1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት መንሸራተት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 55 ማሻቀቡ ተገለጸ

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቀጥር ከ55 በላይ መድረሱን የአካባቢው አስተዳደር አስታወቀ። ከሟቾቹ መካከል ሴቶች፣ ሕጻናት እና አደጋ የደረሰባቸውን ለመታደግ ወደ ቦታው ያቀኑ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ፖሊሶች ይገኙበታል።

በጎፋ ዞን የደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ
የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጽህፈት ቤት አደጋው ከደረሰበት ቦታ “ከ55 በላይ አስከሬን መገኘቱን” ገልጿል። ምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቀጥር ከ55 በላይ መድረሱን የአካባቢው አስተዳደር አስታወቀ። ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው አደጋ ሕይወታቸውን ካጡ መካከል ሴቶች እና ሕጻናት ጭምር ይገኙበታል።

አደጋው የደረሰው ሌሊቱን በጣለው ዝናብ በሦስት መኖሪያ ቤቶች ላይ የተጫነውን ናዳ ለማንሳት ጥረት እየተደረገ ባለበት ተጨማሪ ደራሽ ናዳ በመከሰቱ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው አደጋ በሦስት ቤተሰቦች ላይ መከሰቱን የገለጹት አቶ ምስክር “እነሱን ለማትረፍ ብሎ የወጣ ሕዝብ” ላይ ሁለተኛው አደጋ ከረፋዱ 4:00 ሰዓት አካባቢ መከሰቱን ገልጸዋል። አቶ ምስክር አደጋው ከደረሰበት ቦታ “ከ30 በላይ አስከሬን” መውጣቱን ለዶይቼ ቬለ ቢናገሩም ቆየት ብሎ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል።

የዞኑ የሠላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግማዊ ዘሪሁን “ከ55 በላይ አስከሬን መገኘቱን” እንደገለጹ የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ከሟቾቹ መካከል ለህይወት አድን ተግባር ተሰማርተው የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው ፖሊስ አባላት እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው የአስክሬን ፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረው ነበር።

አደጋውን “እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ክስተት” ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “በተፈጠረዉ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የውድ ወገኖቻችንን ህይወት አጥተናል” ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ከተናደ አፈር ውስጥ ቆፍረው ሲያወጡ እና ወደ ሌላ ቦታ ሲያዘዋውሩ በማኅበራዊ ድረ ገፆች የተሰራጩ ምስሎች አሳይተዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW