በጠለምት ወረዳ በዝናብ እጥረት ለችግር የተጋለጡ ወገኖች
ረቡዕ፣ መስከረም 14 2018
የዝናብ እጥረትና መፈናቀል
በአማራ ክልል በዝናብ እጥረትና ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖች ለምግብና ለሌሎች መሠረታዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ተፈናቃዮችና ለዝናብ እጥርት የተጋለጡ ወገኖች ተናግረዋል። እርዳታ በአግባቡ እየቀረበላቸው ባለመሆኑም ችግራቸው ከቀን ወደ ቀን እየባሰ እንደሆነ ነው በስልክ ለዶይቼ ቬሌ የገለፁት። በተከሰተው የዝናብ እጥረት እንስሳቱ ለመኖ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን ከመንግሥት የተደረገ እርዳታም በቂ እንዳልሆነ አስተያየት ስጪዎች ይናገራሉ።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከትግራይ እንደተፈናቀሉ የነገሩን አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የሚሰጠው እርዳታ እነርሱን ያገለለና ከቅርብ አካባቢዎች በድርቅ ለተፈናቀሉ ሰዎች እንደሆነ አመልክተዋል።
የጠለምት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግዛው ዘነበ ቀደም ሲል ለዶይቼ ቪሌ በወረዳው የዝናብ እጥረቱ ያስከተለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በሰጡት መረጃ በወረዳው 11 ቀበሌዎች ከፍተኛ የዝናብ እጥረት በመከሰቱ በ6ሺህ ሔክታር ማሳ ላይ ተዘርቶ የነበረው አልበቀለም፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ እንስሳትም በዚሁ ምክንያት ሞተዋል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድኞች ትብብር
በአካባቢው የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ለማገዝ እረዳታ ለማሰባሰብ በራስ ተነሳሽነት ከተቋቋመ ኮሚቴአስተባባሪዎች መካክል ወጣት ዓለማየሁ አብራሀ እንደገለፀልን በሀገር ውሰጥ አራት እና ከአገር ውጪ ስምንት ያክል አባላት ያሉት ኮሚቴ ባደረገው እንቅስቃሴ 3.2 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብና የምግብ እህል በማቅረብ ከ4,400 በላይ ለሆኑ ወገኖች እገዛ ለማድርግ ተችሏል። ሆኖም ችግሩ በጣም የሠፋ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቋል። ለእርዳታ ማሰባሰቡ እገዛ ላደረጉ የኮሚቴው አባላትና ለአገዙ ወገኖች በሙሉም ምስጋና አቅርቧል።
እገዛ ከተደረገላቸው አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉ በጎ አሳቢ ወገኖች ባደረጉት ድጋፍ 200 ኩንታል የምግብ እህል በዝናብ እጥረት ችግር ላጋጠማቸው የወረዳው ነዋሪዎች መሰጠቱን ተናግረዋል።
ከእርዳታ የተገለለ ተረጂ ስላለመኖሩ
የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት በዞኑ ከ50 ሺህ በላይ የዕለት ድጋፍ ፈላጊዎች እንደሚገኙ አመልክተው፣ «የበጎ ፈቃድ አጋር አካላት እገዛ አድርገዋል» ብለዋል። መንግሥትም የራሱን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከእርዳታ ተገልለናል የሚሉ ወገኖችን ስሞታ «ስህተት» መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው እነኚህ ወገኖች ወደ ቀድሞ የትውልድ ቦታቸው ሄደው እርዳታ እንዲወስዱ ቢነገራቸውም ከከተማ አንወጣም በማለታቸው እንጂ እርዳታ እንዳልተከለከሉ ገልጠዋል።
በጠለምት ወረዳ በተከሰተው የዝናብ እጥረት 5,669 ሔክታር ላይ ተዘርቶ የነበረ ዘር አልበቀለም፣ 3,300 እንስሳት ሞተዋል፣ ከ71,500 በላይ እንስሳት ደግሞ በህመም ላይ መሆናቸውን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ