በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተያየት
ረቡዕ፣ ጥቅምት 19 2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በትናንትናው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት አቶ ታዬ አጽቀሥላሴ ባቀረቡት የ2018 ዓ.ም የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ዋና የትኩረት አጀንዳዎች ላይ የሰጡትን ማብራሪያን አስመልክተው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ይላሉ?
«የጸጥታው ጉዳይ ወደ ተራ ሽፍትነት ማውረዳቸው ስህተት ነው»
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከምክርቤት አባላት የቀረቡትን ጥያቄዎችን ተንተርሰው ያቀረቡት ሰፊ ማብራሪያ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን ያካተተ ነው። ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት አምስት ፓርቲዎችን ማለትም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ እናት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንዲት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን በማቀናጀት ለመርጫ እየተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻል። የቅንጅቱ የሕዝብ ግኑኝነት ሀላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የሰጡት ማብራሪያ በአፈጻጸሙ ልንለያይ እንችላለን እንጂ በመሰረቱ እንደግፋቸዋለን። አገሪቱን እየፈተነ ያለውንና ምርጫውን ለማካሄድም እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚሰጋውን የጸጥታ ሁኔታው ወደ ተራ ሽፍትነት አውርደው መግለጻቸው ግን ስህተት ነው ባይ ናቸው።
« በመሰረታዊ የብሔራዊ ጥቅሞች ላይ በደራረጉ ልዩነት ሊኖረን ይችላል እንጂ እንስማማለን። ይሁንና በምርጫና የጸጥታ ጉዳዮች የሰጡት አተያየት ግን ትክክል አደለም። የምርጫ ዘመቻዎች ለማካሄድ አስቻይ የጸጥታ ሁኔታ በሌበት ሁኔታ ያሉትን ግችቶች ወደ ተራ ሽፍትነት አውርደው መግለጻቸው ትክክል አደለም።»
«በትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተናገሩት ትክክል ነው»
አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ የዓረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ዴሞክራሲ ሊቀመንበር ናቸው። የእሳቸው አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በትግራይ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመክተው በተናገሩት ላይ አተኩረው ነው። አቶ ዓምዶም ሕወሓት ከፋኖ እና ከኤርትራ መንግሥት ጋር እያካሄደው ያለው ትብብር ለቀጠናው ሰላም ስለማይበጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ ትክክል ነው ይላሉ።
«በምርጫው እንቀጥል አንቀጥል አልወሰንም»
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ በብዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ በመሆኑ በዚህች በአጭር ደቂቃ ሁሉንም ላይ ሐሳብ መስጠት ስለማይቻል በምርጫ ጉዳይበማተኮር አስተያየታቸውን የገለጹልን የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ዶክተር አሰፋ አዳነ ናቸው።
«የጸጥታ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው። እንደ እናት ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ እንሳተፍ አንሳተፍ በሚለው ላይ ተነጋግረን አቋም የወሰድንበት ሁኔታ የለም። ግን የመነጋገሪያ ጽሑፎች አዘጋጅተን እየተነጋገርን ነው ያለነው።»
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀይ ባሕር ተጠቃሚነትን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ «ከዚህ ቀደም የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ያደረጉዋቸውና ለሕዝብ ይፋ ያልሆኑ ስምምነቶች በግልጽ ያወጣ ንግግር ነው» ያሉን ደግሞ አንጋፋው ኤርትራዊ ጋዜጠኛና የፖለቲካ አራማጅ አቶ መሀሪ አብርሃም ናቸው።
አያይዘውም ፖለቲከኖቹ ቀጣዩ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሸዋዬ ለገሠ