1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳይንቲስቶች በጎርጎሪዮሳዊው 2023 አደገኛ የአየር ጠባይ ይከሰታል ይላሉ

ማክሰኞ፣ ጥር 2 2015

በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት የሚታወቀው ከዜሮ በታች በሚወርድ ቅዝቃዜው ነበር። የዘንድሮው የክረምት ወቅት በዚህ ከቀጠለ የበጋው ሙቀት ትንፋሽ ሊያሳጣ እንደሚችል የሚገምቱ ጥቂት አይደሉም። የክረምቱ አየር በመቀየሩ እንኳን ለሰው ለአዕዋፍም ግራ ማጋባቱ እየታየ ነው።

BdTD Indien | Möwen in Neu-Delhi
ምስል Arrush Chopra/NurPhoto/IMAGO

ጤና እና አካባቢ

This browser does not support the audio element.

 

በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የዘንድሮው የክረምት ወቅት የተለመደው አይነት የአየር ጠባይ እየታየ አይደለም። እዚህ ጀርመን እና አካባቢው ባሉ ሃገራት ለወትሮው ከኅዳር ወር አጋማሽ ይጀምር ነበረው ጠንካራ ቅዝቃዜ ታኅሣሥ ወር አጋማሽ ላይ ለጥቂት ቀናት ብቅ ብሎ ነበር። አሁን በጥር ወር ታይቶ የማይታወቅ የሙቀት መጠን እየተመዘገበ ነው። ክስተቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ ማሳያነቱን የሚናገሩ አሉ።

«እስኪ እነኚህን ወፎች ተመልከታቸው ግራ ገብቷቸዋል፤ እንደተለመደው ክረምት ነው ብለው በቅዝቃዜው ወቅት እንደሚያደርጉት ወደ ደቡብ መሰደድ መወሰን አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ወደ ሰሜን ፈረንሳይ አካባቢ ወደ ደቡብ ኔዘርላንድ ተሰድደው ነበር ሆኖም አየሩ በመሞቁ ወደ ለመዱት ማራኪ አካባቢ ተመልሰው መጥተዋል። ወዲያ እና ወዲህ በመብረር ችግር ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው።»

ምስል Satyajit Shaw/DW

የሚሉት በኔዘርላንድ ስታትቦዝብሄር ከተማ የሚገኙት የደን ተመራማሪ ሀንስ ኤሪክ ከርፐርስ ናቸው። እውነትም እሳቸው እንደሚሉት ለወትሮው የክረምቱ ቅዝቃዜ ሲያይል ወደ ደቡብ ንፍቀ ክበብ ሃገራት የሚሰደዱት አዕዋፍ የክረምቱ ወቅት ሲያበቃ እንደሚያደርጉት ወደ ለመዱት አካባቢ ተመልሰው በማለዳ መንጫጫት ጀምረዋል። በክረምቱ ቅዝቃዜ ድራሻቸው ይጠፋ የነበረው አበቦች፣ እንደውም በአንዳንድ አካባቢዎች የፀደይ ወቅትን ሳይጠብቁ ቅጠል ማቆጥቆጥ አልፎ አልፎም አበቦች አውጥተው ንቦችን መሳባቸው እየታየ ነው። የጀርመን ጎረቤት በሆነችው ኔዘርላንድ ውስጥ ይህን ያስተዋሉት የደን ተመራማሪው ኤሪክ ከርፐርስ በክረምቱ ድራሻቸው ለሚጠፋው በግቢያቸው ላሉት አበቦች አሁን አይሰጉም።  

«እዚህ ጋር ወይን ጠጅ አበቦች አሉን፤ በምሽቱ ቅዝቃዜ ምክንያት ጠውልገው ያድራሉ ብዬ አልሰጋም።  በአሁኑ ጊዜም በዝናብ ማነስ ሊጎዱ ይችላሉ ማለትም አይጻልም። የሞቃቱ ደቡብ እና የደቡብ ምዕራብ ንፋስ ነው አሁን ያለን። በዚህ ምክንያትም ሞቃት የአየር ሁኔታ ይኖራል ብለህ ትጠብቃለህ። በዚያም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ይጨመራል። እናም ተደጋጋሚ ሞቃት ቀኖችን እናያለን ማለት ነው። አሁን ያለውም ይኽ ነው። ሆኖም ግን እንዲህ ያለው ነገር በሞቃት የአየር ንብረት ውስጥም ቢሆን በጣም የተለየ ነው።»

የክረምቱ በረዶ በቻይና ምስል Hector Retamal/AFP

በክረምቱ ቅዝቃዜ ይጠፉ የነበሩ ሌሎች በራሪ ነፍሳት ሳይቀሩ ውር ውር እያሉ ነው። አልፎ ተርፎም የቢብቢም ሆነ ሌሎች ትናንሽ በራሪዎች ንክሻ ሰዎችን እያማረረ መሆኑ ነው የሚነገረው።

ሀንስ ኤሪክ ከርፐርስ ባለፉት ዓመታት ጥቂት የማይባሉት የክረምት ወቅቶች ከተለመደው ወጣ ባለ መንገድ ሞቃት እንደነበሩ አስተውለዋል። ያለፉትን ከዘንድሮው ሲያነጻጽሩትም በእርግጥ የሙቀት መጠናቸው ከዜሮ በላይ ቢሆንም ያን ያህል የሚባሉ አልነበሩም። በእሳቸው ግምትም የዘንድሮው ከቀዳሚዎቹ የክረምት ወቅቶች ሞቃት መሆኑ ወፎቹን አደናግሮ ከተሰደዱበት እንዲመለሱ ቢያደርግም ተፈጥሮ በራሷ ሚዛኗን የምታስተካከልበት መንገድ አላት። ሆኖም ግን መደጋገሙ የስጋት ምንጭ አይሆንም ወይ የሚለው የእሳቸውም ጥያቄ ነው። በዚህ ወቅት ያልተለመደው የአየር ጠባይ በጀርመን እና አውሮጳ ሃገራት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አካባቢዎች መከሰቱን ያስተዋሉት የዘርፉ ተመራማሪዎች ታዲያ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት 2023 ከዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ጋር ተዳምሮ ከባድ የአየር ጠባይ የሚታይበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በማሳሰብ ላይ ናቸው። ይህ የአየር ጠባይም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ኑሮ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ እና በቢሊየን ዶላር የሚገመት ጉዳትም ሊያስከትል እንደሚችልም ገምተዋል። ባለፉት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ፤ ጣሊያን እንዲሁም በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ሃገራት ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ከባድ ጥፋት የሚያስከትሉ ወጀቦች እንዲሁም የባሕር ጠለል ከፍታ መጨመርና የመሳሰሉት ተከስተዋል። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ታዲያ እነዚህ ገና የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው መዘዝ መጀመሪያዎቹ ናቸው። ሳሌሙል ሀክ፤ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሂደት ማዕከል ተመራማሪ ናቸው።  

የስፔን የባሕር ዳርቻ መዝናኛ በክረምት ወቅት ባዶ ነውምስል Juergen Augst/Eibner-Pressefoto/picture alliance

«ፓኪስታን ውስጥ፤ ጎርፍ የተከሰተው፣ 50 በመቶ የሚሆኑት የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ነው ባይ ናቸው። ፍሎሪዳን የመታው ኢያን የተባለው ውሽንፍርና ጎርፍም እንዲሁ 30 በመቶው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ነው ባይ ናቸው። በእነዚህ በምናያቸው የተፈጥሮ ቁጣዎች ሁሉ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ተጽእኖ አለባቸው። የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው የተፈጥሮ አደጋ የቀረ ነገር የለም።»

የአየር ንብረት ለውጡን ያባብሳሉ ተብሎ በኢንዱስትሪ ያደጉትን ሃገራት ተጠያቂ ያደረጋቸው የበካይ ወይም ሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ነው። እነዚህ ሃገራት በየበኩላቸው የሙቀት አማቂ ጋዞች ምንጭ የሆኑ በተለይ የድንጋይ ከሰል የኃይል ማመንጫዎቻቸውን እንዲዘጉ የሚደረገው ግፊት ቀጥሏል። ደቡብ አፍሪቃ ላይ በተካሄደው የተመ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ፕሪቶሪያ የድንጋይ ከሰል የኃይል ማመንጫዋን እንድትዘጋ ከአሜሪካ፤ ጀርመን፤ ፈረንሳይ፣ የአውሮጳ ኅብረት እና ብሪታንያ በጋራ በቢሊየን ዶላር የሚገመት ድጋፍ ሊያደርጉላት ተስማምተዋል። እርግጥ ነው ጀርመንም ሆነች አሜሪካ ለታዳሽ የኃይል ምንጭ ትኩረት መስጠታቸው እንዳለ ሆኖ በድንጋይ ከሰል ኃይል ከሚያመነጩት መካከል ናቸው።

የንፋስ ኃይል ማመንጫምስል Ina Fassbender/AFP/Getty Images

አሁን የአየር ንብረት ለውጥ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ስጋት ብቻ ነው መባሉን ፉርሽ የሚያደርገው ክስተት እያንዳንዱን በኢንዱስትሪ ያደረገ ሀገር ሳይቀር እያዳረሰ መሆኑ እየታየ ነው። ጀርመን እና አካባቢው የጥር ወር ሞቃት ሆነ ይበል እንጂ አትላንቲክ ውቅያኖስን ተሻግሮ ዩናይትድ ስቴትስ እና አካባቢው በበረዶ ውርጅብኝ እና በከባድ ዝናብ ተጨንቋል። ዘገባዎች እንደሚያሳዩትም ካሊፎርኒያ ላይ ከባድ ዝናብ በመውረዱ ጎርፍ ይከተላል በሚለው የከተማዋ ባለሥልጣናት ማስጠንቀቂያ ኗሪዎች ከተማዋን መልቀቅ ጀምረዋል። የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎች የሚያሳዩት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የዘንድሮው የክረምት ወቅት ከመቼውም የከፋ ቀዝቃዛ እንደሚሆን፤ የበጋው ወቅት ደግሞ ሙቀቱ ከፍተኛ እንደሚሆን ነው። አሁን በአውሮጳ ሃገራት የሚታየው በክረምቱ ያልተለመደው ሞቃት አየርም በበጋው ወቅት ሊባባስ ይችላል የሚለው ስጋት አይሏል። በዚሁ ከቀጠለም መጪዎቹ አምስት ዓመታት እጅግ ሞቃት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሜቴሬዎሎጂ ትንበያዎች ያሳያሉ።

ከባድ ጎርፍ በካሊፎርኒያምስል Daniel A. Anderson/ZUMA Wire/IMAGO

እንዲህ ያለውን መዘዝ ለመከላከልም ሆነ ለወደፊትም የአየር ንብረት ለውጡ እንዳይባባስ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ባስቸኳይ መውሰድ እንደሚያስፈልግም በማሳሰብ ላይ ናቸው። ኒው ክላይሜት የተባለው ተቋም ባልደረባ ኒክላስ ኹህነ፤ እንደሚሉት ሩሲያ ዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ የተስተጓጎለው የኃይል አቅርቦት በአንድ ወገን የኃይል ቀውስ ቢፈጥርም ሃገራት ከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ ለሚያደርጉት ጥረት ጉልህ ሚና ይጫወታል። በዚህ መሀል ሁለት ሂደቶች ተከስተዋል፤ በአንድ ወገን ሃገራት ሩሲያ ላይ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ አዲስ የጋዝ እና የነዳጅ ፍለጋ ሲሆን፤ አዳዲስ የነዳጅ ቧንቧ ዝርጋታው፣ የነዳጅ ማጣሪያ እና ማዳረሻ ጣቢያ ግንባታው እንዲጧጧፍ አድርጓል። በሌላ ወገን ደግሞ በስፋት ከፀሐይ እና ንፋስ እንዲሁም ከውኃ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውሮጳ ኅብረት፣ በቻይና እና ሕንድ ውስጥ እየተከናወነ ነው።

የፀሐይ ታዳሽ የኃይል ምንጭምስል FADEL SENNA/AFP/Getty Images

«አሁን ሁሉም የጋዝ ዋጋ መርከሱ ጥሩ ነገር እንዳልሆነ ተረድቷል። ስለዚህ የተለየ ዕቅድ ያስፈልጋል፤ ይኽ ዕቅድ ደግሞ ኃይል መቆጠብ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን መትከል ነው። እናም ሁለት ተፎካካሪ አካሄዶች አሉ። ለእኔ ወሳኙ ጥያቄ የትኛው ያሸንፋል? የሚለው ነው።»

የአየር ጠባይ መዛባት በጊዜው ከሚያስከትለው ይልቅ ውሎ አድሮ የሚያወጣው ተጽዕኖ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ነው ተመራማሪዎቹ የሚያሳስቡት። በጀርመን እና ሌሎች አውሮጳ ሃገራት የተለመደው የክረምቱ ቅዝቃዜ በግብርናው ዘርፍ ከሚኖረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ባሻገር ተሃዋስያንን በመቆጣጠር ለጤናም ቢሆን ሚዛን የሚያስጠብቅ ነው። ተፈጥሮ ስታፈነግጥ ያልተጠበቀው ሊከሰት እንደሚችል ነው መረጃዎች ከወዲሁ የሚያመላክቱት።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW