋል። የእነዚህ እናቶች ደግሞ ሃዘን ላይ ናቸው። በአሁኑ ሰአት ኤርትራ ጨለማ ውስጥ ነው ያለችው። ሃዘን ላይ እያለች ደግሞ መጥተው ፌስቲቫል ማድረጋቸውን ወጣቱ አልተቀበለውም፤ እኛም አልተቀበልነውም። ሕጋዊ መንገድ ነው ተከትለን የሄድነው። ጠበቃዎች አቁመናል፤ ጉዳዩም ፍርድ ቤት ደርሷል። ይግባኝ ተብሏል። የከተማው አስተዳደርም በጸጥታ ጉዳይ መደረግ የለበትም ብሎ ነበር። ግን ደግሞ ሕዝባዊ ግንባር ተሟሙተው በስተመጨረሻ ማድረግ ይችላሉ ተባለ።»

ፍትሃዊ ሃብተ በጀርመን ፤ የጀርመን ኤርትራውያን ማኅበረሰብ ምክትል ሊቀመንበር ናቸው። እንዲህ ባለው ዝግጅት ላይ ኤርትራውያን ተቃዋሚዎች ሃሳባቸውን የገለጹበት አጋጣሚ ቢኖርም እንደ ዘንድሮው እና እንደአምናው ያለ ብጥብጥ እንዳልነበር ይናገራሉ።

በጊሰን ከተማ ከፖሊሶች ከነበረው ፍጥጫ በከፊል ምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

«እኔም በስፍራው ነበርኩ፤ ከ2011 ጀምሮ ጊሰን ላይ ዝግጅቱ ይካሄዳል። ሁለት ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር፤ የመብት ጉዳይ በመሆኑ በአጸፋው ምንም አላደረግንም። ሰልፎቹ በተቃዋሚዎች ነው የሚዘጋጁት፤ ጥሩ እና መብታቸው ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ያየነው ግን ከዚህ ይበዛል። ምክንያቱ ምንድነው ብለሽ ከጠየቅሽኝ፤ የና ሃመዱ የማሸበር እንቅስቃሴ ነው። በዚህም እርግጠኛ ነን። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በማኅበራዊ መገናኛው አመጽን ይቀሰቅሳሉ፤ ግባችን አንድ ነው ይላሉ ያም፤ በአውሮጳም ሆነ በአሜሪካ የኤርትራውያንን የበዓል ዝግጅቶች እናሳግዳለን የሚል ነው። ከዚህ ጀርባ ማን ነው ያለው ካልሽኝ ተቃዋሚዎች ብቻ አይደሉም። ተቃዋሚዎችማ ሰልፎችን ነበር የሚያደርጉት፤ ሆኖም ግን ተቃዋሚዎች ጥቃት ስለማድረሳቸው የተመዘገበ ነገር የለም።»

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ እዚያ ያለውን ግጭት ወደ አውሮጳ ለማምጣት የመሞከር ነገር አለ ባይ ናቸው በጀርመን ፤ የጀርመን ኤርትራውያን ማኅበረሰብ ምክትል ሊቀመንበር። የጊሰኑን የኤርትራውያን የባህል ዝግጅት ላይ ብጥብጥ የሚያስነሱት ኤርትራውያን ናቸው የሚለውንም አይቀበሉም ፍትሃዊ ሃብተ። በአመጽ ቅስቀሳም ሆነ ለብጥብጡ ማሕበራቸው ተጠያቂ ነው ያለው ብርጌድ ና ሀመዱ ምንድነው፤ እነማንስ ናቸው ይላሉ?

«ብርጌድ ና ሀመዱ አብዛኞቹ ከትግራይ የመጡ ወጣቶች ናቸው። በማኅበራዊ መገናኛው ይገናኛሉ፤ መሪም አላቸው። የጆን ብላክ የማኅበራዊ ትስስር ይባላል፤ ባለፈው ዓመት ነው የተቋቋሙት። ኤርትራን ፎር ብራይት ፊውቸር የተሰኘ ስብስብ አለ፤ ብርጌድ ና ሀመዱ የዚህ የአመጽ ክንፍ ነው። አሰባሳቢው ጆን ብላክ ኔዘርላንድ ነው የሚኖረው። አባላቱም እዚህ ጀርመን ፣ ስዊዘርላንድ እና እንግሊዝ ይገኛሉ። አንድ ግምትም አለ፤ ይህንንም የስዊዘርላንድ እና የኦስትሪያ አምባሳደሮችም ያረጋገጡት ነው፤ አውሮጳ ውስጥ በኤርትራ ስም ጥገኝነት የጠየቁ በርካታ ወጣቶች አሉ።»

ኤርትራ ጨለማ ውስጥ ሆና እንዲህ ያለ በዓል በውጪ ሀገር መዘጋጀት አልነበረትም የምትለው ፌበን ጌዶን፣ ኤርትራውያን አይደሉም ለሚለው ምን ማስረጃ አለ? ስትል ትጠይቃለች።

በጊሰን ከተማ ከታየው በከፊልምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

«እኛ በስደት ነው ያለነው። እነዚህ ውጭ ሲቃወሙ የነበሩትን ተጋሩ ነው የሚሏቸው። እነዚህ ተጋሩ እንጂ ኤርትራውያን አደሉም ይላሉ፤ በምን ማስረጃ? ውጭ የነበሩት አባቶቻቸው እና እናቶቻቸው ተሰውተው እነሱ ሰኔ 20 ሻማ ያበሩላቸው ናቸው። ስለዚህ ማነው ኤርትራዊ እስክስታ የሚወርደው ወይስ መሮት እየታገለ ያለው? እነዚህ ወጣቶች ቢመቻቸው በአገራቸው በኖሩ ነበር። በአገራቸው ሊማሩ ይገባቸው ነበር፤ ሊንደላቀቁ ይገባቸው ነበር። ግን ስንት መከራና ችግር ተሻግረው ነው የመጡት። እናም ኤርትራዊነትን የሚሰጠንና የሚነሳን አንድም ሰው የለም። ኤርትራውነት በጭፈራ ሳይሆን በደም ነው የሚመጣው። ትግሉ ይህ ነበረ። የመኖር ጥያቄ ነው፤ እዚያ ሲጨፍሩ የነበሩት ግን የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ አባቶች እና እናቶች ናቸው። ውጭ የነበሩት ደግሞ 90 በመቶ ወይም 100 በመቶ ወጣቶች ናቸው ብል አልዋሸሁም።»

በጀርመን ፤ የጀርመን ኤርትራውያን ማኅበረሰብ ምክትል ሊቀመንበር  እንደገለጹልን ከዝግጅቱ ተቃዋሚዎች ከ160 በላይ በፖሊስ ተይዘዋል። የበአሉ አዘጋጆችም ከተጠያቂዎች ወገን ናቸው።  ከበዓሉ አዳራሽ ውጪ የተፈጠረው ረብሻ ከበረደ በኋላ  ምንም እንኳን ዝግጅቱ ቢቀጥልም የግለሰብ መብት በወጉ በሚከበርባት ጀርመን በጥገኝነት በዚህች ሀገር የሚኖሩ የውጪ ዜጎች የውህደት ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል። የፖለቲካ ተንታኞች እንዲህ ያለውን ባህላዊ ዝግጅት ማገድ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ሆኖም ግን አዘጋጆቹን ለተፈጠረው ተጠያቂነት እንዲወስዱ ማድረግ አማራጭ መሆኑን ይመክራሉ። ይኽም ቢሆን ሕግ እና ሥርዓት በሚከበርባት ጀርመን አግባብ ባለው መንገድ በሕግ የሚታይ መሆኑንም ያመለክታሉ። 

በፌደራል ጀርመን የሲቪክ ትምህርት ተቋም የኤርትራ መንግሥት በውጪ የሚኖሩ ኤርትራውያን ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እንደሚሞክር መዝግቧል። እንዲህ ያሉ የበዓል ዝግጅቶችም ገንዘብ የማሰባሰቢያ መድረክ መሆናቸውም ይገለጻል። የጀርመን መንግሥት ኤርትራ ነጻነቷን ካወጀችበት ጊዜ አንስቶ እዚህ ከሚኖሩ ዜጎች የሚሰበሰበው ሁለት በመቶ ገንዘብ ከሕግ ውጪ ነው ሲል በተደጋጋሚ መቃወሙ ይታወሳል። 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW