1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተለያዩ ሃገራት የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ

ማክሰኞ፣ መስከረም 15 2016

የዓለም የጤና ድርጅት በመላው ዓለም በኮሌራ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በተለያዩ ሃገራት በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ብቻ ሳይሆን በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መበርከት ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ያመላክታል ብሏል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኮሌራ ታማሚ በሞዛምቢክ ሆስፒታል
በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 ዓ.ም. በመላው ዓለም በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኮሌራ ታማሚ በሞዛምቢክ ሆስፒታል ምስል Sitoi Lutxeque/DW

በየዓመቱ ከ1,3 እስከ 4 ሚሊየን ሕዝብ በኮሌራ እንደሚያዝ የዓለም የጤና ድርጅት አመልክቷል።

This browser does not support the audio element.

በኮሌራ የሚያዘው ሰው ቁጥር መጨመሩ

በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በመላው ዓለም በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የዓለም የጤና ድርጅት ባሳለፍነው ሳምንት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል። ምንም እንኳን የዘንድሮውን የበሽታውን  አጠቃላይ የስርጭት ሁኔታ የሚያመላክት ዝርዝር መረጃ እስካሁን ድርጅቱ ባያገኝም ባለፉት ጎርጎሪዮሳዊ ዓመታት ማለትም በ2022 የነበረው በ2021 ዓ,ም ከነበረው ከዕጥፍ በላይ መሆኑን ያለፈውን ዓመት በተመለከተ የተጠናቀረው መረጃ እንደሚያሳይ ነው የገለጸው። ባለፈው ዓመት የኮሌራ ወረርሽኝ በ44 ሃገራት ውስጥ መከሰቱ የተመዘገበ ሲሆን ኻቻምና 35 ሃገራት ውስጥ በሽታው መከሰቱንም መረጃው ያሳያል። በዚህም ይኽ ተላላፊ በሽታ በየቦታው መከሰቱ ብቻ ሳይሆን ኮሌራብዙ ቦታዎችን ማዳረሱ የጤና ችግሩ አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን አመላካች መሆኑን አሳሳቢ ብሎታል የዓለም የጤና ድርጅት። በተጠቀሱት ጊዜያት አፍጋኒስታን፤ ካሜሮን፤ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ማላዊ፣ ናይጀሪያ፤ ሶማሊያ እንዲሁም ሶሪያ ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሌራ መያዛቸው ተረጋግጦ መመዝገቡንም የድርጅቱ መረጃ ያስረዳል። በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023ም የኮሌራ ስርጭት ተባብሶ መቀጠሉንም ገልጿል።

የኮሌራ ወረርሽኝ በብዛት የተከሰተው በአፍሪቃ ሃገራት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኮሌራ ወረርሽኝ በደቡብ አፍሪቃምስል Shiraaz Mohamed/AFP

ለተባባሰው የኮሌራ በሽታ ስርጭት የአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ

በአሁኑ ጊዜ ኮሌራ በየቦታው ተባብሶ ለመቀጠሉ የአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው የዓለም የጤና ድርጅት ያመለከተው። ከመጠን ያለፈው ዝናብ ፣ ጎርፍ እና ድርቅ ለኮሌራ ወረርሽኝ መከሰት አስተዋጽኦ እንዳለው፤ ከባሕር ላይ የሚነሱት ኃይለኛ ሞገድ እና ውሽንፍሮችም በየቦታው ወረርሽኙ አዳዲስ እንዲቀሰቀስ፣ ያለውም እንዲጠናከር ማድረጋቸውንም ይገልጻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ ዶክተር ወንድወሰን አሞኘም ይኽንኑ ያጠናክራሉ።

የአውሮጳ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል በቅርቡ ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሐሴ ወር መገባደኛ ቀናት ኮሌራ የተከሰተባቸው ሃገራትን ዝርዝር መረጃ ይፋ አድርጓል። በዚህም በተለይ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ሃገራት ኮሌራ መስፋፋቱን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሁለት የደቡብ አሜሪካ ሃገራትም ኮሌራ የበርካቶችን ሕይወት እያወከ፤ እየቀጠፈም መሆኑን ገልጿል። 

የኮሌራ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቀነስ በተለያዩ ሃገራት የኮሌራ ክትባት በዘመቻ ለመስጠት እየተሞከረ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ በሞዛምቢክ የኮሌራ ክትባት ዘመቻምስል Conceicao Matende/DW

በተጠቀሰው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በእስያ አፍጋኒስታን፤ ከ37 ሺህ በላይ የኮሌራ ታማሚ ሲገኝባት፤ 20 ሰዎች ሞተዋል። ባንግላዴሽ የጠፋ የሰው ሕይወት ባይገለጽም ከ41 ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮለራ ተይዘዋል። ፓኪስታን ውስጥ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሰዎች በኮሌራ ሲያዙ፤ ፊሊፒንስ ውስጥ ከሦስት መቶ የሚበልጡ በዚሁ በሽታ መያዛቸው ተመዝግቧል። ታይላንድ ውስጥም በሽታው ጥቂት ሰዎች ላይ ተገኝቷል። በመካከለኛው ምሥራቅ ሶርያ ውስጥ ከ17 ሺህ የሚበልጥ ሰው ነው በኮሌራ የተያዘው፤ 137 ሰዎች በዚሁ በሽታ ሞተዋል። አፍሪቃ ውስጥ ቡሩንዲ፣ ካሜሮን፤ ኮንጎ፤ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፤ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፤ ናይጀሪያ፤ ሶማሊያ፤ ደቡብ አፍሪቃ፣ ዩጋንዳ፤ ታንዛኒያና ዚምባብዌ ውስጥ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል። ከተጠቀሱት ሃገራት በተለይ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ውስጥ ነው በኮሌራ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሎ የሚታየው። ኢትዮጵያ ውስጥ በበሽታው የ78 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ነው የተገለጸው። ከአሜሪካን አካባቢ ሃገራት ሃይቲ ላይ በተጠቀሰው አንድ ወር ጊዜ ,ወደ አምስት ሺህ ገደማ ሰዎች በኮሌራ መያዛቸው፤ 16ቱ ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን የአውሮጳ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ ያመለክታል። ሜክሲኮ እና ዶሜኒካን ሪፑብሊክን የሚመለከቱ አዳዲስ መረጃዎች እንደሌሉት በመግለጽ።

የንጽሕና ይዞታ እና የኮሌራ ትስስር

ኮሌራ፤ ቪብሮ ኮሌራ በተባለ ባክቴሪያ አማክኝነት የሚከሰት፣ በተበከለ ምግብ እና ውኃ ምክንያት የሚመጣ አንጀትን የሚነካ ህመም ይለዋል የዓለም የጤና ድርጅት። ችግሩም ከዝቅተኛ የአኗኗር ይዞታ እና ከንጽሕና ጉድለት ጋር የተገናኘ በቂ ንጹሕ ውኃ እና የንጽሕና መጠበቂያ ስልት በሌለበት የሚስፋፋ እንደሆነም አጽንኦት ይሰጣል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት ባልተሳካባቸው፤ የንጽሕና መጠበቂያ አገልግሎቶችም በሕዝቡ ብዛት ልክ ባልተስፋፋባቸው የኮሌራ መከሰት ብዙም አያስገርምም። ሰዎች የአካባቢያቸውን ንጽሕና ጨምሮ እንዲህ ያለው ወረርሽኝ ሲከሰት ሊያደርጉት የሚገባውን ጥንቃቄ በባለሙያዎች አማካኝነት መምከር ማስተማሩ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚረዳ ነው የሚታሰበው። ሰዎች ኮሌራ በአካባቢያቸው እንዳይከሰት ከተከሰተም እንዳይስፋፋ፤ ለታመሚዎችን ሊያደርጉት ስለሚገባው ጥንቃቄም ባለሙያው ይመክራሉ።

ኮሌራ፤ ቪብሮ ኮሌራ በተባለ ባክቴሪያ አማክኝነት የሚከሰት፣ በተበከለ ምግብ እና ውኃ ምክንያት የሚመጣ አንጀትን የሚነካ ህመም ይለዋል የዓለም የጤና ድርጅት። በበርካታ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት የንጹሕ ውኃ አቅርቦት የኅብረተሰቡ ችግር ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ ሞዛምቢክ የመጠጥ ውኃ ምስል Romeu Silva/DW

እንደ ኮሌራያሉ ተላላፊ በሽታዎች የሰዎች ከተመቻቸ የመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀል ሲታከልበት ስርጭቱን በማባባሱ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ነው ለምሳሌነት ሶርያ፤ የመን እና ሶማሊያን በመጥቀስ የተገለጸው። ኮሌራ እንዳይከሰት የአካባቢን ንጽሕናን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ያሳሰቡት ዶክተር ወንድወሰን የመጸዳጃ ቤቶች አጠቃቀም ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ። በዋናነትም ኅብረተሰቡ ይኽ በሽታ እንዳተወገደ እና ለረዥም ጊዜም መቆየቱን አውቆ የየበኩሉን ጥንቃቄ እየወሰደ ስርጭቱን ቶሎ መግታት እንዲቻል አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርበትም መክረዋል።

በየዓመቱ ከ1,3 እስከ አራት ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ በኮሌራ እንደሚያዝ ያመለከተው የዓለም የጤና ድርጅት፤ ከዚህ መሃል ከ21 ሺህ እስከ 143 ሺህ ገደማ የሚሆነው በበሽታው እንደሚያልቅ አስታውቋል። የአውሮጳ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል በበኩሉ ባወጣው መረጃ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ ባለው የአንድ ወር ጊዜ ብቻ ወደ መቶሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮሌራ መያዛቸውን፤ ከ200 በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው ማለፉን አመልክቷል። ለሰጡን ማብሪያ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪውን እናመሰግናለን።

ሽዋዩ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW